ኒቆዲሞስ
ሊቁ ቅዱስ ያሬድ የታላቁ ዐቢይ ጾም ፯ኛ ሳምንት መጠሪያ አድርጎ በጾመ ድጓው ‹‹ወሀሎ አሐዱ ብእሲ እምፈሪሳውያን ዘስሙ ኒቆዲሞስ፣ ዘሖረ ኀቤሁ ቀዲሙ ሌሊተ፣ ወይቤሎ ለኢየሱስ እጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ፣ አንሥአኒ በትንሣኤከ፤ አስቀድሞ በሌሊት የሄደ ከፈሪሳውያን ወገን ስሙ ኒቆዲሞስ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ ፈጽመህ የተኛህ የአንበሳ ልጅ ኢየሱስ ሆይ በትንሣኤህ አንሳኝ አለው›› እያለ ስለዘመረለት በየዓመቱ ታሪኩ ሲነገር ታላቅነቱ ሲወሳ ይኖራል። (ጾመ ድጓ ዘኒቆዲሞስ ዘሰንበት)
ኒቆዲሞስ ‹‹ቀናዕያንና ወግ አጥባቂዎች›› ከሚባሉት ፈሪሳውያን አለቆች አንዱ ነበር። ነገር ግን ፈሪሳውያን የተሰኙት አይሁድም ስለ መሲሑ መምጣት በነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት ጌታችን ኢየሱስን ካልተቀበሉት ወገን ነበሩ፡፡ (ዮሐንስ ፫፥፴፬)
የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትምህርት የሰሙና የእጆቹን ተአምራት የተመለከቱ ብዙዎች እርሱን ይከተሉት እንደነበር ሁሉ ኒቆዲሞስ ደግሞ የሕዝቡ አስተማሪ ቢሆንም እንኳን በሌሊት ለመማር ወደ ጌታችን ይሄድ ነበር። ቅዱስ አውግስጢኖስ ይህን ሲያስረዳ አንድም ‹‹ሳይማር ያስተምረን ኖሯል?›› ብለው አይሁድ እንዳያቃልሉት ለገዛ ስሙ ሰግቶ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ጨለማው የኦሪት ምሳሌ ስለሆነ ነው። ወንጌልን መማር ወደ ፍጹም ዕውቀት እንደሚያደርስና የድኅነት መንገድ እንደሆነ ስለተረዳ ለመማር ወደ ጌታችን መጣ። (ትርጓሜ ወንጌል ዘዮሐንስ)
ኒቆዲሞስ መምህሩ ኢየሱስ ክርስቶስን ያከበረው ሰግዶ ጭምር ነው። ‹‹ኒቆዲሞስ ሰገደ በመንፈቀ ሌሊት፤ ለዘቀደሳ ለሰንበት፤ ኒቆዲሞስ ሰንበትን ለአያከበረት ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ሰገደ›› እንዲል። (ጾመ ድጓ ዘኒቆዲሞስ ዘሰንበት)
በመምህርነቱ ሳይመጻደቅ ከጌታችን ዘንድ ለመማር መምጣቱ ታላቅነቱን ሲያስረዳ ለዘመኑ መምህራን ደግሞ ትምህርት የሚሆን ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ›› ያለው መዘንጋቱ ‹‹መምህራነ ኮኑ በበደወሉ፤ ፊደላተ ዘኈለቁ ኵሉ፤ ፊደላትን የቆጠሩ ሁሉ በየቦታው መምህራን ሆኑ›› የሚለው ቅኔም በተግባር እየታየ ነው፤ ፊደል የቆጠረው ሁሉ ቀሚስ አሰፍቶ፣ ሰናፊሉን አንሰርትቶ ልስበክ ባይ ሆኗል። እንኳን ከመምህርነት አስቀድሞ ድኅረ መምህርነትም ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማር እንደሚገባ የኒቆዲሞስ ታሪክ ያስረዳናል። (ያዕቆብ ፫፥፬)
ኒቆዲሞስም ወደ ጌታችን ቀርቦ እንዲህ አለው፤ ‹‹መምህር ሆይ፥ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህን ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና፡፡›› ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም›› አለው፡፡ ነገር ግን ኒቆዲሞስ ምሥጢሩ ስላልተገለጠለት ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማሕፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?›› በማለት ጌታን መልሶ ጠየቀው፡፡ ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና›› ሆኖም ኒቆዲሞስ ምሥጢሩ አሁንም ስላልተገለጠለት ‹‹ይህ ሊሆን እንዴት ይቻላል?›› በማለትም ጌታን ጠየቀው፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን እንዴት ይህን አታውቅም? በምድር ያለውን ስንነግራችሁ ካላመናችሁኝ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ እንዲኖር እንጂ እንዲጠፋ አይደለም…፤›› ብሎ አስረዳው፡፡ (ዮሐ. ፫፥፪-፲፭)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢረ ጥምቀትን ያስተማረው ኒቆዲሞስም ትምህርቱን ተረድቶ እስከ መጨረሻው ጸንቶ ለመኖር ችሏል፡፡ ሰውም ሀሉ እኛም በክርስቶስ ክርስቲያን ይባል ዘንድ በዕለተ ዐርብ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቀኝ ጎን በፈሰሰው ማየ ሕይወት መጠመቅ እንዲሁም ከቀደመ ኃጢአቱ መንነጻትና የሥላሴ ልጅነትን ማግኘት ይገባዋል፡፡
ኒቆዲሞስም ይህን ምሥጢር ጌታችን አስተምሮታልና የእርሱ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ ባሻገር በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ በገዛ ሥልጣኑ ነፍሱን ከሥጋው በለየ ጊዜ ክቡር ሥጋውን ወስዶ በክብር ለመገነዝ የበቃ ሰው ሁኗል፡፡
ጌታችንም የተበተኑ ልጆቹን ከትንሣኤው በኋላ ሲሰበስብ ከሁለቱ የኤማሁስ መንገደኞች አንዱ ኒቆዲሞስ ነበር። በዚህም ጌታችን ከትንሣኤው በኋላ ከተገለጠላቸው የመጀመሪያዎቹ ሰዎችም መካከል አንዱ መሆን የቻለ ታላቅ ሰው ነው።
ለኒቆዲሞስ ምሥጢሩን ገልጾ ያዳነውና ያከበረው ጌታችን ለእኛም ምሥጢሩን ይገልጽልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር