‹‹የሁለተኛው ወንዝ ስም ግዮን ነው:: እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል›› (ዘፍ. ፪:፲)
ከኤዶም ፈልቀው ምድርን ከሚያጠጡት አራት ወንዞች ኤፌሶን፣ ጤግሮስ፣ ኤፍራጥስ፣ መካከል ሁለተኛው ግዮን ወይንም ዓባይ ወንዝ የሀገራችን ሲሳይ /በረከት/ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክሮች ናቸው፡፡ ‹‹ወንዝም ገነትን ያጠጣ ዘንድ ከኤዶም ይወጣ ነበር፤ ከዚያም ለዐራት መዓዝን ይከፈል ነበር፡፡ የአንደኛው ወንዝ ስም ኤፌሶን ነው፤ እርሱም ወርቅ የሚገኝበትን የኤውላጥ ምድርን ይከብባል፡፡ የዚያችም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፡፡ በዚያም የሚያብረቀርቅ ዕንቊ አለ፡፡ የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፤ እርሱም የኢትዮጵያን ምድር ሁሉ ይከብባል፤ የሦስተኛውም ወንዝ ስም ጤግሮስ ነው፤ እርሱም በአሶር ላይ የሚሄድ ነው፡፡ አራተኛውም ወንዝ ኤፍራጥስ ነው›› እንዲል፡፡ (ዘፍ. ፪:፲-፲፬)
ግዮንንም ዓባይ ወይንም ግሽ ዓባይ ብለው የሰየሙት ጻድቁ አባታችን አቡነ ዘርዐ ብሩክ እንደሆኑ በገድላቸው ተጽፏል፡፡ ይህም እንዲህ ነበር፤ አቡነ ዘርዓ ብሩክ የንጉሥ ጭፍሮች ሊገድሏቸው ሲያሳድዷቸው ግዮን ወንዝ እንደደረሱ ከጠላቶቻቸው ለማምለጥ የያዙትን ዳዊትና ወንጌል እንዲሁም ስብከተ ወንጌል ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ሰባት መጻሕፍት ሁሉ ለግዮን ወንዝ አደራ ሰጥተው ሸሹ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ሲመለሱ ‹‹ኦ ግዮን ግሥኢ መጻሕፍትየ፤ ግዮን ሆይ መጻሕፍቴን ግሺ /መልሺልኝ/›› አሏት፡፡ ግዮንም አንድም የውኃ ጠብታ ሳይኖርባት መጻሕቶቻቸውን መለሰችላቸው፡፡ አባታችንም ዘሩፋኤል ለተባለው ደቀ መዝሙራቸው ባሳዩት ጊዜ ከእርሳቸው ጋር አብሮ የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቀ።
አቡነ ዘርዐ ብሩክም ግዮንን ባርከው ‹‹ይኩን ፈውስ ዐብይ በውስቴትኪ፤ በውስጥሽ ታላቅ ድኅነት ይደረግብሽ›› አሉ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መካኖች ይወልዱ፣ ድዉዮች ይድኑ ጀመር፤ ‹‹ወእም አሜሃ ተሰምየት ዐባይ ይእቲ ፈለግ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይህች ዐባይ ተብላ ተጠራች።›› ከዚህም ሌላ ጻድቁ አባታችን በዚሁ ወንዝ አካባቢ ለሠላሳ ዓመት ሲጸልዩ ፈጣሪ ጸሎታቸውን ሰምቶ የድኅነት ቃል ኪዳን ሰጥቶአቸዋል። (ገድለ አቡነ ዘርዐ ብሩክ)
እግዚአብሔር አምላክ ወንዞችን ለሰው ልጅ እንደፈጠራቸው ሁሉ ዐባይ የሀገር ሲሳይ ነው፤ የሰው ልጅ ሕይወቱ በሙሉ ከውኃ ጋር የተያያዘ ነውና፡፡ የውኃ ጥቅም በመጠጥና በመብል ብቻ አልተገደበም፤ በመስኖ አማካኝነት ለእርሻ ከፍተኛ ጥቅም ስላለው የሀገር ሀብት ነው፡፡ ምክንያቱም የትኛውም ሀገር ያለ እርሻ የምግብም ሆነ የመጠጥ እንዲሁም ንጹሕ የከባቢ አየር ማግኘት አይችልም፡፡
