እንኳን ለጌታችን፥ ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን፡፡
«የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ካህናት በሕዝቡ ፊት ይሄዱ ነበር።»
(ኢያሱ ፫፥፲፬)
የከተራ እና የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፦
ከመ/ር ሸዋንዳኝ አበራ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ከዘጠኙ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት አንዱ የሆነውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወርዶ በዮሃንስ እጅ የተጠመቀበት ታላቁ የጥምቀት መታሰቢያ በዓል ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁን የጌታችንን፥ የአምላካችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የጥምቀት መታሰቢያ በዓለ ለማክበር በዋዜማው ታቦተ ሕጉን ወደ ተዘጋጀለት ባሕረ ጥምቀት የሚጓዝበት ዕለትም ከተራ ብላ ሰይማዋለች፡፡
በቅድሚያ ከተራ፥ ጥምቀት፥ ገሃድ እና አስተርእዮ የተሰኙት የግእዝ ቃላት ትርጉምን እንመልከት፦
ከተራ፦ ከተረ ከተሰኘው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ከተረ- ከታሪ- ከታር- ከተራ ሲል ትርጉሙም፦ ከለለ- አጠረ- ከበበ-ጋረደ- አቆመ- ከለከለ ይልና ስም ሲሆን የተከለለ፥ የቆመ፥ የታጠረ ውኃ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከተራ ማለት ኩሬውን ወይም ወራጁን ውኃ እንዳይፈስ ማቆም እና መክበብ ማለት እና እንዲሁም ታቦቱን ከቦ፥ አጅቦ መጓዝን የሚያመለክት እና ከዚህም በመነሣት ከተራ በቁሙ ለጥምቀት ዋዜማ ዕለት የተሰጠ ስም ነው፡፡
*(ምንም እንኳን ፍትሕ መንፈሳዊ ፲፭፥፭፻፷፯ በግእዙ ጾመ ድራረ ጥምቀት የሚለውን የአማርኛው ትርጉም የጥምቀት ዋዜማ ጾም ካለ በኋላ በቅንፍ ገሃድ ቢልም የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፓራሞን – የመዘጋጀት ጾም (Paramon) የሚሉት የልደት ዋዜማ ጾም እና እኛ የገሃድ ጾም የምንለው በቃላት ትርጉም አንድ አይደለም፡፡)
ጥምቀት፦ ጠመቀ ከተሰኘው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጉሙም፦ መጠመቅ፥ መታጠብ፥ መነከር፥ መዘፈቅ፥ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፥ ክርስቲያን መሆን ማለት ነው፡፡
ገሀድ፦ ግሂዶት ከተሰኘው የግእዝ ግስ የተገኝ ሲሆን ገሀደ-ይግህድ- ይግሀድ- ገሃዲ-ገሃድያን-ገሃዲት-ገሃድያት- ገሃደ-ተግህደ-ግሁድ-ግሁዳን- ገሃድ- አግሀደ እያለ ይረባል፤ ገሀደ፦ ተገለጠ-መገለጥ-ገለጠ የተገለጠ-ግልጥ ሆነ፥ ይፋ ሆነ፥ ታየ፥ ታወቀ፥ ተረዳ ማለት ሲሆን በአጠቃላይ ገሀድ ማለት መታየት፥ መገለጥ፥ መታወቅ፥ ይፋ ማለት ነው፡፡
አስተርእዮ፦ ርእየ ከተሰኝ የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ርእየ፦ አየ- ተኮረ- ተመለከተ – አስተዋል፥ ረኣዪ – ራእይ- አርአየ- ተርእየ – አስተርአየ- አስተርእዮ- መታየት- ማሳየት- መገለጥ ማለት ነው፡፡
የምእራቡ እና የምሥራቁ ዓለም አብያተ ክርስቲያናትም ኢፒፋኒ (Epiphany) ይሉታል ቃሉም የመጣው ከጥንቱ ግሪክ (ጽርዕ) ማለትም ከኮይኒ ግሪክ (Koine Greek) ኤፒፋኒያ (ἐπιφάνεια, epipháneia) ከሚለው ሲሆን ትርጉሙም፦ መገለጥ፥ መታወቅ፥ መታየት፤ ወይም የእኛም አባቶች ወቅቱን አስተርእዮ ከሚሉት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
በዓሉንም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የመገለጥ፥ የመታየት የመታወቅ በዓል አስተርእዮ- ገሀድ ስትለው፤ የምእራቡና የምሥራቁ ዓለም አብያተ ክርስቲያናትም ኤፒፋኒ- (Epiphany) ኤፒፋኒያ (ἐπιφάνεια) በትርጉም ከእኛው አስተርእዮ እና ገሀድ ጋር አንድ ነው፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ሥርዓት መሠረት ከእያንዳንዱ ደብር በጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ተነሥቶ ወደ ተዘጋጀው ጥምቀተ ባሕር የሚጓዘው ጌታችን የጥምቀት ሥርዓትን ለመፈጸም ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መሄዱን ለማጠየቅ ነው፡፡
ጥምቀት የተሰኘው ታላቅ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ከውኃ ሲወጣ፥ ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድና በእርሱ ላይም ሲመጣ፥ ድምጽም ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው (ማቴዎስ ፫፥፲፮-፲፯) በማለት የማይታየው መለኮት የተገለጠበት እግዚአብሔር በአካላት ሦስት (ሥላሴ) መሆኑ የታየበት፥ የታወቀበት፥ ገሀድ የሆነበት፥ የተገለጠበት የጥምቀት በዓል ነው፡፡
አስተርእዮ ወይም ገሃድ የተባለበትም ምክንያት ወንጌላዊውና ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ «ቃል ሥጋ ሆነ፤» (ዮሐ.፩፥፲፬) እንዳለው ጌታችን፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በቤተልሔም ከእመቤታችን ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ተወልዶ የማይታየው መለኮት የሰውን ልጅ ሥጋ ነስቶ በመታየቱ፤ (ሉቃስ ፪፥፯-፲፬)
እንዲሁም ወልድ በዮርዳኖስ ወንዝ በዘካርያስ ልጅ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ፥ አብ ከሰማይ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው ሲል፥ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ሲወርድ ሦስቱ አካላት አንድ ላይ በአንድ ቦታ በመታወቃቸው መታየታቸውን፥ መገለጣቸውን ለማስረዳት፤ (ማቴ.፫፥፲፮-፲፯)
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሆኖ ሳለ በትህትና ዝቅ ብሎ በአገልጋዩ በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት ምክንያት አንድነቱንና ሦስትነቱን ለመግለጽ፥ የእኛንም የዕዳ ደብዳቤ በመለኮታዊ ኃይሉ ለመደምሰስ፥ በእርሱ ጥምቀት የእኛን ጥምቀት ለመቀደስ፥ የእግዚአብሔር ልጅነትን ሊሰጠን፥ የጽድቅ ሥራንና ትህትናን ሊያስተምረንና አርአያና ምሳሌ ሊሆነን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በሠላሳ ዘመኑ ጥር አሥራ አንድ ቀን ከንጋቱ በአሥረኛው ሰዓት ተጠምቋል፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአካባቢው ካሉት ወንዞች ይልቅ ራቅ የሚለውን መርጦ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዞ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቅበት ምክንያት ሲኖረው ይህንንም ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊት፦ «ባሕርኒ ርእየት ወጐየት፤ ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ። ባሕር አየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፤» (መዝ.፻፲፫፥፫)
በማለት ከጌታ ልደት ሺህ ዓመት አስቀድሞ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡
በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትም ምክንያት ታላቅ ምሥጢር አለው፤ ምሥጢሩም ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን ላይ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ መከራ ስለ አጸናባቸው ከዚያም ያ መከራ እንደሚቀልላቸው ሽንገል «አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ፤ አዳም የዲያብሎስ ወንድ አገልጋይ ሔዋን የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ፡፡» የሚል የዕዳ ደብዳቤ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን በማስፈረሙና ይህንንም የዕዳ ደብዳቤ አንዱን ቅጂ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ሁለተኛውን ቅጂ በሲኦል አስቀምጦት ስለነበረ ይህን የሰውን ልጅ የዕዳ ደብዳቤ ለመሻር ሲል ጌታችን ለጥምቀቱ ዮርዳኖስን መርጧል፡፡
ጥምቀት የሰው ልጅ የዕዳ ደብዳቤው ተደምስሶለት፥ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጅነትን የሚያገኝበት፥ የጥምቀት ሥርዓት የተጀመረበት ታላቅ ቀን በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ዕለት በየዓመቱ ጥር አሥራ አንድ ቀን እጅግ በታላቅ በሆነ ክብር እና ሥርዓት ታስበዋለች፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖትን ይፋ የአገሪቱ ሃይማኖት በማድረጋቸው ከሚጠቀሱት ሦስት ቀዳሚ አገራት በሁለተኛ ደረጃ ተጠቃሽ ስትሆን ሃይማኖታዊ በዓላትንም እንዲሁ በሐዋርያትና በሐዋርያውያን አባቶች ትውፊት መሠረት የጥምቀት በዓልን ለየት ባለና መጽሐፍ ቅዱስን የሚተረጉም አድርጋ በማክበሩ ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ነች፡፡
የጥምቀት በዓልን ማክበር የተጀመረው በአብርሃና አጽብሃ ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያው ሊቀ ጳጳሳችን በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ዘመነ ጵጵስና በ፫፻፳ ዓ.ም. አካባቢ ሲሆን የአከባበሩ ሥነ ሥርዓት በየዘመናቱ እየሰፋና እየተጠናከረ መጥቶ አሁን በአለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
የቃል ኪዳኑን ታቦት ካህናት ተሸክመው ምዕመናንም በሆታና በእልልታ አጅበው ወደ ወንዝ በመውረድ የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን በዓለ ጥምቀት መታሰቢያ ማክበር የተጀመረው ከ፭፻፴ – ፭፻፵፬ ዓ.ም ድረስ በነገሠው በአፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት እና በማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ዝማሬ ነበር፡፡
ታቦትን አጅቦ ወደ ወንዝ መሄድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሲሆን ይኸውም፦ «የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት።» (ኢያሱ ፫፥፫) በሚለው ትእዛዝ መሠረት ነው፡፡
የጥምቀት በዓል ላይ የቃል ኪዳን ታቦቱን በመያዝ ወደ ወንዝ መሄዱም አንድም እስራኤላውያን በመከራ ከኖሩበት ምድረ ግብጽ ወደ ተስፋይቱ አገር የተሻገሩት የዮርዳኖስ ወንዝን ተሻግረው ሲሆን እኛም ከኃጢአት ሥራ በንስሐ ታጥበን በምግባር ታንጸን በእምነታችን ጸንተን በተስፋ ወደምንጠብቃት ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ለመሰባሰብ እንደምንበቃ በማመን፤ (ኢያሱ ፫፥፲፭-፲፯) አንድም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ መውረዱን፥ ሲጠመቅም አብ ከሰማይ ሆኖ የምወደው ልጄ እርሱ ነው ሲል መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል መውረዱን፣ አንድም በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ጠላታችን ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ የደበቀውን የአዳምን የእዳ ደብዳቤ የቀደደው በመሆኑ፥ (ማቴዎስ ፫፥፲፫-፲፯) አንድም፦ ክርስትና ወደ አገራችን የገባበው ጌታ በዐረገበት በዓመቱ ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ኢትዮጵያዊን ጃንደረባ ሊያጠምቀው ወደ ወንዝ የመውረዱ፤ (ሐ.ሥራ ፰፥፳፮-፴፰) ምሳሌዎች በማድረግ ነው፡፡
ከ፲፩፻፵-፲፩፻፹ ዓ.ም. የነገሠው አጼ ላልይበላ በሁሉም የአገሪቱ ግዛት የሚገኙ አድባራትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ለየብቻቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመሄድ ያደርጉት የነበረውን ክብረ በዓል በማስቀረት በአንድ አካባቢ የሚገኙ አድባራት በአንድነት በመሰባሰብ በአንድ ጥምቀተ ባሕር እዲያከብሩ ትዕዛዝ ሲያስተላልፍ በወቅቱ የነበሩት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስም ጥምቀተ ባህሩን በመዘዋወርና በመባረክ በአንድነት የማክበሩ ሥርዓት እንዲተገበር የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡
ከ፲፪፻፷፪ – ፲፪፻፸፰ ዓ.ም. ድርስ ንጉሥ በነበሩት በአፄ ይኵኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት አቡነ ተክለ ሃይማኖት አሳሳቢነት ይህ የጥምቀት በዓል ሥነ ሥርዓት በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል ሲደረግ ሁሉም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ታቦተ ሕጉ ወደ ጥምቀተ ባሕሩ በሚወርደበት ጊዜና ከጥምቀተ ባሕር ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦና ከቦ እንዲሄድ የሚያዝ የማጠናከሪያ በአዋጅ አስነግረዋል፡፡
በመቀጠልም ከ፲፬፻፲፰- ፲፬፻፶፪ ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት የነበሩትና ጥልቅ የቤተ ክርስቲያን እውቀት የነበራቸውና በመንፈሳዊነታቸውና በደራሲነታቸው የሚታወቁትና ሃይማኖታዊ መጻሐፍትን በመድረስ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያበረከቱት አጼ ዘርዐ ያዕቆብ ታቦተ ሕጉ ከዚያ በፊት ጥር ፲፩ ቀን ወጥቶ በዕለቱ ይመለስ የነበረውን በማሻሻል በከተራ ዕለት ማለትም በጥምቀት ዋዜማ ጥር ፲ ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ጥምቀተ ባህር ወርደው እንዲያድሩ አገሩንም በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ የሚያዝ አዋጅ በማውጣት እንዲተገበር አድርገዋል፡፡
ዛሬም ትውልዱ የአባቶችን ትውፊት በመከተል በጥምቀት ለበዓሉ ድምቀት ካህናት ለዕለቱ የሚስማማ ያሬዳዊ ዜማ፥ ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማሪያን ከዓመት ዓመት የዘመነ መንፈሳዊ ዝግጅትን በማቅረብና በተለይም በዘመናችንም በመዲናችን ወጣቶች የተጀመረውና በመላው አገሪቱ በመስፋፋት ለበዓሉ ታላቅ ድምቀት ያጎናጸፈው የጥምቀተ ባህሩንና የአካባቢውን በተለይም ታቦተ ሕጉ የሚጓዝበትን ጎዳና ማጽዳትና ምንጣፍ ማንጠፍና የመሳሰሉት ዝግጅቶች ታክለውበታል መተግበሩ እጅግ የሚያስደስት ነው፡፡
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓለ ጥምቀት ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት (UNESCO) የዓለም ቅርስ ሆኖ ቢመዘገብም በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ጥቂት የክፋት ልጆች ይህ በዓል በሰላም እንዳይከበር አልፎ አልፎ መታየታቸው ዲያብሎስ ሁሌም እንደማይተኛልን ማሳያ ናቸውና ከምንጊዜውም በበለጥ በወንጌል ታጥቀን በእምነታችን ጠንክረን በመገኘት ሁላችንም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን እምነትና ሥርዓት (ዶግማ እና ቀኖና) ጠብቀን ከውስጥ እና ከውጭ ሆነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን የሚፈታተኑትን በእግዚአብሔር ኃይል በማሸነፍ የትውልድ አደራችንን ለመወጣት ተግተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
የአብ ጸጋ፥ የወልድ ፍቅር፥ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡
All reactions: