የልብ ንጽሕና

የልብ ንጽሕና

ፍጹም ንስሐ ኃጢአትን መጥላት፣ ልብንም ፈጽሞ ከኃጢአት ማጥራት ሲሆን የልብ ንጽሕና ደግሞ ከፍጹም የንስሐ ምልክቶች አንዱ ነው።

የልብ ንጽሕና፦ ፍጹም ንስሐ ማለትም ሰው ኃጢአትን ጨርሶ መጥላቱ እንዴት ሊታወቅ ይችላል? ቀጥሎ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን።

1.ከኃጢአት መንጻት

. ሰው አእምሮውን በመፈተን የሚያስጨንቁትን ከባድ ኃጢአቶች በመተውና ዳግመኛም ወደ እነርሱ ባለመመለሱ በንስሐ የሚኖር ሊመስለው ይችላል። ለምሳሌ ዳግመኛ ዝሙት አልሠራ፣ አልሰርቀ፣ ወይም አላታለለ ወይም ደግሞ አልሰከረ ይሆናል። በዚህ ደረጃ ያሉትን ኃጢአቶች አልፈጸመ ይሆናል። በዚህ የተነሳ አእምሮው እረፍት ስለሚኖረው ንስሐ የገባ ሊመስለው ይችላል። ለዚህ ምክንያቱ እርሱ ያተኮረባቸው ዓበይት ኃጢአቶች ጥቃቅኑንና ሊያስተውላቸው ያልቻለውን ኃጢአቶች ስለሚሸፍንበት ነው። ምናልባትም ራሱን ተነሳሒ አድርጎ በሚቆጥርበት ጊዜ በብዙ ሊያስተውላቸው ባልቻላቸው ወይም ኃጢአቶች ናቸው ብሎ ባላሰባቸው ብዙ ኃጢአቶች ተዘፍቆ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ስለራሱ በመናገር፣ በውዳሴ ከንቱ በመደሰት፣ ራስን በማሞካሸት፣ በራስ ፍላጎት በመጓዝ ለግትርነት በሚያበቁ ሃሳቦች ላይ በመመርኮዝ፤ የተወሰኑ ጸሎቶችን ንቆ በመተውና ለመንፈሳዊ ንባቦች ግድየለሽ በመሆን፤ ምናልባትም ስድብን ባለመታገስ፣ ሰንበትን ባለማክበር፣ ይህን ሁሉ በማድረጉ ራሱን አይወቅስም። በዚህ የተነሳ ራሱን ሊወቅስ ከምችልበት ደረጃ አልደረሰምና። ታዲያ ይህን ሰው በእውነተኛ ንስሐ ውስጥ እየኖረ ነው ማለት እንችላለን።

ስለዚህ ይህ ሰው የንስሐ እርምጃውን ማጠናከር አለበት። በናቃቸው ኃጢአቶች ሁሉ ንስሐ መግባት አለበት። በንስሐ ይኖራል ለማለት የሚቻለውም በእርሱ ሃሳብ ጥቃቅን ከሚመስሉት ጀምሮ ኃጢአትን ሁሉ ሲተው ነውና ከልቦናው ፈጽሞ ያጠፋው እንደሆነ ነው። በዚህ ጊዜም በንስሐ አንድ እርምጃ በመጨመሩ በመንፈሳዊ ብስለት እያደገ ነው ሊባል ይችላል። አእምሮውም ምንም ነገር ሳይንቅ ለሁሉ ኃጢአት ትኩረት መስጠት ስለሚጀምር በንስሐ ሕይወት እየኖረ ነው ለማለት ይቻላል።

