የኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮትና እና የፕሮቴስታንት ነገረ መለኮት ልዩነት
( በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ)
( ክፍል ሦስት )
ሥነ ፍጥረት እና ትምህርተ ድኂን
በኦርቶዶክስ እና በፕሮቴስታንት ነገረ መለኮት መካከል ስላለው ልዩነት ስናነሳ፥ ይህ ልዩነት ግልጥ ሆኖ የሚታየው በነገረ ድኂን ( Soteriology) ትምህርታችን ውስጥ እንደሆነ ተናግረናል። በዚህ ክፍል የሥነ ፍጥረትን ትምህርት በጥቅሉ እንዳስሳለን። በሚቀጥለው ክፍል ደግሞ ነገረ ሰብእ ( Anthropology)ከነገረ ድኂን አንጻር እንተነትናለን። ዋናው ዓላማችን ቤተ ክርስቲያን ያላትን የመዳን ትምህርት ከሥር ከመሠረቱ ለማስቀመጥና፥ አንድ ነገር ገንጥሎ ከመከራከርና ከመጯጯህ፥ ሙሉውን ሥዕል ማስጨበጥ እና ትርጉም ያለው ዲያሎግ፥ እውነቱን ለማወቅ በሚወዱ መካከል እንዲፈጠር ነው።
የኦርቶዶክስ የመዳን ትምህርት የሚጀምረው ከፍጥረት ታሪክ ነው። በፕሮቴስታንቱ ዓለም የመዳን ትምህርት የሚጀምረው ከሰው ውድቀት ነው። በሌላ አነጋገር ኦርቶዶክሳዊ የመዳን ትምህርት ዘፍጥረት ፩ እና ፪ን በማተት ሲጀምር የፕሮቴስታንቱ ዓለም ግን በዋናነት ትኩረት የሚሰጠው ዘፍ ፫ ላይ ነው። ይህ ማለት እኛ ዘፍጥረት ፫ን አናይም ማለት አይደለም። ነገር ግን መነሻችን የተለያየ ስለሆነ፥ ዘፍጥረት ፫ን ራሱ ስንተረጉም፥ እኛ ሞት ላይ ትኩረት ስናደርግ፥ ፕሮቴስታንቱ ዓለም ደግሞ ኃጢአት ላይ ትኩረት ያደርጋል። በነገረ ድኂን ላይ የብዙ ክርክሮች መነሻ የሆኑት የሰው ውድቀት፥ ጥንተ አብሶ፥ የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ በሰው ውስጥ እና ሌሎችም አሳቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከዚህ ልዩነት ጋር የተያያዙ ናቸው።
በኦርቶዶክስ የመዳን ትምህርት ውስጥ የሰው ልጆችን መዳን ስንንናገር፥ መጀመሪያ የምናየው ከፍጥረት አውድ አንጻር ነው። ፍጥረትን እግዚአብሔር ለምን እንደፈጠረ፥ እንዴት እንደፈጠረና በፍጥረት ውስጥ የሰው ቦታ የት እንደሆነ አስረግጠን ከተነጋገርን፥ ስለመዳን ትምህርት ጥርት ያለ እይታ ይኖረናል። የመዳን ትምህርት የሚጀምረው ከፍጥረት ታሪክ ነው ብለናል። ይህም ሊታወቅ የእግዚአብሔር ሕዝብ የመዳን ታሪክ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የሚጀምረውም ከፍጥረት ታሪክ ነው። ኦሪት ዘፍጥረት ብሎ ነው የሚጀምረው። ቅዱስ አትናቴዎስ « በእንተ ሥጋዌ On Incarnation » በተሰኘው መጽሐፉ ላይ የመዳናችንን ነገር ሲያወሳ የጀመረው ከፍጥረት ነበር። ምክንያቱን ሲናገር እንዲህ ይላል፦ « ቃለ እግዚአብሔር ወልድ ስለ መዳናችን በሥጋ ለእኛ መገለጡን ስንናገር፥መጀመሪያ ስለ ፍጥረትና ፍጥረትን ስለፈጠረው ስለ እግዚአብሔር መናገር አስፈላጊ ነው። ይኸውም በሐዲስ ተፈጥሮ እንደገና የፈጠረን አካላዊ ቃል፥ ያው እርሱ አስቀድሞም ዓለምን የፈጠረ መሆኑን ለማሳየት ነው።»
ይህ የቅዱስ አትናቴዎስ አሳብ፥ የነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን የወንጌሉን መክፈቻ የሚያሳስብ ነው። ወንጌላዊው ቃል ( ሎጎስ) ሥጋ መልበሱን፥ የሰውን ባሕርይ ገንዘብ ማድረጉን ሲናገር፥ ሁለት ነገሮችን ነው ያነሣው። ይኸውም በመጀመሪያ ቅድመ ዓለም ከአብ ጋር ያለውን ሕላዌ ነው። «በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።» ዮሐ ፩፥፩-፪። ሁለተኛው ደግሞ፥ ይህ አካላዊ ቃል ( ሎጎስ) ፍጥረትን ያስገኘና የደገፈ መሆኑንን ነው። «ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።» ዮሐ ፩፥፫። ለምንድነው ከዚያ የጀመረው፥ እንደ ቅዱስ አትናቴዎስ አነጋገር፥ « ዓለምን በፈጠረበት በልጁ፥ ያንኑ ዓለም እንዳዳነ ለማሳየት ነው።»
በዚህ ምክንያት ቅዱስ አትናቴዎስን ጨምሮ፥ ቀደምት የሆኑት አባቶች ስለ ሥነ ፍጥረት በተለይም በዘፍ ፩ና፪ ላይ ሰፊ ትርጓሜ ጽፈዋል። በዚህ ዙሪያ የተጻፉ፥ትርጓሜዎችና ስብከቶች ሄክሳሜሮን፥ ወይም አክሲማሮስ ( Hexamemeral literature) ይባላሉ። ( ቃሉን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት ፊሎ ዘእስክንድርያ ሲሆን፥ ሄክሳሜሮን ስድስት ቀን እንደማለት ነው።) ለምሳሌ፥ አናስታሲዮስ ዘሲና፥ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፥ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፥ ሳዊሮስ ዘገብላና ኤጲፋንዮስ ከምሥራቁ፥ አምብሮስ ከምዕራቡ ዓለም ሄክሳሜሮን ጽፈዋል። በአገራችን ያለው አክሲማሮስ፥በትውፊት ለቅዱስ ኤጲፋንዮስ የተሰጠ ነው። በአጠቃላይ በሥነ ፍጥረት ዙሪያም ፥ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ፥ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ፥ ሄሬኔዎስ፥ ዮስጢኖስ ሰማዕት ( Justin Martyr)፥ ዮሐንስ ፊሎፖኑስ፥ ቴዎፍሎስ ዘአንጾኪያ፥ ጠርጡልያን የጻፉ ሲሆን፥የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፥ ቄርሎስ ዘእስንድርያ፥ ዲዲሞስ ዘእውሩ፥ አርጌንስ፥ ፊሎ ዘእስክንድርያና፥ ቴዎድሪጥ ዘሳይረስ እንዲሁም ከምዕራብ የአውግስጢኖስ የዘፍጥረት ትርጓሜዎች ከጥንቶቹ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የአገራችን የነገረ መለኮት ሊቃውንትም ለሥነ ፍጥረት ታላቅ ሥፍራ ስለሰጡ፥ ትምህርቱ በቤተ ክርስቲያናችን የሥነ ጽሑፍ ትውፊት ውስጥ ሰፊ ቦታ ይዞ እናገኛለን። አምሥቱ አእማደ ምሥጢርን የሚተረጉሙ የብራና ላይ ጽሑፎቻችንን ካየን ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል የሚጀምሩት ከሥነ ፍጥረት ነው። ከዚህም በተጨማሪ፥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማርኛ ከተጻፉት ወይም ከተተረጎሙት መጻሕፍቶቻችን መካከል አንዱ ሥነ ፍጥረት ነው። ይህ እንግዲህ በአጠቃላይ ሥነ ፍጥረትን መረዳት ለኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያመለክታል። በመሆኑም ቀደምት አባቶች በእነርሱ ዘመንንና በእኛም ዘመን ስለ ፍጥረት የሚነሡትን የስህትተት ትምህርቶች መልስ በመስጠት፥ እግዚአብሔር ፍጥረቱን እንዴት እንዳዳነ በሚገባ አስተምረዋል። እነዚህን ስህተቶች ቅዱስ አትናቴዎስ ቀደም ሲል በጠቀስነው « በእንተ ሥጋዌ On Incarnation» በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፍላችዋል።
የመጀመሪያው በኤፒኩሪያንና በሌሎችም ቁስ አካላውያን ( materialists) ይሰጥ የነበረው ትምህርት ነው። ይኸውም ለዚህ ዓለም ሠራዒ መጋቢ እንደሌለው፥ ዓለም በራሱ እንደተገኘ፥ በድንገትና በዕድል እንደተፈጠረ የሚናገረው ፍልስፍና ነው።
ሁለተኛው የፈላስፋው የፕሌቶና እና የተከታዮቹ አስተሳሰብ ነው። ይኸውም፥ ዓለም ቀድሞ ለዘላለም ከነበረ ቍስ አካል ( creatio ex materia) እንደተፈጠረ የሚናገር ነው። አናጢ ከነበረው እንጨት አንድ ዕቃ እንደሚሠራው እግዚአብሔር አስቀድሞ ከነበረ ቍስ አካል ( pre-existent, eternal matter) ዓለምን ፈጠረ የሚል አስተሳሰብ አለው። ኦርቶዶክሳውያን አባቶች በሚገባ እንዳመለከቱት ይህ የፈላስፎች አመለካከት እግዚአብሔርን የሚወስንና የመፍጠርን ትርጉም የሚያጠብ ነው።
ይህን ትምህርት ሰፋ አድርገን ስናየው፥ ራሱ ፍጥረትን በሁለት ማለት በሚታየው (form) በማይታየው (mind) በመክፈል የማይታየውን የመለኮት ቅጥያ አድርጎ፥ ፍጥረት ከመለኮት የወጣ ( creatio ex deo) አድርጎ ያስቀምጠዋል። በአሁኑ ዘመን በnew age movement አማካይነት በብዙዎች አእምሮ ላይ የሰረጸው፥ ምድርን ወይም ዓለምን መለኮታዊ የማድረግ የሁሉ አምላክነት ( ፓንቴይዝም) ዝንባሌ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው።
ሦስተኛው፥ ከሐዋርያትና ከሐዋርያውያን አበው ዘመን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኳት በነበሩት በግኖስቲኮች ይነገር የነበረው ነው። እንደ እነርሱ ትምህርት ይህን ግዙፉን ዓለም የፈጠረው እግዚአብሔር ሳይሆን፥ ዴሚአርጅ (ንዑስ አምላክ) ነው። በመሆኑም ይህ ግዙፉ ዓለም በሙሉ ክፉ ነው። ግኖስቲኮች እግዚአብሔርን ከዚህ ዓለም ፍጹም በመለየት፥ ይህን ዓለም የፈጠረው የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነው እግዚአብሔር እንደሆነ ይክዳሉ። ቤተ ክርስቲያን በአንጻሩ ለግኖስቲኮች መልስ የሰጠችው እግዚአብሔር ከፍጥረቱ ጋር ያለውን ግንኙነት በማሳየት ነው። በቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሠረት፥ የሚታየውን እና የማይታየውን ዓለም የፈጠረው፥ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት የሆነው እግዚአብሔር ነው። በጸሎተ ሃይማኖት ላይም « ሁሉን በያዘ ሰማይና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን።» በማለት ያወጀችውም ለዚህ ነው።
የሥነ ፍጥረት ትምህርት እጅግ ሰፊ የሆነ ትምህርት ስለሆነ ወደዚያ ውስጥ በጥልቀት ለመግባት የተነሣንበት ዋና ርዕስ አይፈቅድልንም። ነገር ግን ነገረ ድኂንን ሲያነሱ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት የሚያነሡአቸውን ሁለት ዋና ነጥቦች ነው።
ኦርቶዶክሳውያን አበው ስለ ሥነ ፍጥረት ሲናገሩ በመጀመሪያ፥ የሚያነሡት፥ እግዚአብሔር ፍጥረትን« እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ፤( creatio ex nihilo) ይኸውም፥ ፍጥረትን ከምንም ( out of nothing) ወደ መሆን ማምጣቱን ነው ። ሁለተኛ፥ ሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል መፈጠሩን ነው። እነዚህ ሁለት እውነቶች፥ በሥነ ፍጥረት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የነገረ መለኮት ትምህርታችን ውስጥ፥ ደጋግመን የምናሰላስላቸው እውነቶች ናቸው። እስቲ በዝርዝር እንመልከታቸው።
ሀ. እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረው እምኀበ አልቦ ( ex nihilio) ነው።
እግዚአብሔር ዓለምን እምኀበ አልቦ ማለትም ከምንም ( out of nothing) መፍጠሩን፥ ቅዱስ መጽሐፍ፥ በአንድም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ በብዙ ሥፍራ ተናግሮአል። ቅዱስ አትናቴዎስ ዘፍ ፩፥፩፡ « በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ »። እንዲሁም ዕብ ፲፩፥፫ ላይ «ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።» የሚለውን ጠቅሶ ይህ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑንን አስተምሮአል። ከዚሁም ጋር ከሐዋርያውያን አበው መጻሕፍት አንዱ የሆነው፥ መጽሐፈ ሔርማ « ከሁሉ በፊት፥ ሁሉን በፈጠረና ካለመኖር ወደመኖር ( እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ) ባመጣው በእግዚአብሔር እመኑ» ያለውን በመጥቀስ በመጀመሪያይቱም ቤተ ክርስቲያን ይኸው እውነት እንደነበረ ጠቁሞአል። (ሔርማ ፩፥፩)
ቤተ ክርስቲያን ይህን ዶክትሪን ወይም ዶግማ ስታስተምር የሚከተሉትን ነገሮች እናስተውላለን።
አንደኛ፥ ፍጥረት እምኀበ አልቦ፥መፈጠሩን ስንመለከት፥ የእግዚአብሔር ጸጋ ግልጥ ሆኖ ይታያል። በቁጥር ትምህርት ( በአቡሻህር) « እግዚአብሔር ዓለምን ልፍጠር ብሎ አሰበ፤ አስቦም አለቀረ . . . » እያለ የሚሄድ ንባብ አለ። ምንድነው ያሳሰበው ብለን ስንጠይቅ፥ አንዳችም አስገዳጅ ነገር ኖሮበት፥ ወይም አንዳች አስፈልጎት እንዳልሆነ እናስተውላለን። ። ቅዱስ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ለተሰበሰቡት የግሪክ ፈላስፎች እንደነገራቸው «እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።» ሐዋ ፲፯፥፳፭። ማለትም እግዚአብሔር በአንዳች አይደገፍም። ፍጥረትን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው ለአነዋወሩ አስፈልጎት አይደለም። በቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ላይ እንደተገለጠው፥ « እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ሃሎ እግዚአብሔር በትሥልስቱ፥ እግዚአብሔር በመንግሥቱ፥ እግዚአብሔር በመለኮቱ፤ እግዚአብሔር ከዓለም በፊት እስከ ዘለላለም እግዚአብሔር በሦስትነቱ አለ ፥ እግዚአብሔር በመንግሥቱ እግዚአብሔር በመለኮቱ አለ። ፍጥረትን የፈጠረው፥ በሥላሴ ዘንድ ያለችውን ፍቅር ለፍጥረቱ ሊሰጥ እግዚአብሔር ስለ ወደደ ነው፤ በመሆኑም ፍጥረት የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጫ ነው።
ሁለተኛ፥ፍጥረት እምኀበ አልቦ መፈጠሩን ስንረዳ፥ በእግዚአብሔርና በፍጥረቱ መካከል ፍጹም ልዩነት እንዳለ እናያለን። የግሪኮችን ፍልስፍና እና በዘመናችንም ያሉትን የስህተት ትምህርቶች ስንመለከት፥ በፈጣሪና በፍጥረት መካከል ያለውን ግንኙነት ያደበዝዙታል። ፕላቶናዊ የሆነው አስተሳሰብ ፍጥረትን መለኮታዊ ለማድረግ ሲሞክር እናያለን። ነገር ግን ፍጥረት እምኀበ አልቦ እንደመጣ ስንናገር ለፍጥረት አስገኝ ፈጣሪ እንዳለው ነው። ዓለም የተፈጠረ ነው። የተገኘው ከምንም ነውና አስገኝ ፈጣሪ አለው። ይህ ፈጣሪ ደግሞ ከፍጥረቱ ፍጹም የተለየ ከፍ ያለ ነው። በአንጻሩ ደግሞ እግዚአብሔር ደግሞ ፈጣሪ ነው እግዚአብሔር ዓለምን በመፍጠሩ፥ በመግቦትና በማዳኑ ለፍጥረቱ ቅርብ ነው። በዚያው መጠን ከመነገር፥ በላይ ፥ከመታሰብ በላይ፥ ከፍጥረቱ በላይ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ለጢሞቴዎስ እንደተናገረው፥«እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤» ፩ ጢሞ ፮፥፲፮።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በዚህ መሠረታዊ እውነት ላይ በመመሥረት የነገረ መለኮት ትምህርቷን በሁለት መንገዶች ትገልጣለች። በአዎንታዊ (Via Positiva) ወይም በግሪኩ ካታፋቲኮስ፥ እና በአሉታዊ Via Negativa) በግሪኩ አፖፋቲኮስ መንገድ ነው። በአዎንታዊ መንገድ እግዚአብሔር በመፍጠር፥ በመመገብና እና በማዳን ራሱን ለፍጥረቱ የገለጠበትና ፍጥረቱን የተገናኘበትን መንገድ የምንገልጥበት ነው። ይህ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ይቅር ባይ፥ መጋቢ፥ አዳኝ፥ ተቤዥ መሆኑን የምንገልጥበት ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን የሚቀርብ ስለሆነ፥ ከመታወቅ በላይ ነው። ይህን በአሉታዊ በአፖፋቲክ እንገልጠዋለን። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴዋ ምስጋናዋ ይህን የሚያንጸባርቅ ነው። ለምሳሌ በቅዳሴ ኤጲፋንዮስ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ይላል። « እስከ ዛሬ የማይሉት ማእከላዊ ነው፤ እስከዚህ የማይሉትም ደኃራዊ ነው። ለአነዋወሩ ጥንት የለውም ለአኳኋኑም ፍጻሜ የለውም፤ ለዘመኑ ቍጥር የለውም፤ ለዓመታቱም ልክ ቍጥር የለውም፤ ለውርዝውናው ማርጀት የለበትም። ለኃይሉም ጽናት ድካም የለበትም፤ ለመልኩም ጥፋት የለበትም፤ ለፊቱ ብርሃንም ጨለማ የለበትም። . . . በኅሊና የማያገኙት ሥውር ነው፤ በልቡናም የማይረዱት ምጡቅ ነው፤ አንሥርት የማይደርሱበት ረጅም ነው፤ ዓሣዎች የማይዋኙበት ጥልቅ ነው፤» እያለ በvia negativa ሲናገር እናገኛለን። ( ይህን እግዚአብሔርን የማወቅን ምሥጢር በምንነጋገርበት ወቅት በስፋት እናየዋለን።) በአጭር ቃል እግዚአብሔርን የምናውቀው የምንረዳው፥ ፍጥረቱን በቀረበበትና ራሱን ለእኛ በገለጠበት መጠን ነው። እኛ የማናውቀው ልንረዳውም የማንችለው፥ ከመታወቅ ያለፈ ባሕርዩን ከእኛ አእምሮ በላይ መሆኑን በመግለጥ በአምልኮ ወደ እርሱ እንቀርባለን። ሙሴ በሞአብ ሜዳ ላይ ለእስራኤላውያን እንዳላቸው፥ «ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው። » ዘዳግ ፳፱፥፳፱።
ሦስተኛ፥ ፍጥረት እምኀበ አልቦ በመፈጠሩ፥ ዘላለማዊ አይደለም። እርሱ የሌለበት ጊዜ አለ። ከዘላለም የነበረው እግዚአብሔር ብቻ ነውና። ዳዊት ስለዚህ ሲናገር መዝ ፹፱፥፪ ላይ « ዘእንበለ ይቁም አድባር ወይትፈጠር ዓለም ወምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም አንተ ክመ፤ ተራሮች ሳይወለዱ ( ሳይቆሙ) ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ።» በማለት የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነት ይናገራል። ይህ ፍጥረት ከዘላለም አለመኖሩ ግን ሌላ ታላቅ አንድምታ አለው። ዓለም እምኀበ አልቦ ከተፈጠረ፥ ዘላለማዊነት ባሕርዩ አይደለም፤ ለዘላለም መኖር አይችልም። ለዘላለም የኖረ ስላይደለ፥ የሙስና ( corruption) ዝንባሌ ሊኖረው ነው። ለጊዜ ተገዥ ነውና ለለውጥ ለብልየት የተገዛ ነው። ይህን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ የምናገኘው ነው። ለምሳ መዝ ፻፩፥፳፭_፳፯ ላይ ይላል። «አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አ ያልቁም።» ልበ አምላክ ዳዊት ሁለት እውነቶችን እያነጻጸረ ነው የሚያሳየን፤ፍጥረትንና እግዚአብሔርን ነው። እማንቱሰ ይትሀጐላ፤ ወአንተሰ ትሄሉ። እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ትኖራለህ፤ ወከመ ሞጣሕት ትዌልጦሙ ወይትዌለጡ አንተሰ አንተ ክመ፤ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤» ይለዋል እግዚአብሔርን። ይህ ብልየት፥ እርጅና ከአልቦነት ወደ አልቦነት መሄድን የሚያመለክት ነው።
አራተኛ፥ ፍጥረት እምኀበ አልቦ በእግዚአብሔር ዕቅድና አሳብ የተፈጠረ ነው፥ ፍጥረት የተፈጠረው የእግዚአብሔርን እንዲካፈል ወይም የክብሩ መገለጫ እንዲሆን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ እንዳሳየን ፍጥረት የእግዚአብሔርን ክብር ሲገልጡ እናያለን። « ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።» መዝ ፲፰፥፩። ፍጥረት የተፈጠረው ለእግዚአብሔር ክብር ነው። ( ይህን በተለይ በፍጥረት ውስጥ የሰውን ሚና በምንነጋገርበት በቀጣዩ ክፍል በሰፊው እናትተዋለን።)
አምስተኛ፥ ፍጥረት እምኀበ አልቦ ስለ ተፈጠረና በራሱ ሕልውና ስለሌለው፥ የሚደግፈው ያስገኘው ( የፈጠረው) አምላክ ነው። በሌላ አነጋገር፥ ያለ እግዚአብሔር ፍጥረት በራሱ ሕልውና የለውም። በነገራችን ላይ ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከሌሎች ቃላት ሁሉ መርጦ ቃል ( ሎጎስ) የሚለውን የተጠቀመበት ምክንያት፥ ዓለም የተገኘበትና የተደገፈበት ዓለም የሚመራበት አካላዊ ቃል እንደሆነ ለማሳየት ነው። ሐዋርያው በመልእክቱ ስለ አካላዊ ቃል «ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤ እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤» ይላል። ( ዕብ ፩፥፪-፫) እምኀበ አልቦ የመጣው ፍጥረት፥ ከሙስና አምልጦ መኖር የሚችለው እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ መልሱ፥ ለዘላለም ከኖረውና፥ ብቸኛውን ሕይወትና የህይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ጋር የማያቋርጥ ኅብረት በማድረግ ፍጥረት በሕይወት ይኖራል።
እስከ አሁን የተነጋገርንባቸውን ጠቅለል አድርገን እንደምድመው። እግዚአብሔር ፍጥረትን እምኀበ አልቦ ፈጥሮአል። ፍጥረት እምኀበ አልቦ የመጣ በመሆኑ፥ አልቦነት ወይም ሙስና ሁል ጊዜ ያንዣብበታል። ማለት ከአልቦነት ስለመጣ ወደ አልቦነት ሊመለስ ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጠረው ለአልቦነት ለጥፋት ሳይሆን በሕይወት እንዲኖር ነው። ይህ ሲባል ደግሞ ለፍጥረት ዘላለማዊነትን አላበሰው ማለት አይደለም። እንዲያ ከሆነ፥ ፍጥረት መለኮት ሆነ ማለት ነው። ነገር ግን ፍጥረት በሕይወት እንዲኖር ከእግዚአብሔር ጋር የማያቋርጥ ኅብረት እንዲኖረው አደረገው። ማለት የፍጥረት የሕይወት ምንጭ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ሕብረት ነው። ጥያቄው ይህ ነው። ታዲያ ፍጥረት ይህን ሕብረት ከእግዚአብሔር ጋር የሚያደርገው እንዴት ነው ብለን ስንጠይቅ፥ መልሱ በሰው በኩል ነው። ሰው የተፈጠረው የፍጥረት መካከለኛ፥ የፍጥረት ንጉሥና ካህን ሆኖ ነበር። ( ሰው እንዴት የፍጥረት መካከለኛ እንደሆነና በሰው ልጅ ውድቀት ምክንያት በፍጥረት መካከል ምን እንደመጣ በሚቀጥለው ክፍል እናያለን።)