የመስቀሉ ነገር

‹‹የመስቀሉ ነገር በሚጠፉት ሰዎች ዘንድ ስንፍና ነውና፥ ለምንድነው ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው›› (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰)
 
የመስቀል ነገር በመጀመሪያ የተገለጸው በመላእክት ዓለም ነበር፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሥነ ፍጥረትን በጻፈበት አክሲማሮስ በተባለ መጽሐፉ እግዚአብሔር መላእክትን ፈጥሮ በተሰወረባቸው ጊዜ ዲያብሎስ እኔ ፈጠርኳችሁ አለ፡፡ ያን ጊዜ በመላእክት ዓለም ረብሻ ሆነ፤ ከፊሉ ዲያብሎስን አምኖ ከእርሱ ጋር ሆነ፤ ቅዱስ ገብርኤል ግን የፈጠረንን እስክናገኝ በያለንበት ጸንተን እንቆይ አለ፤ ቅዱስ ሚካኤልና ሌሎች መላእክትም አብረው ጸንተው ቆዩ፤ ተጠራጥውም ከሁለቱም ጎን ሳይሆኑ የቀሩ ነበሩ፡፡ ከዚያም በመላእክትና በዲያብሎስ መካከል ጦርነት ተጀመረ፤ በተዋጉ ጊዜ ዲያብሎስ ሁለት ጊዜ አሸነፋቸው፤ ሆኖም መላእክት አምላካቸውን ‹‹ፈቃድህ ነውን?›› ብለው ቢጠይቁት፤ ‹‹ፈቃዴስ አይደለም፤ ድል የምታደርጉበትን ኃይል እንድታውቁት ብዬ ነው እንጂ›› ብሎ በክንፋቸው ላይ የብርሃን መስቀል ቀረጸላቸው፤ በእጃቸው ደግሞ የብርሃን መስቀል አስያዛቸው፤ ሔደውም ዲያብሎስን ቢገጥሙት በመስቀሉ ኃይል ድል ነስተውታል፡፡ መላእክት ሳጥናኤልን ድል ያደረጉት በመስቀል ኃይል ነው (ራዕ. ፲፪፥፯፣ መዝ. ፶፱፥፬)፡፡
መስቀል በዘመነ አበው
በዘመነ አበው መስቀል የመባረኪያ ምልክት እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፤ ዘፍጥረት ላይ ፤ ‹‹ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች በእምነት ባረካቸው›› ‹‹ወአስተሐለፈ እዴሁ ላዕለ ርዕሰ ኤፍሬም ወምናሴ፤ እጆቹን በኤፍሬምና በምናሴ ላይ በመስቀል ምልክት አድርጎ ጭኖ ባረካቸው›› ይላል፡፡ (ዘፍ. ፵፰፥፲፩)፤ ዕብ. ፲፩፥፳፪)
ዛሬም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህኑ ቀድሶ በሚወጣበት ጊዜ በእጆቹ ይባርካል፤ ይህም የሚያሳየው ቤተ ክርስቲያኗ መሠረቷ ከላይ በዓለመ መላእክት ከታች ደግሞ በዘመነ አበው ያየነው መስቀል መሆኑን ነው፡፡
መስቀል በብሉይ ኪዳን
መስቀል በብሉይ ኪዳን እንደየሀገሩ ሁኔታ ልዩ ልዩ ተግባራት ሲፈጸምበት ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፡-
፩. ለወንጀለኞች መቅጫነት አገልግሏል
የየሀገሩ መቅጫ የተለያየ ነው፡፡ የጽርዓውያን ሰይፍ፣ የባቢሎን ዕቶነ (እሳት) እና ግበ አናብስት፣ የአይሁድ ውግረተ አዕባን (ድንጋይ)፣ የፋርስ እና የሮም ስቅላት ነው፡፡ ሰዎችን ሰቅሎ መግደል የተጀመረው በፋርስ ነው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰቀለውም ሐማ ነው (መ.አስ. ፯፥፱)፡፡
ሮማውያን ከእነርሱ ወስደው እንደተገበሩት ይነገራል፤ አይሁድም ብዙ ጊዜ ወንጀለኞችን የሚቀጡት በውግራት በእሳት ማቃጠል ቢሆንም በመስቀልም ይቀጡ ነበር፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች አይገረፉም፤ በመስቀል ይቀጡ ነበር፡፡ ከተገረፉ ደግሞ አይሰቀሉም፡፡ (ዘዳ. ፳፩፥፳፩-፳፫) በጌታ ላይ ግን ከሕጋቸው ውጭ ግፍ ፈጽመውበታል፤ ገርፈውም ሰቅለውታል፡፡
፪. ለአርማ ይጠቀሙበት ነበር
የኢትዮጵያ ነገሥታትን ጨምሮ የሌሎች ሀገር ነገሥታትም እንደ አርማ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በእጃቸውም ይይዙት፣ በጦርነት ጊዜም በዘንግ አምሳል እንደሚይዙትና በፈረሶቻቸው ግንባር ላይ ይሥሉት እንደነበር ይገለጻል፡፡ በአጠቃላይ በብሉይ ኪዳን መስቀል በብዙ ኅብር/ምሳሌ ተገልጧል፡፡ ለምሳሌ፡- ሙሴ የኤርትራን ባሕር የከፈለባት በትረ ሙሴ ይባላል(ዘጸ. ፲፬፥፲፮)፡፡