ለ. ምናልባትም ሰይጣን ለተወሰነ ጊዜ ከእርሱ በመለየቱ ኃጢአትን ላይሰራ ይችላል። ሰይጣን ለክፉ ሥራው ጠቢብ ነው። መቼ፣ እንዴትና በምን ኃጢአት ሰውን እንደሚጥል ያውቃልና ሰውየው በራሱ በመተማመን ከኃጢአት መጠንቀቁን እስኪተውና ስለሕይወቱ ግድየለሽ እስኪሆን በትዕግሥት ይጠብቀዋል። በሕይወቱ በደከመ ጊዜ በቀላሉ ሊጥለው እንደምሚችል ስለሚያውቅ ያኔ ይመጣበታል። ይህ ሰይጣን ከሰውየው ገለል ብሎ የቆየበት ጊዜ ኃጢአትን የማሸነፊያ ጊዜ አይደለም ጦርነት የሌለበት ጊዜ ነው። ከመንፈሳዊ ጦርነት የማረፊያ ጊዜ እንጂ የድል ወይም የንጽሕና ጊዜ አይደለም።

ምናልባት በኃጢአት ያልወደቅንበት ጊዜ ቢኖር ከኃጢአት ፈጽመን ስለነጻን አይደለም ነገር ግን ሰይጣን ስላልተዋጋን ወይም ደግሞ ኃጢአት ለመሥራት የተመቻቸ ሁኔታ ስለሌለ ነው።

ሰይጣን በተወሰነ ጊዜ ላይዋጋን ይችላል። የእኛን እረፍት ሽቶ ሳይሆን እኛን የሚጥልበት ሌላ ወጥመድ እያዘጋጀ ስለሆነ ነው። ምናልባትም ከኃጢአት የነጻንና የተቀደስን እንድንሆን የሚያሳስብ ሰይጣን ወደኛ ሊመጣና ንጹሐን መሆናችንን ያለፈው በደል ሁሉ ከእኛ መወገዱን ሊያበስረን ይችላል። በዚህ ጊዜ ምንም እንኳ በኅሊናችን የአሸናፊነት ስሜት ቢሰማን ደካማ መሆናችንንና በሥጋ የምንኖር እስከሆንን ድረስ ልንወድቅ የምንችል እንደሆንን መዘንጋት የለብንም። ስለዚህ ከንጽሕና ደረጃ ደርሻለሁና ዳግመኛ አልወድቅም ማለት የለብንም። ይልቅ ግን እንደ ዳዊት “እግዚአብሔር ከኛ ጋር ባይሆን … ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር” ማለት ይገባናል። መዝሙር 123፡2-3። የሚጠብቀንን እግዚአብሔርንም ልናመሰግን ይገባል።

ሐ. ምናልባትም እግዚአብሔር ከኃጢአት ሸክም እንድናርፍና ነፍሳችንንም ተስፋ ከመቁረጥ ሊያድናት አስቦ የእረፍት ጊዜ ሰጥቶን ይሆናል። ያለማቋረጥ በኃጢአት ተዘፍቆ መቆየት ከተስፋ መቁረጥ ሊያደርስ ስለሚችል እግዚአብሔር በጸጋው ከልሎ በቸርነቱ ጠብቆ ከኃጢአት ሊያሳርፈን ይችላል። ይህም ንጹሐን ስለሆንን አይደለም።

መ. ምናልባት ብዙ ጸሎቶች ስለእኛ ቅድመ እግዚአብሔር በመድረሳቸው ሰላም አግኘተን ይሆናል። ቅዱሳን ስለጸለዩልን ጸሎት ወይም ወዳጆቻችን ስላቀረቡት ልመና ከኃአጢአት ሸክማችን ልናርፍ እንችላለን። ይህም ከንጽሕናችን የተነሳ አለመሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ይገባል። ይህ ጊዜም ከሰይጣን የማንዋጋበት በሰላምና በዝምታ የምናሳልፈው ጊዜ ነው እንጂ ከንጽሕና ደረጃ የደረስንበት አይደለም።

በሕጻናት፣ በዕድሜና በመንፈስ ትልቅ ዐዋቂ በሆኑ ሰዎች ንጽሕና መካከል ልዩነት አለ። ሕጻናት ወደዚህ መንፈሳዊ ጦርነት አልገቡም፣ አልተፈተኑምም። ትላልቆቹ ግን በጦርነት ውስጥ ናቸው። ተዋግተውም አልፈዋል። የኃጢአትንም ኃይል ተቃውመናልና የድል አክሊል ያገኛሉ። ሕጻናት ግን እንደነዚህ አይደሉም ገና ናቸው።

ሕጻናት ከማያውቁት ከዚህ ውጊያ በኋላ የሕጻናትን ንጽሕና ገንዘብ ያደረጉ ሰዎች ግን እጅግ የሚደነቁ ናቸው። ይህ የልብ ንጽሕና በቀላሉ የሚደረስበት አይደለም። ከዚህ ደረጃ የሚደርሱት ብዙ ውጊያዎችንና ፈተናዎችን በድል አልፈው ነው። የልብ ንጽሕና እጅግ ከፍተኛ የሆነ የንጽሕና ደረጃ ነው። ስለዚህ አንድ ሰው በተወሰነ ኃጢአት ተፈትኖ ራሱን ከዚህ ኃጢአት ቢያነጻ ይህ ፍጹም ንጽሕና ነው ለማለት አይቻልም።

ፍጹም ንጽሕና ከኃጢአት ሁሉ መንጻት ነው። ይህም በማንኛውም ጊዜና መንገድ ከሚመጣ ከማንኛውም ኃጢአት መንጻት ማለት ነው። ከተወሰኑ ኃጢአቶች ብቻ መንጻት ፍጹም ንጽሕና አይባልም። በመቅደስ ከቀራቹ ጋር ቆሞ ይጸልይ የነበረው ፈሪሳዊ ቀማኛ፣ አመጸኛና አመንዝራ ባለ መሆኑ በሳምንትም ሁለት ቀን በመጾሙ ንጹሕ እንደሆነ አስቦ ነበር። ሉቃስ 18፡11-12። ነገር ገን ከኩራትና በሌሎች ከመፍረድ ራስንም ከፍ ከፍ ከማድረግና ከመመጻደቅ ራሱንም አላነጻም ነበር። ስለዚህ ከተወስኑ ኃጢአቶች በነጻን ጊዜ ከንጽሕና የደረስን ሊመስለን አይገባም። ለንጽሕናችን መለኪያ የሚሆነው ከኃጢአት ወገን የትኛውም ቢሆን በላያችን ሥልጣን የሌለው እንደሆነ ብቻ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውን እንመልከት፦ “ከእናንተ ስለኃጢአት የሚወቅሰኝ ማነው?” ማለቱ ስለየትኛውም ኃጢአት ቢሆን ማለቱ ነው። ዮሐንስ 8፡46። በሌላ ስፍራ ደግሞ “የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና በእኔ ላይም አንዳች አይኖረውም” በማለት ፍጹም ንጹሕ የባሕርይ አምላክ መሆኑን ተናግሯል። ዮሐንስ 14፡30። እንግዲህ ከሰው ወገን ማን ከዚህ ደረጃ ደርሷል?

እውነተኛው ንጽሕና ኃጢአትን ፈጽሞ ከመጥላት ይጀምራል። ይህም ማለት መልካሙንና ክፉውን ለመለየት የሚቻልበት የፍጹምነት ደረጃ መጀመርያ ነው። ዕብ 5፡14። ንጽሕና ከልብ የሚመነጭ እንጂ ከውጭ የሚመጣ አፍአዊ አይደለም። ውስጡ ያልጸዳ ውጭው ግን አምሮ የታየ ሁሉ ንጹሕ ነው ሊባል አይችልም። ማቴዎስ 23፡25-31። ይህም ንጽሕና ማለት የውጫዊ አካላችን ሳይሆን የልቡናችን ከኃጢአት ንጹሕ መሆን ነው ማለት ነው። በመጽሐፍም “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና” በማለት ቀዳሚውና ዋነኛው የልብ ንጽሕና መሆኑ ተነግሯል። ማቴውስ 12፡34። ስለዚህ ከውጫዊ ንጽሕና በተጨማሪ ልናተኩርበት የሚገባው የልብ ንጽሕና ነው። መልካሙና ንጹሑ ሥራ የሚመነጨው መልካም ሃሳብ ከሚገኝበት ንጹሕ ልብ ነው። ይህ ደግሞ ንጹሕ ዓላማና ንጹሕ የአሰራር ዘዴ እስካለ ድረስ ነው። ይህ የልብን ንጽሕናም ወደ ፍጹም ንጽሕና ሳይሆን ከኃጢአት ንጹሕ ወደመሆን ያደርሳል።

የልብ ንጽሕና (2)

  1. ንጽሕናን መፈተን

ሰው ንጹሕ ሊባል የሚችለው እጅግ ከባድ የሆነ የኃጢአት ፈተና ቢደርስበት እንኳ ሳይናወጥ የኃጢአትን ኃይል የተቋቋመ እንደሆነ ነው። በኃጢአት አለመውደቅ ብቻ ሳይሆን በዚህ የኃጢአት ኃይል የማይንገዳገድ ጽኑ የሆነ እንደሆነም ነው። የሰው የልብ ንጽሕናም የሚፈተነው በከባድና በአስፈሪ የኃጢአት ጦርነት ነው። ሰይጣን ታላላቆችን እንኳ ሳይቀር የሚያዋርድ ስለሆነ እኔ ጠንካራ ነኝ ከማለት ይልቅ ደካማነትን ማወቅና እኔም ንጹሕ አይደለሁም ማለት ይገባል። ምሳሌ 7፡26

ከባዱ ውጊያ ሰውን ያለእረፍትና ያለፋታ ይፈትነዋል። አንዴ በመራራው ውጊያ ሊያሸንፍ ይችላል። ውጊያው እየቀጠለ በሄደ ቁጥር እየደከመ ሄዶ ከመሸነፍና ከመውደቅ ሊደርስ ይችላል። ለምሳሌ እንደ ሶምሶን ። መሳ 16፡16-17። ይህ ከባድ ጦርነት መልኩን እየለዋወጠ ሰውን ሊፈትን ይችላል። የሰውየውን ደካማ ጎን በማጥናትና የውጊያ ስልቱን በመቀየር ሊረታውም ይችላል።

ታዲያ ንጹሕ ልብ አለው የሚባለው እንዴት ያለው ሰው ነው? ሰው ንጹሕ ልብ አለው የሚባለው በሃሳብ፣ በስሜት፣ በመናገር፣ በአካል እንዲሁም በማድረግ ከሚሠሩ ኃጢአቶች ሁሉ ልቡናውን ያነጻ እንደሆነ ነው።ንጹሕ የሚባለው እግዚአብሔር በሰጠው ጸጋ ታግዞ እነዚህን ሁሉ ኃጢአቶች ተዋግቶ ያሸነፈ ሰው ነው። ይህ ንጽሕና የመጨረሻው የንስሐ ጉዞ ምዕራፍ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ለመተያየት የሚያበቃ ጸጋ ይገኝበታልና መድኃኒታችን “ ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና።” በማለት እንዳስተማረን። ማቴዎስ 5፡8።

  1. ከኃጢአት ሃሳብና ሕልም መንጻት

ከኃጢአት ከመንጻት በተጨማሪ ከሃሳብና ከግምት፣ ከመላ ምትም መንጻት ይገባል። አንድ ቅዱስ “ የአንተነትህን እውነተኛ ገጽታ የሚገልጸው ውጫዊ ስራህ ብቻ ሳይሆን የምታስበው ሃሳብና የሚኖርህ መላምታዊ (ግምታዊ) አስተያየትም ጭምር ነው” ብሏል። የተለያዩ ሦስት ሰዎች በጨለማ ውስጥ ያዩትን ሰው “ሌባ ነው፣ ወንበዴ ነው፣ ማንም ሳያየው ለመጸለይ የመጣ ክርስቲያን ነው።” ቢሉት፤ የሦስቱም ሃሳብና መላምት ከልባቸው የመነጨ ነው። ጌታችንም “መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካምንም ያወጣል፣ ክፊም ሰው ከልቡ ክፉ መዝገብ ክፉውን ያወጣል።” በማለት ልብ የመልካምም የክፉም ሃሳብና ግምት ምንጭ መሆኑን ተናግሯል። ሉቃስ 6፡45።

ስለዚህ ሃሳባችን ክፉ ከሆነ ልባችን ገና አልነጻም፤ ልቡ ንጹሕ የሆነ ሰው ምን ግዜም  ቢሆን የሚያስበው መልካም ነገርን ነውና። ሰዎች ስለሠሩት ክፉ ሥራም ክፉ አያስብም በንጹሕ ልብ ይቅርታ ያደርግላቸዋል እንጂ።ህፉ ሃሳብንም አይቀበልም።

ሰዎች ስለንጽሕናቸው የሚጨነቁ፣ ስለሃሳባቸው ንጽሕና የሚጠነቀቁ ሊሁኑ ይችላሉ። ነገር ግን በሕልማቸው ኃጢአት ሊሠሩ ወይም የቀደመ ኃጢአታቸውን ያስታውሱ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች የቀደመ ኃጢአታቸውን ማስታወስና ማሰብ የለባቸውም ከዚያ ሃሳብ መንጻት አለባቸው። ኃጢአትን ከማለም ነጻ የሚሆኑበት የተወሰነ ጊዜም ያስፈልጋቸዋል።ይህ ጊዜም የቀድሞው የኃጢአት ትዝታ ከኅሊናቸው እንዲጠፋ ይረዳቸዋል። በዚህ ምትክም አእምሮአቸው ንጹሑንና ለንስሐ ሕይወት የሚስማማውን ሃሳብ እንዲመዘግብ ይሆናል፤ ያኔ የሚያልመው ነገርም ንጹሕ ይሆናል።

  1. ከማያስፈልጉ ነገሮች መንጻት

ከማያስፈልጉ ነገሮች መንጻት ማለት ከሚያልፉና ጥቅም ከሌላቸው ነገሮች መንጻት ማለት ነው።

እነዚህ የሚያልፉና የማይጠቅሙ ነገሮች ወይ የሚሠሩ፣ የሚነበቡ፣ የሚታዩ፣ የሚደመጡ ወዘተ ሊሁኑ ይችላሉ። እነዚህ ሃጢአትም ጽድቅም አይደሉም። እነዚህን ነገሮች የሚያዘውትር ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖርበትን፣ ራሱን የሚቀድስበትን፣ ንስሐ የሚገባብትን ጊዜ ያባክናል። ከዚህም የተነሳ መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ለመሥራት ጊዜ ያጣል። እነዚህ የማያስፈጉና የማይጠቅሙ ነገሮች ለመንፈሳዊ ሥራ እንቅፋት ይሆናሉና ራሳችንን ከእነርሱ ማላቀቅ እና ማንጻት ያስፈልጋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ለዘላለም ነው። በማለት ስለተናገረ የምናየው ነገር የማይጎዳ ግን የሚያልፍ ነውና ጊዜያችንን ለሚጠቅምና ዘለዓለማዊ ለሆነው መንፈሳዊ ሥራ ማዋል ይገባናል።2 ቆሮ 4፡18። የሚታየውን ጊዜያዊና ሃላፊ የሆነውን ነገር የማይመለከት ሰው እንደ ዳዊት፦ “ለኔስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” ይላል። መዝሙር 72፡28። ፍጹም የሆነውን ወደ እግዚአብሔር መቅረብም ያለ ንጹሕ ልብ መቅረብ አይቻልምና የልብ ንጽሕና እጅግ አስፈላጊ ነው።

ከኃጢአት መንጻት ቅድስና እንጂ የልብ ንጽሕና አይደለም። ከኃጢአት መንጻት ከኃጢአት መለየት ኃጢአትን አለመሥራት ነው። የልብ ንጽሐን ግን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ሃሳብ፣ በሥራም ያለማቋረጥ፡ከእግዚአብሔር ጋር በሚስማማ ሕይወት መኖር ነው።

በዓለም ውስጥ ብዙ የሚታዩና የሚሰሙ ነገር ግን የማይጠቅሙ ነገሮች አሉ። ለነርሱ ትኩረት አለመስጠትና እራስንም ከእነርሱ ማንጻት ይገባል። ዓይኖቻችን የሚያዩት ነገር የሚያዩት ነገር ባገኙ ጊዜ ትኩረታችንን ለዚያ ነገር መስጠት አይገባም። ዓይንን ብቻ ሳይሆን ሕዋሳቶቻችንን ሁሉ፤ ሕዋሳት ሁሉ የሃሳብ ምንጮች ሊሆኑ ይችላሉና። ያን ጊዜ በአእምሮችን የተቀረጸውን ሃሳብ ስፍራ ሳንሰጠውና ሳናተኩርበት ያሳለፍነው እንደሆነ ይህ የልብ ንጽሕና ቅድመ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ወይም ደግሞ አእምሮአችንን ያስገዛንለትና ጊዜ የሰጠነው እንደሆን የኃጢአትን ፍላጎት በውስጣችን ሊፈጥር ይችላል። ይህ ሃሳብ በእግዚአብሔር ሰው ልቦና ውስጥ የኃጢአትን ፍላጎት ሳይሆን በልቡናው ውስጥ ለኃጢአትና ለዓለም ነገር በመሞት ላይ እንዲያተኩር የሚያነሣሣ ሃስብ ሊፈጥርበት ይችላል።

እነዚህ የሚያልፉና የሚጠፉ ሃሳቦች ሌላው ቢቀር ጊዜ ያባክናሉ። ጊዜ የሕይወት አንድ ክፍል ነው። እግዚአብሔርም ጊዜ የሰጠን እንድንጠቀምበት፣ ነፍሳችንን እንድናድንበት፣ ሃሳባችንና ልቡናችንን እንድናነጻበት፣ ስሜታችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር እንድናስገዛበት ነው እንጂ እንድናበክነው ስላይደለ በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል።

አእምሮን ጥቅም በሌለው ነገውር ማስጨነቅ የእግዚአብሔር ፍቅር በውስጥ የሌለ ነገር የሚገልጥ ነው። ስለዚህ በልቦናችንና በአእምሮአችን ከእግዚአብሔር አስበልጠን ስፍራ የምንሰጠውና የምናተኩርበት ነገር መኖር የለበትም።

ፍጹም ንጹሕ የሆነ ልብም ለሚያልፉና ለማይጠቅሙ የዚህ ዓለም ነገሮች ሁሉ የሞተና ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሕያው የሆነ ልብ ነው። አእምሮው በማይታየው ሰማያዊ ነገር የተያዘ ስለሆነ ለሚታየው ኃላፊ ነገር አይገዛም። ያለእረፍትና ያለማቋረጥም ሰማያዊውን መለኮታዊ ምስጢር ስለሚያስብ ለማይጠቅም ነገር ሥፍራና ጊዜ የለውም። ይህም ከንጽሕና ቅደመ ሁኔታዎች አንዱ ነው።

ሰው በሚታዩ ነገሮች ሊሠራባቸው እንጂ የሚታዩት ነገሮች በሠው ላይ ሊሠሩብት አይገባም። ሰው ልቡን ከእግዚአብሔር ጋር ስለሚያደርግ በሚታየው ነገር ቢሠራም ትኩረቱ ስለሚታየው ነገር አይደለም። በወንጌል “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይውዳል፣ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል” እንደተባለ በሚታየው ዓለም ስንኖር የማይታየውን በማሰብ ትኩረታችንን ከሚታዩትና ከማይጠቅሙት የዚህ ዓለም ነገሮች ማራቅ ይጠበቅብናል። ማቴዎስ 6፡24። ይህም ከንጹሕ ልብ የሚጠበቅ ነው። በመጽሐፍ “ነገር ግን ያለሃስብ እንድትኖሩ እወዳለሁ።” ተብሏላና። የሚታየውን ሃላፊ ነገር አለማሰብ የልብ ንጽሕና ምልክት ነው። 1ቆሮንቶስ 6፡32። ለዚህ ነው ቀደምት አባቶቻችን “ ክርስቶስንም አገኝ፡ዘንድ በክርስቶስም በማመን ያለውን ጽድቅ አገኝ፡ዘንድ ስለ እርሱ ነገር ሁሉ ጉዳት እንደሆነ እቆጥራለሁ።” በማለት የሚታየውን ዓለም የናቁት። ፊልጶስ 3፡8። ዓለም በነዚህ ቅዱሳን ዘንድ የተናቀች ስለነበርች እነርሱ በሰላም ይኖሩ ነበሩ፤ይህም ቅዱስ ጳውሎስ “በዚች ዓለም የሚጠቅሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፣የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።” ያለውን  በተግባር እንደፈጸሙት ያስረዳናል።1 ቆሮንቶስ 7፡31።

ማንኛውም ሃሳብ በራሱ ውጤት የሌለው አይደለም ነገር ግን ለሌላ ሃሳብ ምንጭ ይሆናል። ሃሳብ በአእምሮአችን ውስጥ በሰፈነ ጊዜ ለተለያዩ ግምቶችና ሕልሞች ምንጭ ይሆናል። ለጸሎት በምንቆምበት ጊዜ ከእነዚህ ሃሳቦች የተነሳ በፊታችን የሚመላለሱት ልዩ ልዩ ነገሮች ተመስጦአችንን እንድናጣ ያደርጉናል። ስለዚህ የዚህ ዓለም ሃሳብና ሥጋዊ ስሜት ጊዜያችንን እንዳያባክነው መጠንቀቅ ይኖርብናል። የቀደመ ልማዳችን በኅሊናችን በመጣ ጊዜ ወዲያው በመነሳት “አቤቱ ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ”” በማለት መጸልይ ይገባል።መዝሙር 118፡37።

የአእምሮ መንቃትና ከሃሳብ ጋር መዋጋት ከአእምሮና ከልብ ንጽሕና ይቀድማል። ስለዚህ ለእግዚአብሔርና ለእርሱ መንግሥት እንግዳ የሆነ ሃሳብ ሁሉ ከእኛ መራቅ አለበት። ልቡናችንም እንዲሁ ከዓለማዊ ሃሳብ የተለየ መሆን አለበት። ሰማያዊ በሆነው ሃሳብ ደስተኞች ለመሆን ራሳችንን ከዓለም ማራቅ አለብን። የሰው ስሜቱ ከዓለም የተለየ ከሆነ ዓለማዊ የሆነውን ነገር ለማሰብ የሚያነሳሳው ነገር አይኖርም። ዓለማዊ የሆነ ነገርም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ ይቃወመዋል፤ አእምሮው በሰማያዊ ሃሳብ የተያዘ በመሆኑም ዓለማዊውን ነገር አያስበውም ምክንያቱም “ አቤቱ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ? ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።” በማለት የሚያገኘውን ደስታ ያዘገይበታልና ነው። መዝሙር 118፤96።

ታዲያ ሰው ከልብ ንጽሕና ሊድረስ የሚችለው እንዴት ነው? ከልብ ንጽሕና ሊደርስ የሚችለው ከኃጢአት ሲነጻ፣ ከህልም፣ ከሃሳብና ከግምት ሲነጻ፣ እንዲሁም ከማይጠቅም ወይም ከማያስፈልግ ነገር ሲነጻ ነው። እነዚህ ሁሉ የንጽሕና አሉታዊ ገጽታዎች ናቸው።

ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

ከ “የንስሐ ሕይወት”

በአቡነ ሽኖዳ 3ኛ

ትርጉም ዲ. ታደሰ ወንድም አገኘሁ

 

 

Close Menu