ውኃ አዝርዕት እንዲበቅሉ እጽዋት እንዳይደርቁ ከማድረጉም ባሻገር በመስኖ አማካይነት የተለያዩ አዝርዕትን፣ በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትን በማምረት በቂ ምግብ ለማግኘትም ያስችላል፡፡ በተለይም ውኃን ወይንም ወንዝን ገድቦ ለመስኖ በመጠቀም በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ ምርት ማምረት ስለሚቻል ለእርሻ ጥቅም አለው። ይህም በመስኖ በመጠቀም ለምግብ ፍጆታና ለገበያ የሚሆን ምርት በሰፊው ማምረት ስለሚቻል ነው።
ኢትዮጵያ ግን ያሏትን ወንዞች በተገቢው መንገድ ለመጠጥ እና ለምግብ አቅርቦት ለማዋል ብትጥርም በውኃ እጦት ችግር የማይጠቃ አካባቢ የለም፡፡ ይህም ሀገራችን ውስጥ ካሉት አንዱ ከባድ ችግር ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ውስጥ ከግማሽ በላይ ያለው ሕዝብ ደግሞ በመካከለኛ እና በዝቅተኛ የገቢ ምንጭ የሚተዳደር በመሆኑ በምግብም ሆነ በመጠጥ አቅርቦት ችግር ተጋላጭ ነው፡፡ በየጊዜውም ለተነሡ ረኀቦችና ድርቆችም መንስኤው የወንዞች ለመጠጥና ለምግብ አቅርቦት በቂ አለመሆን እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ እግዚአብሔር አምላክ ለእኛ የፈጠረልን የሀገር ሲሳይ የሆነው ዐባይ ወንዝ ለዘመናት ከሀገራችን ኮብልሎ ጎረቤት ሀገር ግብፅን ሲመግብ መኖሩ የታወቀ ነው፡፡ ከሀገራችን የሰበሰበውን አፈር ጠራርጎ ዐባይ እንደ ዘንዶ እየተምዘገዘገ በበረሃ አቋርጦ ሀብቱን በየመንገዱ እየዘራ ግብፅ ከገባ በኋላ ግን ለወራት ሰክኖ በመቀመጥ አቅሙን ሙሉ ይሰጣታል:: እርስዋም እስከፈለገችው ትጠቀምበታለች::
ዐባይ ከኢትዮጵያ እንደመነሳቱ ሙሉ በሙሉ ባለቤትነቱ ለእርሷ እንደሚገባ በማመን በዘመናት የተነሱ መንግሥታት ከግብፅ እንዲሁም ከተባበሩት የዓለም መንግሥታት ድርጅቶች ጋር በመወያየት ወንዙን ሀገሩ ለማስቀረት ብዙ ተሟግተዋል፡፡ ወደ ጦርነት ከመግባት ይልቅም በስምምነት ጉዳዩ እንዲፈታም ተጥሯል፡፡
ሆኖም እንደኛ ሁሉ የግብፅ ጥሬ ሀብት እና ዋና የሀገሪቱ ገንዘብ ማመንጫ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ለእኛ ማስቀረት ባንችልም ለሁሉቱም ሀገራት ይሆን ዘንድ ዐባይን የመገደብ መብት እንደተሰጠን ይታወቃል፤ ለዚህም ሁሉም ተረባርቧል፡፡
በአሁን ሰዓትም የዐባይ ግድቡ ውኃ ይዞአል:: ይህም የሁላችን ስለዚህ ይህ ለሁላችን ደስታ ነው:: ‹‹የወንዙን ውኃ ሙላልን ብለን እግዚአብሔር እስከ ልካቸውና እስከ ወሰናቸው ይሞላ ዘንድ ስለ ወንዝ ውኃ እንማልዳለን›› ተብሎ በጸሎተ ቅዳሴ ላይ እንደምንማጸነው በቀጣይ ዘመን ኢትዮጵያን ከዐባይ ሲሳይ ተቋዳሽ ያደርጋት ዘንድ እንመኛለን:: (ሥርዓተ ቅዳሴ)
እግዚአብሔር አምላክም የዐባይ ወንዝ ሲሳይ ተካፋይ እንዲያደርገን ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡
ማኅበረ ቅዱሳን