የወላዲተ አምላክ ዜና ዕረፍት ወፍልሰት (ዕርገት)
በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት መሠረት ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም በዚህ የእንግድነት ዓለም በሕይወተ ሥጋ ስልሳ አራት ዓመታትያህል ቆይታ በክብር አርፋለች። ቅዱሳት ሐዋርያትም በፈቃደ እግዚአብሔር ከያሉበት መጥተው በኢየሩሳሌም ተሰብስበው የፈጣሪያቸውን እናት ድንግል ማርያምን በጸሎትና በማዕጠንት አክብረው ገንዘው ጥልቅ በሆነ ኃዘን በጌቴሲማኒ ቀብረዋታል።
ቅዱሳን ሐዋርያት እመቤታችንን በክብር ለመሸኘት በጉዞ ላይ ሳሉ አይሁድ “ኑና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥል” ብለው በክፋት ተነሱ። በተለይም ደግሞ በእመቤታችን ላይ በክፋትና በተንኮል ከተነሳሱት ከእኒህ አይሁድ መካከል ታውፋንያ የተባለው አይሁዳዊ አማናዊት ታቦተ እግዚአብሔር የሆነችው የድንግል ማርያም ቅዱስ ሥጋ ያረፈበትን አልጋ ለመያዝ እጁን በድፍረት ዘረጋ። በዚህን ጊዜ ልዑለ ባሕረይ እግዚአብሔር የአሚናዳብ ልጅ ዖዛ እጁን በታቦተ ጽዮን ላይ በድፍረት በመዘርጋቱ ምክንያት ተቆጥቶ እንደቀጣው ሁሉ (2ኝ፡ሳሙ. 6፣6፤ 1ኛ ዜና. መዋ. 13፣7-10)፤ ታውፋንያም በሰማያዊው መልአክ ሰይፍ እጆቹን ተቀጥቷል።
ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም ታላቁ ሐዋርያ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ልሄድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና” (ፊል. 1፣23) ብሎ እንደተናገረው በልጇ በወዳጇ በኢየሱስ ክርስቶስ ፈቃድ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዘለዓለማዊ የክርስቶስ መንግሥት ተሸጋግራለች። በዚህን ጊዜ እመቤታችን በምድር ካለችው ቤተክርስቲያን ጋር የሰማያዊቷ ቤተክርስቲያንም አክሊል በመሆኗ የሰማይ ሠራዊት በደስታ በዝማሬ ፍጹም አክብረው ተቀብለዋታል።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የምታክብረው ይህ የድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍት “አስተርእዮ” በመባል ይታወቃል።
ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የምታክብረውን በዓለ ዕርገት / “ፍልሰታ” በማለት ይገልጹታል።
ይህንን ዓቢይ ምስጢር አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ፤አንተና የመቅደስህ ታቦት” (መዝ. 131፣8)፤ እንዲሁም በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፤ (መዝ. 44፣9) ሲል የተናገረው ቃለ ትንቢት በንጽሐ ሥጋ፣ በንጽሐ ነፍስ፣ በንጽሐ ልቡና የጸናች የቅድስት ድንግል እመቤታችንን ዕረፍትና ትንሳኤ እንዲሁም ፍልሰት (ዕርገት) በምስጢር ከማሳየቱም ሌላ ወላዲተ አምላክ በልጇ በወዳጇ በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት በክብር መኖሯንም በግልጽ ያስረዳል፣ ያስገነዝባል።
በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ። (ራዕ. 11፣19)
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃዋና ልመናዋ ዘወትር አይለየን … አሜን።
ምንጭ፦ “ወላዲተ አምላክ በነገረ ድኅነት” በመ. አንዱዓለም ዳግማዊ