‹‹የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?››

‹‹የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?›› (ማቴ.፳፬፥፫)

መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በዓለም ፍጻሜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቃንን በቀኙ ኃጥአንን ደግሞ በግራው ለይቶ እንደየሥራችን ሊፈርድ ይመጣልና ምልክቶቹን እናውቅ ዘንድ በወንጌል ተጽፎልናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስም በደብረ ዘይት ተራራ ተቀምጦ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱም ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው ስለዳግም ምጽአት ጥያቄ አቀረቡለት፤ ‹‹ንገረን፤ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?›› ጌታችንም ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ ‹‹ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ጦርነትን፥ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፤ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው፡፡ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም፣ የምድርም መናወጥም ይሆናል፡፡ እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡ ያን ጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡ ያንጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፡፡ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡ ከዐመጽም ብዛት የተነሣ ፍቅር ከብዙዎች ዘንድ ትጠፋለች፡፡ እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል፡፡ በአሕዛብ ሁሉ ላይ ምስክር ሊሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ያንጊዜም ፍጻሜ ይደርሳል፡፡›› (ማቴ.፳፬፥፫-፲፬)

ጌታችን ኢየሱስ የነገራቸው የዓለም ፍጻሜ ምልክት ለደቀ መዝሙርቱ ቢሆንም ትንቢቱ ግን በእኛ ትውልድ እየተፈጸመ መሆኑን በሚገባ ልናውቅና ተረድተንም የሚጠበቅብንን ጥንቃቄ መፈጸም ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ግን ብዙዎች ዓለም በደረሰችበት የሥልጣኔ ደረጃ የተነሣ የሚኖሩት ምድራዊ ሕይወትን እንጂ መንፈሳዊውን አይደለም፤ ለሃይማኖትም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ያላቸው አመለካከት ከተቀየረ ሰንብቷል፡፡ በእነርሱ አስተሳሰብ ሰዎች ዓለማዊ (በእነርሱ አጠራር ዘመናዊ) ሕይወትን እንዲኖሩ የተፈቀደ ነው፡፡ ነገር ግን በማቴዎስ ወንጌል የተጻፈው የጌታችን ኢየሱስ ቃል እንደነገረን በሰዎች ኃጢአት የተነሣ የምንኖርባት ዓለም የሰይጣን ማደሪያ ወደ መሆን ርሳለች፤ ጌታም ስለምጽአት ቀን የተናገረው ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዝሙርቱ የነገራቸውን ምልክት እያንዳንዱን ነጥለን እንመልከት፡-

‹‹ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ›› (ማቴ.፳፬፥፭)

በተለያዩ ዘመናት ‹‹እኔ ክርስቶስ ነኝ›› በሚል ሐሰተኛ ትንቢት ከሕዝብ ዘንድ ተነሥተው ሰዎችን ሲያውኩ እና ሲያስቱ የነበሩ ከሓድያን ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በሀገራችን ኢትዮጵያ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የተነሡ ሐሳውያን ሰባኪዎች በስሙ ተልከናል በማለት በክርስቶስ ስም የሐሰት ትምህርት ያስተማሩ ነበር፡፡ አሁንም በተመሳሳይ መልኩ በዚህ ዘመን የሚያስተምሩ ሐሰተኞች አሉ፡፡

በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት የእነዚህ ሐሰተኞች የክሕደት ትምህርት ብዙዎችን አስቷል፤ ዛሬም እንደምናየው ብዙዎችን ወደ ጥርጣሬ እና ክሕደት የሚያስገባቸው የሐሳውያን ነቢያት መነሣት ነውና ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ በየትኛው ሰዓት ወይንም ቦታ እንደሚያጋጥሙን ስለማናውቅ እውነተኞቹን ጠንቅቀን መለየት አለብን፡፡ ለምሳሌ ያህል በቴሌቭዥን መስኮታችን ቀርበው እኔ ክርስቶስ ነኝ ብለው እንደ ጌታችን ተአምራት ለማድረግ በማስመል በአስማታቸው የተለያዩ ነገሮች ሲያሳዩን ከርመዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ‹ክሪስ ኤንጅል› በሚል ስያሜ ከምዕራባውያን ወገን የመጣ አንድ ታዋቂ ሰው ጌታችን ለሐዋርያትና ለደቀ መዛሙርቱ በውኃ ላይ ተራምዶ የእምነትን ኃይል እንዳስተማራቸው እርሱ ደግሞ በውኃ ላይ እንደተራመደ በማስመሰል፣ ልጅ የነበረቸውን ሕፃን ደቂቃ ባልሞላት ጊዜ ወደ ብላቴና በመቀየር፣ አንድን ሴት ከወገቧ በታች ለሁለት በመክፈል ልዩ ኃይል እንዳለው በሰዎች ዘንድ ተአማኒት ያገኘ ሰው አለ፡፡ ይህም ሰው የሚጠቀመው የሰይጣንን መንፈስ እንጂ በእግዚአብሔር ኃይል አይደለም፡፡ ነገር ግን የእርሱን ፕሮግራም ብዙዎች ይመለከቱታል፡፡ በዚህም ስለ እርሱ ለማወቅ በሚጥሩ ጊዜ የእርሱን አመለካከት ወደ መቀበልና በሰይጣን ወደ ማመን አንዲሁም እስከማምለክ ደርሰዋል፡፡ ስለዚህም ከእንደነዚህ ዓይነቱ ሰዎች ለመጠበቅ በአካል ብቻም ሳይሆን በዓይናችን የምንመለከታቸውን ወይንም በጆራችን የምንሰማቸውን ማናቸውንም ነገር መመርመር እንዲሁም በጸሎት ከፈተና እንዲያወጣን መማጸን ያስፈልጋል፡፡

‹‹ጦርነትን፥ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ›› (ማቴ.፳፬፥፮)

በዳግም ምጽአት ጌታችን ለፍርድ ከመምጣቱ በፊት በዓለማችን ፍጻሜ ዋዜማ የሆነው ክንውን አንዱ በምድር ላይ ጦርነት በዓለም ሀገራት መካከል ጦርነት መብዛቱ ነው፡፡ ይህን እውነት በጆራችን እየሰማንና በዓይናችን እያየን በመሆኑ ልንክድ አንችልም፡፡ ወንድም ከወንድሙ ጋር ጦርነት ውስጥ ገብቶ ብዙ ወገኖቻችን በሞት እያለቁ ነው፡፡ ይህም የሚያሳየን የዓለም ፍጻሜ ዋዜማ ላይ መሆናችንን ነው፡፡ ስለዚህም ሁላችንም በኃጢአታችን ሳቢያ የመጣብንን ችግር እና መከራ ተቋቁመን እንድናልፍና በዳግም ምጽአት ቀን በቀኙ እንዲያቆመን በንስሓ ኃጢአታችንን ማንጻት እና ሥጋ ወደሙን መቀበል ያስፈልጋል፡፡

‹‹ሕዝብ በሕዝብ ላይ፥ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኀብ፣ ቸነፈርም፣ የምድርም መናወጥም ይሆናል›› (ማቴ.፳፬፥፯-፰)

ሕዝብ በሕዝብ ላይ የተባለው በሀገራችን ሕዝቦች መካከል እንደሚነሡት ዓይነት ፍጅቶች ማለት ነው፡፡ በእነዚህ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል እየተደረጉ ያሉ አስከፊ የእርስ በርስ ግጭቶች ከጉዳታቸው አስከፊነት ባሻገር ዘረኝነትን የሚያስፋፉ በመሆናቸው የእግዚአብሔር ቊጣ በእኛ ላይ እንዲበረታ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ ዘረኝነት እርስ በርስ ከመዋደድ ይልቅ በሰዎች መካከል ጥላቻ እንዲፈጠር ያደረጋል፡፡ ይህንም አምላካችን ፈጽሞ የሚጠላው ነገር በመሆኑ ቸርነቱን ይነፍገናል፡፡

መንግሥት በመንግሥት ላይ ማለት ጎረቤት የሆኑ ሀገራት እርስ በርስ እንደሚፋጁ ጌታችን ሲገልጽልን ነው፤ ለምሳሌ ኢትዮጵያና ግብጽ በዓባይ ወንዝ እንደሚጣሉት፣ እስራኤልና ፍልስጥኤም በሃይማኖት እንዲሁም በድንበር ግጭት እንደሚጣሉት ዓይነት ነው፡፡ አንድ የሀገር መንግሥት በሌላው ላይ የሚያደርገውንም ጥቃት ያመለክታል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ በአንድ ሃይማኖት በአንድነት እንድንኖር እንጂ በሰው ሀገር ድንበር መጣላትም ሆነ ከሌሎች ሀገር ጥቅም ፈልጎ የሀገራትን ድንበር መጣስ፣ ሕዝብን መጨረስ እና ሰላም መንፈግ ወንጀል ከመሆኑ ባሻገር እጁግ ከባድ ኃጢአትም ነው፡፡

በየሀገሩም ረኀብ ቸነፈር፣ የምድርም መናወጥም ይሆናል የተባለው በዓለም ሁሉ ላይ ነጋ ጠባ የምንሰማቸው ዜናዎች ስለእነዚህ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቈጠሩ ሕዝቦች ተርበዋል፤ መድኃኒት ባልተገኘላቸው በሽታዎች ሕይታቸውን አጥተዋል፤ በመሬት መንቀጥቀጥና መንሸራተት እንዲሁም በእሳተ ገሞራ ሀገራቸው ተናውጧል፡፡

በዚህ ጊዜ በዓለማች ላይ በከተሠተው ቸነፈር እና ባስከተለው ረኀብም ልክ ምድር ተናውጣለች፡፡ በየሀገራቱም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በየታው ይሞታሉ፤ ወይንም በዚያ ሳቢያ ንብረተቻውን አጥተው ለረኀብ ይጋለጣሉ፡፡ ይህም እየተፈጸመ ያለው ጌታችን ኢየሱስ እንደተናገረው በዋዜማው ላይ በመሆኑ ገና ያላተፈጸሙ ምልክቶች አሉና ያንን ማወቅ እንዲሁም በኃጢአት ምክንያት የመጣብን መሆኑን በመረዳት በንስሓ መመለስ አለብን፡፡

‹‹ያን ጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፤ ይገድሉአችኋልም›› (ማቴ.፳፬፥፱)

ሰዎች በምድር ላይ በሃይማኖታቸው ታምነው ሲኖሩ ብዙ መከራ ይደርስቸዋል፤ ይራባሉ፤ ይጠማሉ፤ ይታሠራሉ፤ ይሰደዳሉ፤ ይገደላሉ፤ ይህም በዚህ ትውልድ እንደታየውና በርካቶች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች በመሆናቸው እና ማዕተባቸውን አልበጥስም በማለታቸው ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው እንደተሰደዱት፣ ንብረተቻው በመናፍቃን ተቃጥሎባቸው ለረኀብና ለጥም መጋለጥና በግፍ መገደል ለዘመኑ ፍጻሜ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህም መከራዎች የምጥም መጀመሪያዎች ናቸውና በዚህ እንደማያቆም ጌታችን ኢየሱስ በወንጌል ተናግሯል፡፡

ይህም ሁሉ ግን ጌታችን እንደተናረው ቃሉ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነውና ጸንተን ልንኖር ይገባል እንጂ ማማረር የለብንም፡፡ ምክንያቱም በክርስቶስ ክርስቲያን እንድንባል የተቀበለውን መከራ መቀበል እንዲሁም መስቀሉን መሸከም አለብን፡፡

‹‹ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ›› (ማቴ.፳፬፥፱)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኛችን እና ሕይወታችን በመሆኑ በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን ሰዎች ሁላችን በእርሱ በማመናችንና በመታመችን በአሕዛብ ዘንድ የተጠላን እንሆናለን፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት እነርሱ ሐሰተኛ በመሆናቸው ክርስቲያኖች ግን እውነተኛ እና የእውነት መንገድን በመከተላችን፣ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደድን ስንሆን እነርሱ ግን የተጠሉ በመሆናቸው እንዲሁም እነርሱ ለሚገዙለት ባዕድ አምልኮ እኛ ክርስቲያኖች ባለመገዛታችን ይጠሉናል፡፡

ይህ ብቻም አይደለም፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል የሚያስተምሩ የሃይማኖት አባቶችም በአሕዛብ ዘንድ የተጠሉ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የእግዚአብሔርን ቃል ስለሚያስተምሩ ፀረ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በሆኑ መናፍቃን በሙሉ የተጠሉ ናቸው፡፡

‹‹ያንጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፡፡›› (ማቴ.፳፬፥፲)

በዘመኑ ፍጻሜ ሰዎች ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ክደው ሌሎች ሃይማኖቶችን በራሳቸው ፈቃድ በመከተል በተሳሳተ መንገድ ይጓዛሉ፡፡ ሥጋዊ ፍቃዳቸውን ለሟሟላት የሚስማማቸውንና የሚመቻቸውን አመለካከት በመከተል የተለየ ተቋም ይመሠርታሉ፡፡ ለሕገ እግዚአብሔርም፣ ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ተገዢ ከመሆን ይልቅ የሥጋቸውን ፈቃድ የሚያሟላላቸውን አካሄድ ይከተላሉ፡፡ አምልኮተ እግዚአብሔርን የሚፈጽሙበት ቦታ፣ የአለባባስ እና የጸሎት ሥርዓታቸውም ከእውነተኛው መንገድ የተቃረነ ነው፡፡

እነዚህ የሃይማኖት ተቋማትም የተለያዩ ከመሆናቸው የተነሣ በየትኛውም አጋጣሚ ስምምነት ስሌላቸው ይጣላሉ፤ በክፋት ተነሣሥተው እርስ በርሳቸውም ለሞት አሳልፈው ይሰጣጣሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜም ሰዎች በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ሥር በመኖር ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ርቀዋል፡፡ ስለዚህም ወደ ትክክለኛም ሃይማኖት ሊመለሱ ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው ‹‹ጌታ አንድ ነው፤ ሃይማኖትም አንዲት ናት፤ ጥምቀትም አንዲት ናት፡፡›› (ኤፌ. ፬፥፭)

‹‹ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ›› (ማቴ.፳፬፥፲፩)

ጌታችን ኢየሱስ እንደተናገረው በዓለም ፍጻሜ መዳረሻ ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉ፤ በሕዝብ መካከል በሚያስተምሩበት ጊዜ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸው ትንቢት እንዳላቸው በሐሰት ይመሰክራሉ፡፡ የሐሰት ትምህርት ያስተምራሉ፤ ‹‹ራእይም አየን›› በማለት ሐሰት ነገርን ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹በዚያም ቀን ነቢያቱ ሁሉ ትንቢትን ሲናገሩ እያንዳንዱ ስለ ራእዩ ያፍራል፤ ያታልሉም ዘንድ የማቅ ልብስ አይለብሱም።›› (ዘካ. ፲፯፥፬)

በአሁኑ ጊዜም በዓለማችን ውስጥ ሐሰተኞች ነቢያት ስለበዙ ትንቢቱ እየተፈጸመ መሆኑን በመረዳት ሁልጊዜም ከእውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል እንዳንወጣ መጠንቀቅ፣ ለቃሉም መገዛት ያስፈልጋል፡፡

‹‹ከዐመጽም ብዛት የተነሣ ፍቅር ከብዙዎች ዘንድ ትጠፋለች›› (ማቴ.፳፬፥፲፪)

በዓለሙ ፍጻሜ ሰዎች ከአመፃቸው የተነሣ ከፍቅር ይልቅ መለያየትን ይመርጣሉ፤ ከመተሳሰብና መተዛዘን ይልቅ ጭካኔንና ግፍን በሌሎች ላይ ይፈጽማሉ፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ሰዎች እንደ አውሬ እየታደኑ የሚገደሉበት ግፍም የዘመኑ ፍጻሜ ማሳያ ነው፤ በሃይማኖትም ሆነ በዘር አማካኝነት እርስ በርስም እንደ ጠላት የተጨፋጨፉ ነው፡፡

አንዳንዶች ደግሞ በሰዎች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ክፋትን መፈጸም ከመልመዳቸው የተነሣ ወንድሞቻውንና እኅቶታቸውን እንደ ባዳ እስከመቊጠር ይደርሳሉ፤ በዚህም ሰብአዊነትን ያጣሉ፡፡

ነገር ግን ሰዎች በምድር ይኖሩ ዘንድ ፍቅር በመካከላቸው ሊኖር ይገባል፤ በሕይወታቸው ውስጥም የሚያደርጉትን ማንኛውም ምግባር በፍቅር መፈጸም እንጂ በማስመስል መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሁሉን በፍቅር አደርጉ›› በማለት አስተምሯል፡፡ (፩ኛ ቆሮ.፲፮፥፲፬)

‹‹እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል›› (ማቴ.፳፬፥፲፫)

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ይህ ቃል እስከ ዓለም ፍጻሜ ጊዜ ድረስ መከራን ታግሦ መቆየትን ያመለክታል፡፡ በዚህ ትውልድ የምንኖር ሰዎች ዋዜማው ላይ በመሆናችን በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን መከራ በትዕግሥት አልፈን እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ መዝለቅ አለብን፡፡

በርግጥ የምንኖርባት ዓለም በተለይም በዚህ ጊዜ መከራና ሥቃይ የበዛባት በመሆኑ ጊዜው አስከፊ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ውስጥ የተከሠቱ ማኅበራዊ እና ሀገራዊ ችግሮች የሰዎችን ኑሮ ከማቃወስ ባሻገር ለእርስ በርስ እልቂትም አጋላጭ ሆነዋል፡፡ በዚህም መሠረት በአሁኑ ጊዜ በርካቶች በሥቃይ ውስጥ ይገኛሉ፤ እጅጉን ተስፋፍቶ የሰዎችን ሕይወት እየጨረሰ ባለው የኮሮና ቫይረስም የተነሣ ለብዙ መከራ ተዳርገዋል፡፡ ቤተሰቦቻንን አጥተን መኖር፣ ከአጠገባችን የሚኖሩ ጎረቤቶታችን ወይም ዘመዶቻቸን እንደ ቀልድ በበሽታ ሲቀጠፉ እያየን ሥቃያችን ተቋቊመን እና በዚያም ሳቢያ ከገባንበት ችግር እስክንወጣ መታገሥ ሊከብደን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ በእምነት በመጽናት የሚቻል ነውና በእግዚአብሔር ታምኖ መኖር ከእኛ ይጠበቃል፤ በዚህም አምላካችን መከራን አስችሎ ትዕግሥትን ያድለናል፡፡

‹‹በአሕዛብ ሁሉ ላይ ምስክር ሊሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ያንጊዜም ፍጻሜ ይደርሳል››(ማቴ.፳፬፥፲፬)

በዓለም ፍጻሜ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በ፬ቱ ማዕዘናት እንደሚሰበክ በቃሉ ተናግሯል፤ ይህም በክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአሕዛብ መካከል እንኳን ሳይቀር ነው፡፡

በመጨረሻም እግዚአብሔር በሰው ሁሉ ላይ ፍርዱን ሊያደረግ ይህንንም ዓለም ሊያሳልፍ በሚያስፈራ ግርማ ይመጣል፤ ከእርሱም እጅ የሚያመልጥ የለም፡፡

የተወደዳችሁ ምእመናን ሆይ! እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ትንቢቱ አሁን በምንኖርበት ትውልድ እየተፈጸመ ስለሆነም እየደረሱብን ያሉ መከራዎች በኃጢአታችን ምክንያት የሚመጡብን መሆናቸውን ማስተዋል አለብን፡፡ ስለዚህም ጌታችን በትዕግሥት እስከ መጨረሻ እንድጸና እንዳስተማረን በቃሉ ጸንተን መኖር አለብን፡፡እግዚአብሔርም ለእርሱ ከታመንን በጽድቁ ጎዳና እስከ መጨረሻው ይመራናልና በትዕግሥት ያለፍርሃት እስከ ፍጻሜው ድረስ ጸንተን እንጓዝ፡፡

eotcmk.org

Close Menu