የሊቀ መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በዓል (ታህሳስ 19)
ይህን ቀን የምናከብረው አምላካችን፣ ጌታችናን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰለስቱ ደቂቅን ከሚነደው ከእሳቱ እቶን ውስጥ ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ያዳነበትን በማሰብ ነው።
አባቶቻችን እንዳስተማሩን፣ ቅዱስ መጽሐፍም እንደሚነግረን በዚያን ዘመን ጣኦት የሚመለክበት ዘመን ነበር።
እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው ያምኑ የነበሩ ሶሥቱ ወጣቶች፤ አናንያ(ሲድራቅ)፣ አዛርያ (ሚሳቅ)፣ ሚሳኤል(አብድናጎ) ይባሉ ነበር።በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 3 ከቁጥር 1 እስከ መጨረሻው እንደተጻፈው ታሪኩ በአጭሩ እንዲህ ነበር።
ንጉሡ የጣኦት ምስል አሰራ፣ በገሊላ አውራጃ ያለወን ሕዝብ ጠርቶ ለጣኦቴ ያልሰገደ ወደ እሳት ውስጥ ይጣላል ብሎ አወጀ። በዚያን ወቅት እኒያ ሰልስቱ ደቂቅ ነበሩ። የንጉሥ ትእዛዝ ነውና ሕዝብ ሁሉ ለጣኦቱ ሲንበረከክ እነዚያ በእግዚአብሔር አዳኝነት የተማመኑ ሶሥት ወጣቶች ግን ቆመው ያዩ ነበር። የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምንም ነገር አያስፈራውምና ናቡከደናፆር እርሱ ላስቆመው ጣኦት አለመስገዳቸውን ሲሰማ እጅጉን ተናደደ። ከመበሳጨቱም የተነሳ የሚነደውን እሳት ሰባት እጥፍ እንዲነድ አስደረገ። ሦስቱንም ወጣቶች አስሮ እሳቱን እያሳየ ለእኔ ጣኦት መስገድ ይሻላችኋል ወይስ ከዚህ ከሚነደው እሳት መጣልና መቃጠል አላቸው። እነርሱ ግን የምናመልከው አምላካችን ከሚነደው ከእሳቱ እቶን ያድነናል ባያድነንም እንኳ አንተ ለሰራኸውና ለምታምልከው ጣኦት አንሰግድም አሉት። ወዲያውም ንጉሡ ሦስቱን ወጣቶች አስረው ወደ እሳቱ እንዲጥሏቸው ወታደሮችን አዘዘ። ወጣቶቹን አስረው የጣሏቸው ወታደሮች የእሳቱ ወላፈን ሲያቃጥላቸው ሠለስቱ ደቂቅን ግን መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወርዶ እሳቱን አጠፋላቸው። ንጉሡም ናቡከደናጾር በዚያን ጊዜ እንዲህ አለ “ታስረው የተጣሉት ሦስት ነበሩ አሁን ግን አራተኛ ሰው በእሳቱ መካከል ሲመላለስ ይታየኛል” አለ። “ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም። ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እርሱም። እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ። የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ። እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ። መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ። ናቡከደነፆርም መልሶ። መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ። እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ። የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው። (ዳን.3 በሙሉ)
የእግዚአብሔር የማዳኑ ስራ ሲገለጥ ቅዱስ ገብርኤል ሲታይ አዋጅ ሁሉ ተሻረ።
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የመልአኩን የቅዱስ ገብርኤልን ተራዳኢነት በታኅሣሥ 19 ቀን ይህን ዕለት ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡
የዕለቱ ንባባት፦
ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ። ስለዚህም ደግሞ እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥ አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ የእምነትንም ሥራ በኃይል ይፈጽም ዘንድ ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን። 2 ተሰሎ 1፡6-12
እናንተ ግን፥ ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፥ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ። አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፥ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፥ አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ። ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ፥ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን። ይሁዳ 1፡20-25
የጌታም መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ታየው። ዘካርያስም ባየው ጊዜ ደነገጠ፥ ፍርሃትም ወደቀበት። መልአኩም እንዲህ አለው። ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል። እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል። ዘካርያስም መልአኩን። እኔ ሽማግሌ ነኝ ምስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ? አለው። መልአኩም መልሶ። እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፥ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፤ እነሆም፥ በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ፥ ይህ ነገር እስከሚሆን ቀን ድረስ ዲዳ ትሆናለህ መናገርም አትችልም አለው። ሕዝቡም ዘካርያስን ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ መቅደስም ውስጥ ስለ ዘገየ ይደነቁ ነበር። ሉቃስ 1፡11- 21
የቅዱስ ገብርኤል ጥበቃው አይለየን።
ለአምላካችን እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን።