ዘመነ ጽጌ
በሀገራችን በኢትዮጵያ የዘመን ስሌት አዲሱን ዓመት በወርኃ መስከረም አንድ ብለን መቁጠር እንደጀመርን ከምናስተውላቸው ዓበይት ክስተቶች መካከል የውኃውን መጉደል፣ የሰማዩን መጥራት እንዳለ ሆኖ ትልቁን ሥፍራ የሚይዘው የምድር በአበቦች ማጌጥ ነው፡፡
በወርኃ መስከረምና ጥቅምት(ዘመነ ጽጌ) ምድር ለሠርጓ እንደተዘጋጀች ሙሽራ መዓዛቸው ግሩም በሆኑና ልዩ ልዩ ቀለማት ባላቸው አበቦች ታሸበርቃለች፡፡ ይህን ጊዜ ጠቢቡ ሰሎሞን ከመዝሙር ሁሉ በሚበልጠው መዝሙሩ እንዲህ ገልጦታል፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፣ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡/መኃል. 2፡11/ በማለት ወርኃ ክረምት ተፈጽሞ የበጋው ወቅት የሚጀምረው ምድርን በአበባና በዝማሬ በማስዋብ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በዚህም የአበባ ወቅት ልጇ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ሕይወት ጋር አመሳስሎ በወንጌሉ በዚህ ምድር ኑሯችን አብዝተን ልናስብ የሚገባው ዘላለማዊውንና ሰማያዊውን ሕይወት እንዴት ገንዘብ ማድረግ እንዳለብን እንጂ ስለ መሬታዊ አኗኗራችን በሀሳብ ብዛት ልንደክም እንደማይገባ እንዲህ አስተምሯል፡፡ ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ የሜዳ አበቦች እንዴት እዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፣ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጎደላችሁ እናንተማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን ምንስ እንለብሳለን ብላችሁ አትጨነቁ . . . /ማቴ.6፡28/ በማለት ሰብአ ዓለም እንደሚጨነቁት ለኃላፊውና ጠፊው ምድራዊ ኑሮ በመጨነቅ ደክመን ከዘላለማዊው ሕይወት ከእርሱ እንዳንለይ ያሳስበናል፡፡
ቅዱስ ዳዊትም በምድር ላይ የሰው ልጅ ሕይወቱ እንደ አበቦች መሆኑንና ሰው በተሰጠው ጥቂት ጊዜ መሥራት ያለበትን ሁሉ ፈጽሞ ከፈጣሪው ጋር ሊኖር እንደሚገባው የእኛን ሕይወት ከአበቦች ጋር በንጽጽር ያሣያል፡፡ ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ሰብእሰ ከመሣዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው እንደዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፣ ነፋስ በነፈሰበትም ጊዜ ያልፋልና፡፡ በማለት ሣር ከምድር በቅሎ አብቦ ያፈራል ያላፈራ እንደሆን ግን በፀሐይ ጠውልጎ በነፋስ ይረግፋል ከበቀለበትም ይታጣል፡፡ እንዲሁም ሰው ይወለዳል በልጅነት አበባ አምሮ በወጣትነት ፍሬ ቢያፈራ ማለትም መልካም ምግባር ቢሠራ በጉልምስናው እየተደሰተ በቶሎ ያልፋል፡፡ ልክ አበባው በፀሐይ ጠውልጎ በነፋስ እንደሚረግፈው ሰውም በሕመም ፀሐይ ደርቆ በሞት ነፋስ ይወሰዳል፡፡ መልካም ሥራ ከሌለው እስከመወለዱም ይረሳና አስታዋሽ ያጣል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓለም የተሰጠን ጊዜ በጣም አጭር በመሆኑን ከዚህ ዘመን /ዘመነ ጽጌ/ እንረዳለን፡፡
በሌላ በኩል ስንዱ እመቤት የሆነችው ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ዘመነ ጽጌ /ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 6/ ያለውን ወቅት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስደትን በማሰብ ማኅሌተ ጽጌ /የአበባ ወቅት ምሥጋና/ በተባለውና በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣው አባ ጽጌ ድንግል በደረሰው ማኅሌተ ጽጌ እመቤታችንን እና ልጇን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባ እየመሰለች በሌሊት የማኅሌት ምሥጋና ታመሠግናለች፡፡
ይህ ወቅት ልክ ምድር በአበቦች እንደምታጌጥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በዚህ ታላቅ ሊቅ የምሥጋና ድርሰት በከበሮው በጸናጽሉና በመቋሚያ ልጆቿ ዙሪያዋን ከበው አምላካቸውን እግዚአብሔርን በእመቤታችን በኩል ስለተደረገላችው ሁሉ በማመስገን ይደምቃሉ፡፡
ማኅሌተ ጽጌ በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን፣ ብዛቱም ልክ እንደ መዝሙረ ዳዊት 150 ነው፡፡ ይህ የምሥጋና ድርሰት ምሥጢር፣ ታሪክ፣ ምሳሌ፣ ጸሎትና ምሥጋናን አካቶ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ከዐሥራው መጻሕፍት ተውጣጥቶ የተዘጋጀ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በአበባ ስትመስል ልጇን በፍሬ፤ ልጇን በአበባ ስትመስል እርሷን በበትር/በግንዱ/ እየመሰለች ታመሰግናታለች፡፡ ልክ ኢሳይያስ ከእሴይ ሥር ግንድ ይወጣል ከግንዱም አበባ /ኢሳ.11፤1/ በማለት እመቤታችን በግንድ ተመስላ በአበባ የተመሰለ ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳስገኘች ለማስረዳትና ትውልዷም ከዳዊት ወገን መሆኑን ሲያስረዳ እሴይን ሥር ብሎ ይጠራዋል፡፡
አባ ጽጌ ድንግልም በምሥጋና የወለደው አባቱ ዳዊትን ተከትሎ ፍሬ ሕይወት ክርስቶስን ያፈራሽ አበባ እመቤታችን አንቺ ነሽ /ማኅሌተ ጽጌ/ እያለ ያመሰግናታል፡፡
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ፣ ማርያም ዕፀ ሳቤቅ ወምሥራቅ ዘያዕቆብ፣ ወላዲቱ ለሥርግው ኮከብ በማለት ይሥሐቅ ለመሥዋዕት በሞሪያ ተራራ በአባቱ እጅ ሊሰዋ በቀረበ ጊዜ በእርሱ ፈንታ የተሰዋው በግ የተያዘብሽ ዕፀ ሳቤቅ /ዘፍ.22፤13/ አንቺ ነሽ፡፡ ይስሐቅ የአዳም፣ በጉ የክርስቶስ፣ ዕፀ ሳቤቅ የእመቤታችን ምሳሌ ነውና፡፡ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ተብሎ የተነገረልሽ በኮከብ የተመሰለ አማኑኤልን የወለድሽልን አማናዊት ምሥራቅ አንቺ ነሽ፡፡ አንድም የእውነት ፀሐይ ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘብሽ ምሥራቅ አንቺ ነሽ በማለት የቅድስት ድንግል ማርያምን ወላዲተ አምላክነት የልጇንም መድኃኒትነት ይመሰክራል፡፡
ማዕረረ ትንቢት ማርያም ዘመነ እንግዳ፣
ወዘመነ ፍሬ ጽጋብ ዘዓመተ ረኃብ ፍዳ፣
ብኪ ተአምር ዘይቤ ኢዩኤል ነብየ ኤልዳ፣
ያንጸፈጽፍ እም አድባሪሁ ወአውግሪሁ ለይሁዳ፣
ፀቃውዓ መዓር ጥዑም ወኀሊብ ፀዓዳ፡፡
ትርጉም፡- የትንቢት መከር መካተቻ የሆንሽ እንደ ዘመነ ጽጌ የረሃብን ዘመን ያስወገድሽ ማርያም የኤልዳ ነብዩ ኢዩኤል/ይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ጸዓዳ ወተት ይፈሳል ብሎ/ የተናገረው ትንቢት በአንቺ ታወቀ፣ ተፈጸመ እንዲል አባ ጽጌ ድንግል በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ፡፡
ለሁሉም ጊዜ እንዳለው የታወቀ ነው፡፡ ነቢያት የተናገሩት የትንቢት መከር መካተቻ /ፍጻሜ/ የሆንሽ ማለት ስለ አምላክ ከድንግል በድንግልና መወለድና ከእርሷ የተወለደውም የዓለም ሁሉ ቤዛ ሆኖ ስለመሰጠቱ ትንቢት የተናገሩ የነቢያት የትንቢታቸው እና የአበው ተስፋ ፍጻሜ መሆኗን ያስገነዝባል፡፡ በዚህ መስከረም መገባደጃና በወርኃ ጥቅምት እሸቱ የሚበላበት ማርም ከቀፎ የሚቆረጥበት ረኃብ የሚወገድበት ወቅት ነው፡፡ ለዚህም ገበሬው አይዞሽ ነፍሼ ደረሰልሸ ገብሴ በማለት የምድርን በረከት ፈጣሪን እያመሰገነ ይመገባል፡፡
ማር የሚገኝ በአበባ ወቅት ነው፡፡ አበባ ከሌለ ማር የለም፡፡ አበባ ድንግል ማርያም ባትገኝ ማር ክርስቶስም ከወዴት ተገኝቶ የመረረ ሕይወታችንን ያጣፍጠው ነበር፡፡ /ኢሳ. 1፡9/ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሠልን ነበር እንዳለ ይህች በጊዜዋ የተገኘችÂ አበባ ድንግል ማርያም ናት፡፡ ነቢዩ ኢዩኤልም ከይሁዳ ተራሮች ጣፋጭ ማርና ፀዓዳ ወተት ይፈሳል፣ ብሎ የተናገረው ከሊባኖስ ተራራ መወለዷን ሲያጠይቅ ነው፡፡ ምክንያቱም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከአብርሃምና ከዳዊት ወገን ናት በእስራኤል ዘንድ እንደነዚህ የከበረ የለምና በተራራ መስሎ ተናገረላቸው፡፡ ስለዚህ ነው የነቢያት የትንቢታቸው ፍጻሜ አንቺ ነሽ ብሎ ከተናገረ ከአባ ሕርያቆስ ጋር አባ ጽጌ ድንግልም በምሥጢር ይተባበራል፡፡
በዚህ በዘመነ ጽጌ ወቅት ቅዳሜ ሌሊቱን ለእሑድ አጥቢያ በየገዳማቱና አድባራቱ በያሬዳዊ ዜማ ተውቦ የሚቀርበውን ይህን ጽጌ ማኅሌት በመሳተፍ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከትና ረድኤት እንድትሳተፉ እያሳሳብን በዚህ መካነ ድር ደግሞ በወርኃ ጽጌ ባሉት ተከታታይ ዐራት ሳምንታት ከማኅሌተ ጽጌው ድርሰት መነሻ በማድረግ ስለ እመቤታችንና ስለ ልጇ ከተነገረው የምናስነብባችሁ መሆኑን በደስታ እንገልጽላችኋለን፡፡
ጣዕሟን በአንደበታችን ፍቅሯን በልቡናችን ያኑርልን፡፡ አሜን፡፡
በአምኃ ልዑልሰገድ