‹ይፈኑ ለክሙ ጰራቅሊጦስሃ፤ አጽናኝ መንፈስ ይልክላችኋል›› (ዮሐ.፲፬፥፲፮)
እንኳን ለበዓለ ጰራቅሊጦስ አደረሳችሁ!
ዲያቆን ይትባረክ መለሰ
ሰኔ ፲፬፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት
የቤዛነት ሥራውን ከፈጸመ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ሲያርግ ለሐዋርያት የሰጣቸው ተስፋ አጽናኝና የእውነት መንፈስ የሆነውን መንፈስ ቅዱስን አብ እንደሚልክላቸው፣ እርሱም አጽናኝ የሆነ ጰራቅሊጦስ እንደሆነ ለዘለዓለሙም ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን ነግሯቸው ነበር፡፡ ጌታችን እንደተናገረውም በሰጣቸው ተስፋ መሠረት ባረገ በዐሥረኛው ቀን በተነሣ ደግሞ በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡ ‹‹ወአነ እስእሎ ለአብ ይፈኑ ለክሙ ጰራቅሊጦስሃ፤ ካልአ ዘይሄሉ ምስሌክሙ ለዓለም፤ እኔም አብን እለምነዋለሁ፤ እርሱም ለዘለዓለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ ሌላ አጽናኝ መንፈስ ይልክላችኋል›› እንዲል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፲፮)
ይህንንም መንፈስ ቅዱስ የወረደበትን ቀን በዓለ ጰራቅሊጦስ እያልን እናከብረዋለን፤ ከጌታ ዐበይት በዓላትም አንዱ ነው፡፡ጰራቅሊጦስ ማለት መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ወይም ለመንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ሌላኛው ስሙ እንደሆነ ከርእሳችን እንረዳለን፡፡‹‹ጰራቅሊጦስ መንፈሰ አብ ወወልድ ስቡሕ፤ ጰራቅሊጦስ የተመሰገነ የአብና የወልድ መንፈስ ነው›› በማለት አምላክነቱን በአንድነት በሦስትነት ጸንቶ የሚኖር እውነተኛ አምላክ፣ ከአብ የሠረጸ የእውነት መንፈስ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ (ሰይፈ ሥላሴ ዘሐሙስ)
ጰራቅሊጦስ ማለት ‹‹መንፈስ ቅዱስ፣ አጽናኝ፣ አስታራቂ፣ አሳምሮ የሚያናግር ማለት ነው›› ይላል፡፡ (ሕያው ልሳን) አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ‹‹ጰራቅሊጦስ›› ማለት ‹‹ናዛዚ፣ መጽንዒ፣ መስተፍስሒ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ በዓለ ሃምሳ፣ የትንሣኤ ሃምሳኛ፣ የዕርገት ዐሥረኛ፣ እሑድ ቀን የሚውል ወዘተ…›› እያሉ ይተረጉሙታል፡፡ (ገጽ ፱፻፯)
በጥቅሉ ጰራቅሊጦስ ማለት መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ያዘኑትን የሚያጽናና፣ የራቁትን የሚያቀርብ፣ የተሰወረውን የሚገልጥ፣ የረቀቀውን የሚያጎላ፣ የተከፉትን የሚያስደስት፣ ለመምህራን አንደበት የሆነ መጽንዒ፣ የሚያጸና፣ መንጽሒ የሚያነጻ ኃጢአትን ይቅር የሚል የሚደመስስ የእውነት መንፈስ፣ የእውነት አምላክ ነው፡፡ ጌታችን እርሱን እስኪልክላቸው ኃይልን ብርታትን እስኪላበሱ አላዋቂዎችን አዋቂ የሚያደርግ ከሣቴ ምሥጢር፣ ፈሪዎችን ደፋር (ጥቡዓን) የሚያድርጋቸው፣ በአሕዛብ በዓላውያን ፊት ያለ ኀፍረት፣ ያለ ፍርሃት እንዲመሰክሩ፣ በእሳቱ፣ በስለቱ እንዳይሸማቀቁ የሚያደርጋቸውን የእውነት መንፈስ እንደሚልክላቸውና እርሱም ለዘለዓለሙ አብሯቸው እንደሚኖር ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር፡፡
እንዲህም ብሏቸዋልና፤ ‹‹ዘኢይክል ዓለም ነሢኦቶ፤ ዓለም እኔን ለሕማም ለሞት አሳልፎ እንዲሰጠኝ ለሕማም ለሞት አሳልፎ ሊሰጠው የማይቻለው፤ እስመ ኢይሬእዮ ወኢየአምሮ፤ አያየውም፤ አያውቀውምና፤ ወአንትሙሰ ተአምርዎ፤ እናንተ ግን ታውቁታላችሁ፤ አድሮባችሁ ይኖራልና በውስጣችሁም ይኖራልና፡፡›› አድሮባቸው የሚኖረውን፣ ሕማመ ሥጋ፣ ድካመ ሥጋን የሚያርቅላቸውን፣ የምሥራቹን ለዓለም ሁሉ የሚያደርሱበትን ኃይል ጸወን የሚሆናቸውን እውነተኛ የሆነ የራሱንና የአባቱን መንፈስ ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን፣ ባረገ በዐሥረኛው ቀን በዕለተ እሑድ ጰራቅሊጦስ የተባለውን የእውነት መንፈስ ላከላቸው፡፡ እርሱ የእውነት መንፈስ ነው አለ፤ የሐሰት መንፈስ አለና ሲለይ ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ በ፻፳ው ቤተ ሰብ ላይ እንደወረደ፡- ‹‹እንዘ ሀለዉ ኩሎሙ ኅቡረ አሀተኔ መጽአ ግብተ እምሰማይ ድምፅ ከመ ድምፀ ነፋሰ ዓውሎ፤በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ ከወደ ሰማይ እንደ ዓውሎ ነፋስ ድምፅ ያለ ድምፅ ነጉዶ ተሰማ …›› (የሐዋ.ሥራ ፪፥፪) ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስትና ሰባ ሁለቱ አርድእት መቶ ሃያው ቤተ ሰብ በኅብረት በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፡፡
ምክንያቱም ከላይ እንዳየነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹አንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም፤ እናንተ ግን ከሰማይ ኃይል እስክትለብሱ ማለትም ሰማያዊ ሀብትን፣ ሰማያዊ ዕውቀትን፣ ሰማያዊ ኃይልን እስክትለብሱ በኢየሩሳሌም ቆዩ›› ብሏቸው ነበርና በኅብረት ይኖሩና፣ በኅብረት ይጸልዩ፣ የተስፋውንም ቃል ይጠብቁ ነበርና ድንገት በተሰበሰቡበት እንደ ዓውሎ ነፋስ ያለ ታላቅ ድምፅ አሰምቶ የተቀመጡበትን ቤት ሞላው፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፪፥፪)
ላንቃ ላንቃ ያለው እሳት መስሎም ታያቸው፤ በሁላቸውም ላይ መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው፡፡ በዚህም ኃይል የሚሆናቸውን፣ ሀብት የሚሆናቸው ዕውቀትን ገንዘብ አደረጉ፡፡ ሁሉም በየራስ በየራሳቸው ሰባ ሁለት ቋንቋ መናገር ጀመሩ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያትና በሌሎቹ ላይ እንደ ነፋሰ ዓውሎ ሆኖ ነው የወረደው፡፡ ምክንያቱም ነፋስ ረቂቅ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ረቂቂ ነውና፤ ነፋስ ኃያል ነው፤ ፍሬውን ከገለባው ይለያል፤ መንፈስ ቅዱስም ጻድቃንን ከኃጥአን ይለያልና፡፡ ነፋስ በምልዓት ሳለ አይታይም፤ አይታወቅም፤ ነገር ግን የሚታወቀው ባሕር ሲያናውጥ፣ ዛፍ ሰያወዛወዝ፣ ቅጠሉን ሲያረግፈው፣ አቧራውን ሲያስነሣው በሥራው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በምልአት ሳለ አይታወቅም፤ ነገር ግን ቋንቋ ሲያናግር፣ ምሥጢር ሲያስተረጉም ይታያልና፡፡ ነፋስ መዓዛ ያመጣል፤ መንፈስ ቅዱስም መዓዛ ጸጋን ያመጣልና በነፋስ ተመስሎ ወርዷል፡፡
ሰባ ሁለት ቋንቋ ሲናገሩም ከልዩ ልዩ ቦታ የተሰበሰቡና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ አይሁድ በዚያ (በኢየሩሳሌም) ነበሩና አደነቁ፤አንዳንዶቹ እንዲያውም ግራ ተጋብተው ‹‹እነዚህ ሰዎች ሁላቸውም የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንደምን እንሰማቸዋለን›› እያሉ ያደንቁ ነበር፤ አንዳንዶቹ ግን ይስቁባቸው ነበር፡፡ምክንያቱም ከከተማ የመጡ እኩያን አይሁድ ሰቃልያነ አምላክ ናቸውና የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ላለማድነቅ በሐዋርያት ላይ ሳቁባቸው፤ ‹‹እሊህ ያልፈላ ጉሽ ጠጅ ጠጥተው የሆነ ያልሆነውን ይቀባጥራሉ›› ብለው ተሳለቁ፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፪፥፭-፲፫)
እንደ እውነቱ ከሆነ ያልፈላ ጉሽ የወይን ጠጅ የጠጣ፣ ጠጥቶም የሰከረ ሰው፣ እንኳን የማያውቀውን ቋንቋ ሊናገር ቀርቶ የሚያውቀውንም በተናገረው አይናገረም፤ ስካር አንደበትን ያስራል፤ ትንፋሽን ያሳጥራል እንጂ አዲስ ቋንቋ፣ ሁላቸውም የሚሰሙት የሀገራቸውን ቋንቋ ሊናገሩ አይችሉም ነበር፡፡ አይሁድ ግን ክፉዎች ነበሩና እውነቱን መቀበል አይሹም፡፡ የዘመናችን መናፍቃንም ወንጌል ተከድኖባቸው፣ እውነቱ ተሸፍኖባቸው፣ በዕውቀት የተራቀቁትን፣ መንፈስ ቅዱስ ተመልተው ምሥጢር የሚያመሠጥሩትን፣ ክብሩን የሚገልጡትን በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ መምህራንን፣ ሊቃውንትን እንደሚያቃልሉትና እንደሚያሾፉ ዓይነት ማለት ነው፡፡
ግን ጊዜው የስካር አይደለም፤ ምክንያቱ ገና ንጋት (ነግህ) ነውና፤ ነቢዩ ኢዩኤል የተናገረው ቢፈጸም ነው እንጂ፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹በሥጋዊ በደማዊ ሰው ሁሉ መንፈሴን አሳድርበታለሁ›› ያለው ጌታ አስቀድሞ በነቢዩ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱ ላይ ስለ መውረዱ አዲስ ዕውቀትን እንደገለጠላቸው ነገራቸው፤ ገሠጻቸው፤ ስለ ጌታችን ወደዚህ ዓለም መምጣት፣ አይሁድ ግን በክፋት እንደሰቀሉት፣ እርሱ ግን በሥጋ ሞቶ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ስለ መነሣቱና ስለማረጉ ለዚህም ምስክሮቹ መሆናቸውን ጭምር ሰበከ፡፡
በዚህ ስብከት ልባቸው ተነካ፤ ጴጥሮስንና ሌሎእንም ‹‹ምን እናድርግ›› አሏቸው፡፡ ጴጥሮስም ‹‹ንስሐ ግቡ፤ ኃጢአታችሁም ይሰረይላችሁ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ›› አላቸው፡፡ (የሐዋ.ሥራ ፪፥፭-፴፰) ቋንቋ የሚያናግረውን፣ በጥበብና በዕውቀት የሚሞላውን፣ በሀብቱ ስቦ በረድኤት አቅርቦ ሀብተ መንፈስ ቅዱስን የሚያሰጥ የኃጢአት ስርየትም የሚገኝበትን በክርስቶስ አምኖ በመጠመቅ የሚገኘውን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ እንዲቀበሉ መከራቸው፡፡ ቃሉንም የሰሙ፣ ሰምተውም ያመኑ ብዙ ነፍሳት ተጠመቁ፤ ቁጥራቸውም ሦስት ሺህ ያህል ነበሩ፡፡
እናም በዓለ ጰራቅሊጦስ እያልን ከዕርገት በዐሥረኛው ቀን፣ ከትንሣኤው በሃምሳኛው ቀን የምናከብረው ታላቅ በዓል መሠረቱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ከሰማያት የወረደበት፣ ለጌታ ቤተ ሰቦች የተገለጠበትና በእያንዳንዳቸው ላይ ያደረበት፣ በዚህም ሕይወት የሚሰጠውን አምላካዊ ዕውቀት ያገኙበት፣ ዓለምን ተዘዋውረው ያስተምሩበትና ተአምራት መንክራት ያድርጉ ዘንድ ሕዝቡንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚጠሩበትን የዓለም ቋንቋ የገለጠበት፣ በዚህም የመንፈስ ቅዱስን ድንቅ ሥራ የተመለከቱ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት ልባቸው የተነካ ብዙዎች በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የተጠመቁበትና ወደ በረቱ የተሰበሰቡበት ድንቅ የተአምራትና የምሥጢር ቀን በመሆኑ እንድናከብረው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተሠርቶልናል፡፡
መጽሐፈ ፍትሐ ነገሥት ‹‹በበዓለ ሃምሳ ሥራ አትሥሩ፤ ነገረ ክርስቶስን ባመኑ ምእመናን ላይ የወረደ መንፈስ ቅዱስ ተገልጦበታልና›› ይላል፡፡ (ፍት.ነገ.አን.፲፱፥፯፻፵) እናም እኛ ክርስቲያኖች ይህንን ታላቅ የበረከት በዓል፣ ይህንን የተቀደሰ ቀን ስናከብረው እንዴት ይሆን? በወይን ጠጅ ሰክረን ወይስ ኃጢአታችን ይሰረይልን ዘንድ ንስሓ ገብተን ወይስ በሌላ ሁኔታ? ጰራቅሊጦስ ነፍስና ሥጋን የሚያጸና፣ ለንጹሐን የክብር አክሊልና ሞገስ ነው፤ ይህን የእውነት መንፈስ በእኛ ላይ ያድር ዘንድ፣ ስብራታችን እንዲጠገን፣ ጎደሏችን እንዲሞላ፣ ድንቁርናችንን እንዲያስወግድ፣ ከኀዘናችን እንዲያጽናናን፣ እንለምነዋለን ወይስ በምግበ ሥጋ ተጠምደን ጨለማውን የማያርቀውን ዕውቀት የማይገልጸውን፣ ኀዘንና ትካዜ የሚጨምረውን የበዓል አከባበር እናከብራለን?
ራሳችንን እንድናይ፣ ንስሐን የሚቀበል፣ ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ የሚያነጻ መንፈስ (ጰራቅሊጦስ) በእውነት ይርዳን! ተቀድቶ የማያልቅ የዕውቀት መጠጥ ነው፤ ምሥጢር ገላጭ በመሁኑ ምሥጢሩን እንዲገልጽልን በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደ መንፈስ ቅዱስ በእኛም ላይ ያድር ዘንድ አእምሮውን፣ ማስተዋሉን እንዲሰጠን መልካም ፈቃዱ ይሁን፤ አሜን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!