ጾመ ነቢያት
መምህር ሳምሶን ወርቁ
ነቢያት አስቀመው እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን የተስፋ ቃል እንደሚፈጸም አምነው የአምላክ ሰው መሆንን በተስፋ ጠበቁ፡፡ ምንም እንኳን ለአዳም የተሰጠውን የተስፋ ቃል ከዘመን ደርሰው በዓይናቸው ባይመለከቱም በትንቢት መነጽር ተመልክተው ደስ ተሰኝተዋል፡፡ ነቢያት በየተነሡበት ዘመን ሁሉ የመዳን ቀንን ይናፍቁ ነበር፤ ከዚህ የተነሳ በጾም በጸሎት ስለ መዳን ቀን ወደ እግዚአብሔር ተማጽነዋል፡፡ ይህንን ለመዘከር ቤተክርስቲያን ከኅዳር ዐስራ አምስት አስከ ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ በዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ፤ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ እስከ ታኅሣሥ ሃያ ስምንት ጾም አውጃ እንዲጾሙ ታደርጋለች፡፡
የጾመ ነቢያት ስያሜዎች
ጾመ ነቢያት ምንም እንኳን ዓላማው አንድ ቢሆንም የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡ በዋነኝነት ነቢያት ስለጌታ ሰው መሆንና ስለ ሰው መዳን የጸለዩትን ጸሎት የጾሙትን ጾም በማሰብ፤ የአምላክ ሰው መሆንን ምሥጢር በትንቢት ተመልክተው ለእኛ ለሰው ልጆች የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ አስበው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ለአዳም የተሰጠው ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› የሚለው የተስፋ ቃል መፈጸሚያ ጊዜ እንደደረሰ ስለሚያጠይቅ ጾመ አዳም ይባላል፡፡ ፊሊጶስ በአረማውያን ሀገር ገብቶ ሲያስተምር በሰማዕትነት ዐርፏል፡፡ ሥጋው ለደቀመዛሙርቱ ቢሰወርባቸው እግዚአብሔር እንዲገልጽላቸው ከኅዳር ዐስራ ስድስት ጀምረው ጾመው በሦሥተኛው ቀን ሥጋውን ስለአገኙ እስከ ልደት ድረስ ጹመዋልና ጾመ ፊልጶስ ይባላል፡፡
ቤተክርስቲያን ወቅቱን እንዴት ትዘክረዋለች?
ቤተክርስቲያን ወቅቱን በዘመነ አስተምህሮ እግዚአብሔርን በማዳኑ ያደረገልንን ቸርነት ምሕረት በማሰብ ‹‹የቀደመውን በደላችንን አታስብብን÷ አቤቱ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን›› (መዝ. ፸፰፥፰) እያለች የነቢዩ ዳዊትን የትንቢት ቃል መፈጸሙን ትሰብካለች፡፡ መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ እግዚአብሔር በይቅርታው በማዳኑ መገለጡን እያሰበች ታመሰግናለች፡፡ ስለዚህም ‹‹ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፤ ፊታችሁም አያፍርም፡፡ ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው›› (መዝ. ፴፫፥፭) በማለት አባታችን አዳም በበደሉ ወድቆ በነበረበት ጊዜ በንስሐ ተመልሶ ወደ እግዚአብሔር የጮኸውን ጩኸት የጸለየው ጸሎት እግዚአብሔር ሰምቶ የተስፋ ቃል እንደሰጠው፤ ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ተስፋው እንደተፈጸመ፤ በዚህ የእግዚአብሔር መሐሪነቱ መገለጡን የነቢያቱን ቃል መሠረት አድርጋ ታስተምራለች፡፡
በዘመነ ስብከት ነቢያት የእግዚአብሔር ወልድን በሥጋ መገለጥ በተመለከተ ያስተማሩትን ትምህርት ትሰብካለች፡፡ በሙሴ በነቢያት በመዝሙራት የተነገረለት የአምላክን ሰው መሆን አስቀድሞ ‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም፤ እጅህን ከአርያም ላክ›› (መዝ. ፻፵፫ ፥፯) ብሎ ዳዊት ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔርን ልጁን ከአርያም ልኮ ከኃጢአት ፍዳ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ እንዲያድነው እንደለመነ፤ የለመነው ልመና ጊዜው ሲደርስ በኋለኛው ዘመን እንደተፈጸመ ትሰብካለች፡፡ ወደ እኛ የተላከው ልጁ ብርሃንና እውነት መሆኑን ነቢዩ ዳዊት ሲናገር ‹‹ብርሃንና እውነትን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ›› (መዝ. ፵፫፥፫) ሲል በድጋሜ ተናግረዋል፡፡ ብርሃንና እውነት የተባለ ወልድ፤ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን ሽሮ መርቶ ወደ መንግሥቱ የሚያደርስ መሆኑን አስቀድሞ የተነገረ እንደነበርና አሁን እንደተፈጸመ ትሰበካለች፡፡
ነቢያት ስለ ምሥጢረ ሥጋዌ የተናገራቸው ትንቢታት
በአራቱም ክፍለ ዘመናት፤ በዘመነ አበው፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ ነገሥትና በዘመነ ካህናት የተነሡት ዐበይት ነቢያትና ደቂቀ ነቢያት የእግዚአብሔር ልጅ ቀጠሮ ሲፈጸም ሥጋን እንደሚዋሐድ በብዙ ሕብረ ትንቢት ተናግረዋል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የእመቤታችን ሥጋን መዋሐድ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውሃ ፈሳሽ አይደለም፤ አስቀድሞ ትንቢት አናግሯል፤ ሱባኤ አስቈጥሯል፡፡
ስለ ልደቱ ‹‹ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች÷ ወንድ ልጅም ትወልዳለች÷ ስሙንም ዐማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።›› (ኢሳ. ፯፥ ፲፬) ብሎ ኢሳያስ ሲናገር ነቢዩ ሚክያስ በቤተልሔም እንደሚወለድ ተናግሯል፡፡ ‹‹አንቺም ቤተልሔም ኤፍራታ ሆይ÷ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘለዓለም የሆነ÷ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።›› (ሚክ. ፭፥፪)
ስለ ስደቱ ‹‹እነሆ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እየበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ÷ የግብጽም ልብ በውስጧ ይቀልጣል።›› (ኢሳ.፲፱፥፩) አጋንንትን ከሰው ልቡና እንደሚሰድድ ተናግሯል፡፡ የዲያብሎስን ሥራ ሊያፈርስ በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ ነቢዩ ዳዊት ‹‹ባሕር አየች፤ ሸሸችም፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፤ ተራራዎች እንደ ኰርማዎች፤ ኰረብታዎችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፤ አንቺ ባሕር የሸሸሽ አንቺም ዮርዳኖስ ወደ ኋላሽ የተመለሽ፟ ምን ሆናችኋል›› (መዝ. ፻፲፫፥፫) ሲል ተናግሯል፡፡
በወንጌል ብርሃን ጨለማውን ዓለም እንደሚያበራ ‹‹በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።›› (ኢሳ. ፱፥፪) ሲል ኢሳያስ ሲናገር ይሁዳ በሠላሳ ብር አሳልፎ አንደሚሸጠው ‹‹እነርሱም ለዋጋዬ ሠላሳ ብር መዘኑ።›› (ዘካ. ፲፩፥፲፫) ሐዋርያት እንደሚበተኑም ነቢዩ ዘካርያስ ተናግሯል፡፡ ‹‹እረኛውን ምታ በጎቹም ይበተናሉ›› (ዘካ. ፲፫፥፯) እረኛ የተባለ ጌታ በፈቃዱ በአይሁድ በተያዘ ጊዜ ሐዋርያቱ እንደሚበተኑ አስቀድሞ የተነገረ ነው፡፡ ስለ እኛ መከራ እንደሚቀበል ‹‹እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ÷ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በርሱ ላይ ነበረ÷ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።›› (ኢሳ. ፶፫፥፭) አልፎ ተርፎ ከወንበዴዎች ጋር እደሚሰቀል ‹‹ከዐመፀኛዎችም ጋራ ተቈጥሯልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ተሸከመ ÷ስለ ዐመፀኛዎችም ማለደ።›› ሲል ነቢዩ ኢሳያስ ተናግሯል፡፡ (ኢሳ. ፶፫፥፲፪) በፍጻሜ ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሳ ‹‹እኔ ተኛሁ አንቀላፋኹም እግዚአብሔርም ደግፎኛልና ነቃሁ።›› (መዝ. ፫፥፭) ተነሥቶ እንደሚዐርግ ‹‹አምላክ በእልልታ÷ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ።›› (መዝ. ፵፮፥፭) በማለት ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡
ነቢያት ምሥጢረ ሥጋዌ በትንቢት መነጽር ተመልክተው ደስ ቢሰኙም ከዘመኑ ደርሰው ማየት ግን አልቻለም፡፡ ‹‹እናንተ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩምም÷ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ወደ፟ው አልሰሙም አለ።››(ሉቃ. ፲፥፳፬) ለዚህ ነው ዘመን ገጥሞት ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ የተረዳ፤ የጌታን ልደት የተመለከተ፤ አረጋዊ ስምዖን ሕጻኑ ኢየሱስን በእጁ ዐቅፎ እየባረከ እንዲህ አለ። ‹‹ጌታ ሆይ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና›› (ሉቃ. ፪፥ ፳፱) ሲል ይህም የአምላክ ሰው መሆንን በናፍቆት ይጠባበቁ እንደነበር ያጠይቃል፡፡
በአጠቃላይ የነቢያት የትንቢታቸው ዓላማ የሰው ልጅ ድኅነት ማየት ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ እስራኤል አስቀድሞ ለአበው የተሰጠውን ተስፋ ጸንተው እንዲጠባበቁ በየዘመኑ የተነሡ ነቢያት ያስተምሩ ነበር፡፡ ይህንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲመሰክር ‹‹ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት÷ በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ÷ ስለክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ÷ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር። ለእነርሱም ከሰማይ በተላከ በመንፈስ ቅዱስ ወንጌልን የሰበኩላችሁ ሰዎች አሁን ባወሩላችሁ ነገር እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው፤ ይህንም ነገር መላእክቱ ሊመለከቱ ይመኛሉ።›› (፩ ጴጥ. ፩፥፲)
የነቢያት ትንቢት ዓላማ የሰውን ልጅ ድኅነት ማየት ነበር፤ ይህም ክርስቶስ በሠራልን የማዳን ሥራ ተፈጽፏል፡፡ ከማዳን ሥራው ሱታፌ እንዲኖረን በክርስቶስ የማዳን ሥራ ማመን መሠረታዊ ከሆኑ ምሥጢራትን (ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቊርባን) መፈጸምና በተቀበልነው ጸጋ መንፈሳዊ ተጋድሎ መጋደል ያስፈልጋል፡፡ ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች መካከል ጾም አንዱ ነው፡፡ በጾም እግዚአብሔርን መፍራትን ገንዘብ አድርገን ምሕረትን እናገኛለን (ዕዝ. ፰፥ ፳፫) በጾም ጭንቀታችንን ሐዘናችንን ለእግዚአብሔር እንገልጣለን (መዝ. ፴፬፥፲፫) በጾም በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ እናገኛለን (ኢሳ. ፶፰፥፮) በጾም ለእግዚአብሔር ያለንን አምልኮት እንፈጽማለን፤ (የሐዋ. ፲፫፥፩) በጾም ርኩሳን አጋንንትን ድል እንነሳለን፡፡ (ማር. ፱፥፳፱)
ስለዚህ ቤተክርስቲያን ነቢያት በአምላክ ሰው መሆን የሚገኘውን ድኅነት አምነው መጾማቸውን፤ በጾም የሚገኘውን ዋጋ እያሰበች፤ ሥርዓት ሠርታ፣ ከዐበይት በዓላት አንዱን ልደት በጾም ትቀበላለች፡፡ በተለይ ዛሬ በሰዎች አድሮ ቤተክርስቲያናችንን እየተዋጋን ያለውን ጥንት ጠላታችን ዲያብሎስን ድል መንሳት የምንችለው በጾም ነውና ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ‹‹የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ።›› (ኤፌ. ፮፥፲፩) የጦር ዕቃ የተባለ ጾምን እንደሚገባ ልንታጠቅ ይገባል፡፡ የቀደሙ ቅዱሳን አበው ዲያብሎስንና ሠራዊቱን በጾም ድል ነስተው በትውልድ ቅብብል ዛሬ እዚህ እንደደረሰልን፤ እኛም በጾም ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ድል ነሥተን የቀናች ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ለሚመጣው ትውልድም ብርሃን ሆና እንድትቀጥል ዘመናትን እንድትሻገር በማድረግ በጾም ተጋድሎአችንን ልፈጽም ይገባል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር