የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ለምን በተለያዩ ቀናት ይከበራል?

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ለምን በተለያዩ ቀናት ይከበራል?

ከመ/ር ሸዋንዳኝ አበራ፡፡

የክርስትና ሃይማኖት በራሱ በጌታችን፥ መድኃኒታችንና አምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተመሥርቶ በቅዱሳን ሐዋርያትና አርድእት ስብከት በሁሉም የዓለማችን ማእዘን ከተስፋፋበት ዘመን ጀምሮ ክርስቲያኖች በቅዱሳት መጻሕፍት የተጠቀሱትንና ከአባቶች በትውፊት የተላለፉትን የጌታችንና የቅዱሳን በዓላትን ሲያከብሩ ነበር፡፡ በእኛም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (የኤርትራንም ጨምሮ) የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት ሲከበሩ የቆዩና በመከበርም ላይ ያሉ ሲሆን ከነዚህ በዓላት መሃከልም የልደት በዓል አንዱና ዋናው ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በይሁዳ ከተማ በሆነችው በቤተልሔም መወለዱን ወንጌላውያኑ ቅዱስ ማቴዎስ እና ቅዱስ ሉቃስ የጻፉትን፤ ተወለደበትን ዓመት፥ ወር እና ዕለቱን በተመከተ አባቶቻችን ቅዱሳት መጻሕፍትንና ከቀደሙት የተላለፈላቸውን ትውፊትን በመመርመርና ዕለቱ ታላቅ ዕለት ነውና በክብር እንዲታሰብ በመወሰን ለትውልድ እንዲተላለፍ አድርገዋል፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን ለክርስትና ሃይማኖታችን መነሻ ስፍራ በሆነችው በኢየሩሳሌምና በአካባቢ የነበሩ የጥንት ክርስቲያኖች ያደርጉት እንደነበረው በእስራኤልና በአካባቢዋ ባሉ አገሮችም የተበተኑ ክርስቲያኖች ከአባቶቻቸው እንደተላለፈላቸው ትውፊት የጌታ ኢየሱስን የልደት በዓል በየዓመቱ እንደ አመቺነቱ በግልና በህብረት ተሰባስበው እንደየትውፊታቸው የተወሰኑት ታኅሣሥ ፳፰ ቀን፥ ከፊሎቹ ደግሞ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ያከብሩ ነበር፡፡

የአምላካችን፥ ጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት፥ የጥምቀት፥ የስቅለት፥ የትንሣኤ በዓል አከባበር እና አጽዋማት አጀማመርን በተለያዩ ቀናት የመሆኑን ምክንያት በመርመርና የነበረውን የቀናት ልዩነት ለማሰወገድ በሁሉም ሥፍራ የሚገኙ ክርስቲያኖች በአንድ ቀን አጽዋማትን እንዲጀምሩና በዓላትንም እንዲያከብሩ ለማድረግ በ፫፻፳፭ በኒቅያ የተሰበሰቡት ፫፻፲፰ አባቶች አርዮስን ከስህተት ትምህርቱ ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ አውግዘው ከለዩት በኋላ አያሌ የቀኖና (ሥርዓት) ውሳኔዎችንም አስተላልፈዋል፡፡

፫፻፲፰ቱ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ታሪክን መርምረው በተለያዩ ዕለታት ይፈጸሙ የነበሩ ዐበይት በዓላትና የአጽዋማትም አጀማመር በሁሉም ክርስቲያን ዘንድ በተመሳሳይ ዕለት እንዲጀመሩና እንዲከበሩ በቀኖና ወስነዋል፡፡ በዚሁም መሠረት የልደት በዓል በግብጾች ኪያህክ 29 ቀን በእኛ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን፤ (በተውሳክ በግብጾች ኪያህክ 28 ቀን በእኛ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን) እንዲከበር መወሰናቸውን ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፲፱ ቍጥር ፯፻፳፮ ላይ «ወንድሞቼ ሆይ በበዓለት ቀን ተጠበቁ ይኸውም የጌታችን በዓለ ልደት ነው፡፡ በዕብራውያን በዘጠነኛው ወር በሃያ አምስተኛው ቀን አድርጉ ይኸውም በግብጻውያን በአራተኛው ወር በሃያ ዘጠነኛው ቀን ነው፡፡» ተብሎ ተደንግጓል፡፡

ይህም ማለት በዕብራውያን ከመጀመሪያው ወር ከኒሳን (ሚያዝያ) ወር ስንጀምር ዘጠነኛው ወር በእኛ ታኅሣሥ በዕብራውያን ኪስሌቮ እና
ቴቭት ላይ ይውላል ይህም ማለት የዕብራውያን የዘመን አቆጣጠር በጨረቃና በፀሓይ (Lunisolar) ጥምር ዑደት ላይ የተመሠረተ ሲሆን የእኛ፥ የግብጻውያን፥ የአውሮፓውያኑ የጥንቱ የጁሊያንና የአሁኑ የግሪጎርያን የዘመን አቆጣጠር የተመሠረተው በፀሓይ ዑደት ላይ በመሆኑ የቀናትና የወራት ከፍና ዝቅ የማለት ሁኔታ ይታያል፡፡ የግብጻውያኑ ከእኛ ጋር አንድ ስለሆነ ከመጀመሪያው ወር ከመስከረም ስንጀምር አራተኛው ወር ታኅሣሥ (ኪያህክ)ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የዘንድሮው የልደት በዓል የሚውልበትን ቀን ብናሰላው የእኛ ታኅሣሥ ፳፰ በግብጽ ኪያህክ (Kiahk)28፣ በጥንቱ በጁሊያን አቆጣጠር ዲሴምበር 25 ቀን ሲውል በዕብራውያን ደግሞ ቴቭት (Teveth) 10 ቀን ይውላል፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው ፖለቲካ ወደ ሃይማኖት ሲጠጋ አንድ የነበረችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጀመሪያ በ፬፻፶፩ በክርስቶስ አንድ ባህሪ የእስክንድርያና የአንጾኪያ አብያተ ክርስቲያናት ሲጸኑ የሮሜና የቁስጥንጥንያ አብያተ ክርስቲያናት ሁለት ባህሪ ብለው ተለዩ፡፡ በ፲፻፶፬ ሁለት ባህሪ በማለት ከኦርቶዶክስ ተዋኅዶ የተለዩት ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናትም መንፈስ ቅዱስ ከአብ ይሠርጻል የሚለውን የሐዋርያት ትምህርት በጽናት በያዙት የቁስጥንጥንያ ቤተ ክርስቲያን (አሁን የምሥራቅ ኦርቶዶክስ) እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ከአብም ከወልድም ይሠርጻል የሚል አዲስ ትምህርት ይዘው በመጡት የሮማን ቤተ ክርስቲያን (አሁን የሮማን ካቶሊክ) መካከል ደም መፋሰስ ያስከተለ ልዩነት ተከሰተ፡፡ በመቀጥልም እ.ግ.አ.በ፲፭፻፲፯ በጀርመኑ ማርቲን ሉተር፥ በ፲፭፻፴ዎቹ በእንግሊዝ ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ እና በሌሎችም የቀጠለው የተሃድሶ እንቅስቃሴ በርካቶች ከሦስተኛው አንጃ ማለትም ከሮማን ካቶሊክ እየተለዩ ቢወጡም ሁሉም የሚያከብሩት የአንድ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ሲሆን የብዙዎች ጥያቄ ሁሉም የቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ እሱ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ነው ብለው ካመኑና እሱም አንድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሆነ ለምን በዐራት የተለያዩ ቀኖች የልደት በዓሉ ይከበራል? የሚል ነው፡፡

በዚሁም መሠረት የአምላካችን፥ የጌታችንና የመድኃኒታችንና የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በየዓመቱ ታኅሣሥ ፳፱ በተውሳክ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን (January7) በአጠቃላይ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የኦርየንታል ኦርቶዶክስና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እናከብራለን፡፡ በእኛ ታኅሣሥ ፳፰ በተውሳክ ታኅሣሥ ፳፯ ቀን (January 6) የአርመን ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ እና ወንጌላዊት አብያተ ክርስቲያናት ሲያከብሩ፥ በሌላም በኩል በኢየሩሳሌም የአርመን መንበረ ፓትርያሪክ ሁለቱን የጌታ በዓላት ማለትም ልደትንና ጥምቀትን ጥር ፲፩ በተውሳክ ጥር ፲ ቀን (January 19) አንድ ላይ ያከብራሉ፡፡ ቀሪዎቹ የምእራብ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም ሮማን ካቶሊክ፥ ሉትራን፥ አንግሊካንና ሁሉም ፕሮቴስታንቶች December 25 (ታኅሣሥ ፲፮ በተውሳክ ታኅሣሥ ፲፭ ቀን) ያከብራሉ፡፡

የጥንት ባለብዙ አማልክት ሮማውያን ሳቱርናሊያ (The Roman Festival of Saturnalia) የሚሉትን በዓል ከDecember 17 እስከ 23 ድረስ የአምልኮ በዓል የነበራቸው ሲሆን ኋላ ላይ በ274 የሮማው ገዢ አውሬሊያን (Roman emperor Aurelian) ፀሐይ እሑድ ዲሴምበር 25 ቀን ተወለደች በማለት በየዓመቱ ዲሴምበር 25 Dies Natalis Solis Invicti (birthday of the unconquered sun) በማለት እና በየሳምንቱ እሑድ Dies Solis- Sunedai- Sunday ብሔራዊ በዓላቶቻቸው እንዲሆኑ ወሰነ፡፡
(ከሳምንቱ ቀናት የፀሐይ የልደት ቀን ነው ያለትን እሑድ የፀሐይ ቀን (Sunday) በማለት ሰይመዋል፡፡

ምንም እንኳን ለክርስቶስና በስሙ ለተጠሩት ክርስቲያኖች ጠላት የሆኑት አሕዛብ የሮማ ነገሥታት ክርስትናን ለማጥፋት ይረዳናል በማለት የአሕዛብ በዓላት ቀናቶችን በማንሸራተት በክርስቲያኖች በዓል ቀን ላይ እንዲውሉ በማድረግ ለጣኦቶቻቸው እንዲሰግዱ እና እንዲያመልኳቸው አስገዳጅ ሕግ ቢደነግጉም ክርስቲያኖች ይበልጥ ተጠናክረው ክርስትና አሳዳጆች ቤት ድረስ በመግባት አሸናፊነቱን ሊያረጋግጥ ችሏል፡፡

አሕዛብ የሮማ ንጉሠ ነገሥት አውሬሊያን (Aurelian) ዲሴምበር 25 ቀንን የማይሸነፈው ፀሐይ የልደት ቀን (Dies Natalis Solis Invicti -birthday of the unconquered sun) ብሎ ዕለቱ እንዲከበር ከመወሰኑ ሁለት መቶ ዓመት ቀደም በማለት በኢየሩሳሌም፥ በመካከለኛው ምሥራቅና በቅርብ ምሥራቅ አካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በዕብራውያን አቆጣጠር ኒሳን (Nisan)14** ቀን፥ በጁሊያን አቆጣጠር March 25 ቀን፥ በግብፅ (ኮፕት) አቆጣጠር ባራምሃት (Baramhat) 29 ቀን፥ በእኛ አቆጣጠር መጋቢት ፳፱ ቀን ሊቀ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ያበሠረበት ቀን፤ እንዲሁም በዕብራውያን ዘጠነኛው ወር ሃያ አምስተኛው ቀን ማለትም ቴቭስ (Teveth)25፥ በጁሊያን አቆጣጠር December 25 በግብጽ (ቅብጥ) አቆጣጠር ኪያህክ (Kiahk) 29 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ታኅሣሥ ፳፱ (በግብጽና በእኛ አቆጣጠር በተውሳክ ኪያህክ 28፥ ታኅሣሥ ፳፰) የአምላካችንን የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ያከብሩ ነበር፡፡ (**የጁሊያን፥ የግሪጎሪያን፥ የግብፅ እና የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠሮች መሬት በፀሐይ ዙሪያ በምታደርገው ዑደት (solar) ተመስርቶ የተቀመረ ሲሆን አንድ ዓመት 365 1/4 ቀናት ያሉት በመሆኑ የአቆጣጠር ዘዴ መለየየት እንጂ በሌላው ተመሳሳይ ሲሆኑ የዕብራውያኑ በጨረቃና ፀሐይ (Lunisolar) ዑደትን መሠረት ያደረገ ቀመር በመሆኑ አንድ ዓመት 354 ቀናት በተውሳክ 384 ቀናት ያሉት እና አንድ ዕለት ከሌሎቹ የዘመን አቆጣጠር ጋር የሚገጥመው በ19 ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ የዕብራውያን ቀመር የክርስትና በዓላትን ለማክበር አስቸጋሪ ነው፡፡)

ወደ መነሻ ርዕሴ ልመለስና ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል እንዳያከብሩ በዚያን ዕለት የክርስቶስን ሳይሆን አምላካችን የሚሏትን የፀሐይን ልደት ከአሕዛብ ጋር በኃይል እንዲያከብሩ ቢደረግም ጊዜው ሲደርስ የመጀመሪያው ክርስቲያን የሮማው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ (Emperor Constantine) የአምላካችን የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ በጁሊያን አቆጣጠር ዲሴምበር (December) 25 ቀን 336 በይፋ እንዲከበር በማድረግ የልደት በዓል ወደ ጥንቱ ዕለት መመለሱን የታሪክ መዛግብቶች ያረጋግጣሉ፡፡ ይኸውም በግብጥ ኪያህክ (Kiahk) 29 በኢትዮጵያ ታኅሣሥ ፳፱
ቀን ነው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው አሕዛቡ ንጉሠ ነገሥት አውሬሊያን (Emperor Aurelian) በ274 ጀምሮ በኃይል የአሕዛብ በዓል በጌታ የልደት በዓል ቀን እንዲከበር ቢያደርግም የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ከስድሳ ሁለት ዓመት በኋላ በ336 ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ (Emperor Constantine) በይፋ ወደ ቀደመ ዕለቱ እንዲመለስ አድርጎ በዚህ መልኩ የአብያተ ክርስቲያናት መከፋፈል ሳያፋልሰው እስከ 1582 (በእኛ ፲፭፻፸፭ ዓ.ም.) ድረስ አቆጣጠሩ ቢለያይም በአንድ ቀን ከአርሜንያ ሐዋርያዊት ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በስተቀር በሁ ክፍሎች በሙሉ የልደት በዓል በአንድ ቀን ማለትም በጁሊያን ዲሴምበር 25፥ በግብጥ ኪያህክ 29 በተውሳክ 28፥ በኢትዮጵያ ታኅሣሥ ፳፱ በተውሳክ ፳፰ ሲከበር በአንድነት ቆይቷል፡፡

የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጎርጎሪዮስ አሥራ ሦስተኛ (Pope Gregory XIII) የሚጠቀሙበት የጁሊያን ዘመን አቆጣጠር የአሥር ቀናት ስህተት አለው መቀነስ አለበት በማለትና ስህተቱን ለማስተካከል በሚል
4 October 1582 በማግስቱ 5 መሆኑ ቀርቶ 15 October 1582 ተብሎ እንዲቆጥረ በማዘዙና በዚሁም መሠረት አሁን ምእራባውያን የሚጠቀሙበት የጎርጎርያዊያን አቆጣጠር በሥራ ላይ ስለዋለ ይህን ተከትሎ እ.ግ.አ ከ1582 (እ.ኢ.አ. ፲፭፻፸፭ ዓ.ም.) ጀምሮ ለአንድ ሺህ አምስት መቶ ዓመት ይከበርበት ከነበረው ዕለት አሥር ቀን ቀደም በማለት መጀመሪያ የካቶሊክ ክርስቲያን እምነት ተከታይ አገራት ጣሊያን፥ እስፓኝ፥ ፈረንሳይ፥ ፖርቱጋል ሲያከብሩት በመቀጠልም የፕሮቴስታንት ክርስቲያን እምነት ተከታይ አገራት እንደ ጀርመን፥ ስዊዲን፥ ስዊዘርላንድ፥ ታላቋ ብሪታኒያ፥ አሜሪካ የመሳሰሉት አገራት ከሁለት መቶ ዓመታት በኋላ በመቀላቀል ከጥንተ ልደት አሥር ቀን ቀደም በማለት በአዲሱ የጎርጎርዮስ ቀመር ዲሴምበር 25 ቀን በጥንት የጣኦት እምነት ሥርዓራቸው በማጀብ ሲያከብሩ የምሥራቅ እና የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት በአብዛኛው ምሥራቅ አውሮፓ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በጥንቱ በጁሊዮስ አቆጣጠር ዲሴምበር 25፥ ግብጦች (ኮፕት) ኪያህክ 29 በተውሳክ 28፥ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ታኅሣሥ ፳፱ በተውሳክ ፳፰ የጌታን የልደት በዓል አንድ ቀን እናከብራለን፡፡ (ይህ ቀን በአዲሱ የጎርጎርዮስ ቀመር መሠረት ጃኑዋሪ 7 ላይ ይሆናል፡፡)

በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ያለን ክርስቲያኖች እንደ አብያተ ክርስቲያናችን ትውፊት በአራት የተለያዩ ቀናት የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል እናከብራለን፡፡ ዋናው ቁም ነገር የልደቱ ቀን አከባበሩ ላይ ሳይሆን አከባበሩን ከአሕዛብ ቅራቅንቦ የጸዳ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?» (፪ኛ ቆሮንቶስ ፮፥፲፬-፲፭)ሁሉም ነገር በልክ እና እንደ አገራችንና እንደ አባቶች ትውፊት መሆን ይኖርበታል፤ ጌታችን በመዋዕለ ስብከቱ «የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር፤» (ማቴዎስ ፳፪፥፳፩)በማለት እንዳስተማረው ለእግዚአብሔር ቤት፥ በሃይማኖታዊ በዓላት፥ ለአምልኮ የሚሆኑትን ከአሕዛብና ከጣኦት ሥርዓቶች ወረርሽኝ እናጽዳቸው፡፡

የክርስቲያን በዓላት አከባበር መሠረታችን መጽሐፍ ቅዱስ ነውና በወንጌል እንደተጻፈው… «ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች መድኃኒት እርሱም የጌቶች ጌታ የሆነ ክርስቶስ ተወለደልን፤» (ሉቃስ ፪፥፲-፲፩) እያልን በንጹህ ልብ ሆነን የቤተልሔም አካባቢ እረኞች ከሰማይ ሠራዊትና ከቅዱሳን መልአክት ጋር – «ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ፤» (ሉቃስ ፪፥፲፬) እያሉ በዝማሬ ደስታቸውን እንደገለጹ እኛም እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታችን ሊያድነን መወለዱን፥ በዮርዳኖስ መጠመቁን፥ በገዳመ ቆሮንዮስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት መጾሙንና ዲያብሎስን ድል ማድረጉን፥ ወንጌልን ማስተማሩን፥ ድውያንን መፈወሱን፥ ሙታንን ማስነሳቱን፥ ታላላቅ ተአምራትን መሥራቱን፥ በቀራኒዮ ቤዛ መሆኑን፥ በሦስተኛው ቀን ሞትንና ሙስናን አሸንፎ መነሣቱን፥ በአርባኛውም ቀን ወደ አብ ወደ ሰማይ ማረጉንና በሙታንና በሕያዋን ላይ ለመፍረድ በኃይል ባለው ግርማ ዳግም እንደሚመጣ አምነን በትጋት ቃሉን በመተግበር በስም ብቻ ሳይሆን በምግባርም ክርስቲያን መሆናችንን ማሳየትና እንደ ቃሉ መኖር ላይ በማተኮር በዓላቱን እናክብር፤ ሐዋርያው ያዕቆብ «ሥራ የሌለው እምነት በራሱ የሞተ ነው፡፡» (ያዕቆብ ፪፥፲፯) እንዳለው እንዳይሆንብን የቀደሙ ቅዱሳንን ፈለግ ተከትለን እንደ ስማችን ክርስቲያን በመሆን የእምነት፥ የተግባር፥ የሰላም፥ የፍቅርና ይቅር ባይ እንሁን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

Close Menu