♥ የቅዱስ ሚካኤል ክብር ♥
✍በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❖♥ መልአክ የሚለው የግእዝ ቃል ሲኾን “ለአከ” ማለት (ላከ) ማለት ነው፤ ስለዚኽ መልአክ ማለት መልእክተኛ ማለት ነው፤ ይኸውም ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡ የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሰው የሚያመላልሱ ረቂቃን ናቸውና የተሰጣቸው ሥያሜ ነው፡፡
❖♥ ልዑል እግዚአብሔር ሰባቱን ሰማያት ከፈጠረ በኋላ በዚያው በዕለተ እሑድ መላእክትን “እምኀበ አልቦ ኀበ ቦ” (ካለመኖር ወደ መኖር) ማእምራን (ዐዋቂዎች) ለባውያን (አስተዋዮች) አድርጎ ፈጥሯቸዋል፡፡ ከነዚኽ መላእክት ውስጥ አንደኛውና የመላእክት አለቃ የኾነው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡
❖♥ ቅዱስ ሚካኤል የሚመራቸው ነገደ ኀይላት የሚባሉ በኢዮር ሰማይ የሚኖሩ መላእክትን ነው፤ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስም በሥነ ፍጥረት መጽሐፉ ላይ፦
✍️ “ወለራብዕ ጾታ ዐሠርቱ ስሞሙ ኀይላት ወሊቆሙ ሚካኤል ወአንበሮሙ በራብዕ ሰማይ” ይላል አራተኛው ዐሥሩን ነገድ ስማቸውን ኀይላት ሲላቸው እነዚኽም ባለሰይፍ ሲኾኑ የእግዚአብሔርን ወዳጆች ሲጠብቁ ጠላቶቹን ይቀጣሉ፤ የእነዚኽ ነገደ መላእክት አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል ሲኾን በኢዮር በአራተኛው ከተማ አስፍሯቸዋል እንዲል፡፡
❖♥ ሳጥናኤል “እኔ ፈጣሪ ነኝ” ብሎ የክሕደት ንግግርን በተናገረ ጊዜ አስቀድሞ ሰራዊቱን በመያዝ ከነገደ ዲያብሎስ ጋር የተዋጋ መልአክ ነውና፤ ዮሐንስም ስለ ቅዱስ ሚካኤል ኀያልነት በራእ ፲፪፥፯-፱ ላይ፡-
✍️ “በሰማይም ሰልፍ ኾነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፤ ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም ዓለሙንም ኹሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ ርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከርሱ ጋር ተጣሉ” በማለት ዲያብሎስን የተፋለመ መልአክ መኾኑን ገልጾታል፤ በዚኽም “መልአከ ኀይል” ተብሏል፡፡
❖♥ የ99ኙ ነገደ መላእክት አለቃ ስለኾነው ስለ ቅዱስ ሚካኤል ክብር፣ ውበት፣ ምልጃ ማሕቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው እንዲኽ ይላል፡-
💥 ╬ “ክብረ ሚካኤል ናሁ ተዐውቀ
በትሕትናሁ ዐብየ ወልሕቀ
ዲበ አእላፍ ዘተሰምየ ሊቀ
ዘይትዐፀፍ መብረቀ ይተነብል ጽድቀ”
(የሚካኤል ክብረ እነሆ አኹን ታወቀ፤ በትሕናውም ፈጽሞ ላቀ ከፍ ከፍ አለ፤ በአእላፍ ነገደ መላእክት ላይ አለቃን የተባለ መብረቅን የሚጐናፀፍ ርሱ ጽድቅን ይለምናል) ይላል፡-
❤ የ99ኙ ነገደ መላእክት አለቃ ከመኾኑ ጋር ይልቁኑ ዮሐንስ በራእዩ በምዕ 8፡2 ላይ “በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው” ካላቸው፤ ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት በመዠመሪያ የሚጠቀሰው ቅዱስ ሚካኤል ነውና ሊቁ፡-
╬ ♥ “እስመ እምአፉሁ ይወጽዕ ነጐድጓድ
ሕብረ ክነፊሁ ያንበለብል ነድ
እምሊቃነ መላእክት የዐቢ በዐውድ
ሚካኤል ውእቱ መልአኩ ለወልድ”
(የወልድ አገልጋዩ ሚካኤል ነው፤ በዙሪያው ኹሉ ካሉት ከሊቃነ መላእክት ይበልጣል፤ የክንፉ መልክ ነባልባላዊ እሳትን ያቃጥላል፤ ከአንደበቱ ነጐድጓድ ይወጣልና)
╬ ♥“አዕበዮ ንጉሠ ስብሐት
ለሚካኤል ሊቀ መላእክት
ዘይስእል በእንተ ምሕረት
መልአከ ሥረዊሆሙ ለመላእክት”
(የምስጋና ባለቤት ክርስቶስ ለመላእክት ጭፍሮች አለቃቸው የኾነ ስለ ምሕረት የሚማልድ የመላእክት አለቃ ሚካኤልን ከፍ ከፍ አደረገው) በማለት ይጠቅሰዋል፡፡
❖♥ የስሙ ትርጓሜንም ስንመለከት ሚካኤል ማለት ቃሉ የዕብራይስጥ ሲኾን ሚ- ማለት “ማን”፤ ካ- “እንደ”፤ ኤል- “አምላክ” ማለት ነውና ሚካኤል ማለት “መኑ ከመ አምላክ” (ማን እንደ አምላክ) ማለት ነው፡፡
❖♥ የመልክአ ሚካኤል ደራሲም ይኽነን ይዞ፦
╬ “ሰላም ለዝክረ ስምከ ምስለ ስመ ልዑል ዘተሳተፈ
ወልደ ያሬድ ሄኖክ በከመ ጸሐፈ”
(የያሬድ ልጅ ሄኖክ እንደጻፈው ከልዑል ስም ጋር ለተባበረ ስም አጠራርኽ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡
ቅዱስ ያሬድም፡-
💥 ╬ “መልአከ ፍሥሐ ሚካኤል ስሙ
ለመላእክት ውእቱ ሊቆሙ
መልአኮሙ ሥዩሞሙ
የሐውር ቅድሜሆሙ እንዘ ይመርሆሙ”
(ስሙ ሚካኤል የተባለ የደስታ መልአክ ለነገደ መላእክት አለቃቸው ነው፤ የተሾመላቸው አለቃቸው ርሱ እየመራቸው በፊት በፊታቸው ይኼዳል) ይላል
❖♥ በብሉይ ኪዳን ለአበው ነቢያት እየተገለጠ፤ ለሐዋርያትም በስብከት አገልግሎታቸው እየተራዳ፤ ለሰማዕታት፣ ለቅዱሳን አበው በተጋድሏቸው እየተገለጠላቸው አስደሳች መልኩን ያዩት ነበር።
❖♥ ይኽነን የቅዱስ ሚካኤልን ውበት ቅዱስ ያሬድ እንዲኽ ይገልጠዋል፡-
╬ “መልአከ ፍሥሐ ዘዐጽፉ መብረቅ
ሐመልማለ ወርቅ ሚካኤል ሊቅ”
(መጐናጸፊያው መብረቅ የኾነ የደስታ መልአክ፤ አለቃ ሚካኤል የወርቅ ዐመልማሎ ነው)
❖♥ የመልክአ ሚካኤል ደራሲም ይኽነን ውበቱን ሲገልጠው፡-
╬ “ሰላም ለአክናፊከ እለ በሰማያት ያንበለብሉ
ከመ ሠርቀ ፀሓይ ሥነ ጸዳሉ”
(የጸዳሉ ውበት እንደ ፀሓይ አወጣጥ የኾነ በሰማያት ለሚያንበለብሉ ክንፎችኽ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል፡፡
❖♥ ቅዱስ ያሬድ ደግሞ፡-
╬ “ውእቱ ሊቆሙ ወመልአኮሙ ሚካኤል ስሙ
ዐይኑ ዘርግብ ልብሱ ዘመብረቅ
ሐመልማለ ወርቅ”
(ዐይኑ የርግብ (እንደ ርግብ የዋህ፣ ጽሩይ) የኾነ ልብሱ የመብረቅ መጐናጸፊያ የኾነለት የወርቅ ዐመልማሎ ስሙ ሚካኤል የተባለ ርሱ የመላእክት አለቃቸው መሪያቸው ነው) ይላል፡፡
❖♥ መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብብ ሙሴን ከፈርዖን፣ ኢያሱን ከአማሌቅ፣ ሕዝቅያስን ከሰናክሬም፣ ዳዊትን ከጎልያድ እጅ በተራዳኢነቱ የጠበቀ ሲኾን፤ ስለ ቅዱስ ሚካኤል አማላጅነትና ተራዳኢነት ነቢዩ ዳንኤል፡- “ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ…ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርኻለኊ በዚኽም ነገር ከአለቃችኊ ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም… በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብኽ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል” በማለት አማላጅነቱን መስክሮለታል (ዳን ፲፥፲፫፤ ፲፥፳፩፤ ፲፪፥፩)፡፡
❖♥ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነትና አማላጅነት ቅዱስ ያሬድ እንዲኽ ይገልጠዋል፡-
╬💥 በ፲ወ፬ቱ ትንብልናከ ዐቢይ ልዕልናከ
በመንክር ትሕትናከ
አስተምህር ለነ ሰአልናከ”
(በዐሥራ አራቱ ልመናኽ ምልጃኽ፤ በታላቅ ልዕልናኽ በሚያስደንቅም ትሕትናኽ ሚካኤል ትለምንልን ዘንድ ማለድንኽ)
💥╬ “ዘወሀበ ትንቢተ ለኤልዳድ ወሙዳድ
አመ ምጽአቱ ይምሐረነ ወልድ
ሰአል ለነ ሚካኤል መንፈሳዊ ነገድ
ከመ ንክሃል አምስጦ እምሲኦል ሞገድ”
(ለኤልዳድና ለሙዳድ የትንቢትን ጸጋ የሰጠ የሚኾን ወልድ በሚመጣ ጊዜ ይምረን ዘንድ ከረቂቅ ነገድ ወገን የኾንኸው ሚካኤል ከሲኦል እሳታዊ ሞገድ ማምለጥ እንችል ዘንድ ለእኛ ለምንልን) ይላል፡፡
╬💥 “ከናፍሪሁ ነድ ዘእሳት አልባሲሁ ዘመብረቅ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ውእቱ ይዕቀብክሙ ነግሀ ወሠርከ ሌሊተ ወመዐልተ”
❤ (ከናፍሮቹ የእሳት ልብሶቹ የመብረቅ የኾነ የመላእክት አለቃ ሚካኤል በተራዳኢነቱ በጠዋትም፤ በሠርክም፤ በቀንም በሌሊትም ይጠብቃችኊ) እንዲል፤ ሙሴን ከፈርዖን፣ ኢያሱን ከአማሌቅ፣ ዳዊትን ከጎልያድ፣ ሕዝቅያስን ከሰናክሬም፤ ዳንኤልን ከአፈ አናብስት፣ ሶስናን ከረበናት፤ ቅድስት አፎምያን ከዲያብሎስ እጅ በምልጃው የታደገው፤ አስቀድሞም ዘንዶው ዲያብሎስን ተፋልሞ የጣለው ይኽ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በቀንም በሌሊትም ተራድቶ ይጠብቀን እላለኊ (ራእ 12፡7፤ ራእ 13፡1-3)፡፡
❖♥ ቅዱስ ሚካኤልን ጨምሮ እነዚኽ ቅዱሳን መላእክት ሰው የጸለየውን ጸሎት ያቀረበውን መሥዋዕት ቅድመ እግዚአብሔር በማድረስ የእግዚአብሔርን ምሕረት ወደ ሰው በማምጣት ሰውን ከአምላካቸው ጋር በማማለድ ጸንተው ያሉ እንደኾኑ በብዙ ሥፍራ ላይ ተዘርዝሯል፡-
ለምሳሌ ያኽል (ዘፍ 48፥15፤ ዘጸ 23፥20፤ መሳ 6፥11፤ ኢዮ 33፥23፤ መዝ 33፥7፤ 88፥6፤ 90፥11፤ 1ነገ 19፥5፤ 2ነገ 6፥15፤ ዳን 3፥17፤ 4፥13፤ 8፥15-19፤ ዘካ 1፥12፤ ማቴ 18፥10፤ ሉቃ 1፥19፤ 13፥6-9፤ 15፥7፤ ዮሐ 20፥11፤ የሐዋ 12፥6፤ ዕብ 1፥14፤ ራእ 8፥3-4ን ይመልከቱ)፡፡
የመላእክት አለቃ የቅዱስ ሚካኤል በረከት ይደርብን፤
[እናንተም በአስተያየት መስጫው ላይ በረከቱ እንዲያድርባችሁ ይህን የመላእክት አለቃ አወድሱት]
[በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ በድጋሚ ፖስት የተደረገ]