የሙሴ በትር ባሕር ከፍሏል፣ ጠላት አስጥሟል፣ መና አውርዷል፣ ደመና ጋርዷል፣ ውሃ ከዐለት አፍልቋል፣ በግብፃውያን ላይ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ሙሴም ምሳሌው የሆነለት ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀልም ባሕረ እሳትን ከፍሏል፣ ማየ ገቦን ደመ ገቦን ለመጠጣችን ለጥምቀታችን አስገኝቷል፡፡ ኃይሉን በዲያብሎስና በአጋንንት ላይ አሳይቷል፣ ነፍሳትን ከሲዖል ባርነት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነጻ አውጥቷል፡፡
መስቀል በሐዲስ ኪዳን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳም በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ፣ ሰው ሆኖ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በመስቀል ተሰቅሎ፣ ድኅነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ፣ በመስቀሉ ተጣልተው የነበሩ ሰባቱን መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) አስታርቋል፡፡
መስቀል በሐዲስ ኪዳን የመዳን ምልክት መሆኑ የተረጋገጠበት በክርስቶስ ደም የተቀደሰ፣ የጠብ ግድግዳን ያፈረሰ፣ ቅድስናና ክብር ያለው የአበው ተስፋ የተፈጸመበት፣ ሰው ከውድቀቱ የተነሳበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹እግዚአብሔር ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም ወገብረ መድኃኒተ በማእከለ ምድር … እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ›› (መዝ. ፸፫፥፲፪) መድኃኒት መስቀል መድኃኒት ክርስቶስን ተሸክሞ ታየ (ዮሐ. ፲፱፥፲፯፣ኤፌ. ፪፥፲፮፣ ቆላ. ፩፥፳)፡፡
ደመራ
ደመራ ማለት መጨመር፣መሰብሰብ፣መከመር ነው፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግእዝ ቃል አውጥተው ደመራ ግእዝና አማርኛን ያስተባበረ መሆኑን ገልጸው የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት እሌኒ ከቁስጥንጥንያ ተነሥታ ከጌታችን መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ከተቀበረበት ለማውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሔደች፡፡ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ የጌታችን መስቀል ተአምራትን እንዳያደርግ አይሁድ በምቀኝነት ቀብረውት ነበርና የተቀበረበትን ቦታ የሚያሳያት አጥታ በመፈለግ ብዙ ጊዜ አሳለፈች፡፡ በኋላ ግን አንድ ኪራኮስ የሚባል አረጋዊ አካባቢውን ነግሯት ደመራ አስደምራ ዕጣን አጢሳ ወደ ፈጣሪዋ ብትማፀን የዕጣኑ ጢስ ወደ ሰማይ ከወጣ በኋላ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ተመልሶ መስቀሉ የተቀበረበትን ስፍራ አመለከታት፡፡ እርሷም በምልክቱ መሠረት ብታስቆፍር የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር መስቀል አገኘች፤ ከእርሱ መስቀል ጋር ሁለት ወንበዴዎች የተሰቀሉበትን መስቀል አብራ አግኝታው ስለነበር የጌታችን መስቀል ለይታ ያወቀችበት መንገድ ግን ድውያንን በመፈወሱ፣ አንካሳ በማበርታቱ፣ ጎባጣን በማቅናቱ የዕውራንንም ዐይን በማብራቱ ነው፡፡ ስለዚህም በየዓመቱ የመስቀልን በዓል ስናከብር ደመራ የምንደምረውና የምናበራው ንግሥት ዕሌኒን አብነት በማድረግ ነው፡፡
እርስዋም መስከረም ፲፯ ቁፋሮ አስጀምራ መጋቢት ፲ ቀን መስቀሉን አግኝታ አስወጥታ የቤተ ክርስቲያኑም መሠረት ወዲያው እንዲጣል አደረገች፤ የደመራ ሥርዓት ከዚህ ሲያያዝ የመጣ ነው፤ የበረከት በዓል ያድርግልን፤አሜን፡፡
 
መምህር ሸዋገኘሁ ከበደ
Close Menu