ከታሪክ ማኅደር

የቤተ ክህነት አስተዳደር
ስለ ሊቀ ጳጳሱና ጳጳሳቱ ሹመትና አስተዳደር
በወትሮው ልማድ ሊቀ ጳጳሱ የኢትዮጵያ ጳጳሳት የበላይ ሆኖ ከእስክንድርያ ፓትሪያርክ ተሾሞ ይመጣና ሥራውንም በንጉሠ ነገሥቱ ዋና ከተማ ተቀምጦ ያካሂድ ነበር።
ጳጳሶቹም፣ ከዚያው ከግብጻውያን መካከል ተመርጠው እየተሾሙ መጥተው ታላላቅ ንጉሥ የሚያስኝ የስብከት አገር የሚሰጣቸው ናቸው። ሥራቸውም በየክፍል አገራቸው ሥልጣን መስጠትና በሕግ፣ በተክሊል፣ በሃይማኖት፣ በጥምቀት፣ በቁርባን ይህንንም በመሳሰለ በመንፈሳዊ ነገር ሁሉ መዳኘትና በንስሃ መቅጣት ነው።
ከ1922 ዓ. ም በፊት የኢትዮጵያ መምህራን ምንም የተማሩ ቢሆኑ የጵጵስና ሥላጣን አይሰጣቸውም ነበር። እንደ “ሞኖፖል” ሆኖ ተሹመው የሚመጡት እነዚያው ግብጻውያን ብቻ ነበሩ። ይህም ከመንፈሳዊ ሥራ ወጥቶ የንግድ መንገድ የያዘ ጉዳይ ሕዝቡን ሳይጠቅም ቤተ ክህነቱን የሚጨቁን በመሆኑ መንግሥታችን ከእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ብዙ ተላልኮና ተከራክሮ የቀድሞውን ልማድ ፍቆ የኢትዮጵያ መምህራንም ከጵጵስናው ምርጫ ውስጥ እንዲገቡ አደረገ።
ወዲያው ባ1921 ዓ.ም አራት ሊቃውንት ተመርጠው ምድረ ግብጽ ሄደው የጵጵስና ሥልጣን ተቀብለው ተመለሱ።
ደግሞ ባ1922 ዓ.ም ከነዚህ ካራቱ ሌላ ዕጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አዲስ አበባ ላይ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ በበአታ ቤተ ክርስቲያን ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የእስክንድርያ ፓትሪያርክ የጵጵስና ሥልጣን ተቀበሉ። ለነዚህም ለአምስት ጳጳሳት ለያንዳናዳቸው ደንቡን አስተዳደሩን እስቲያጠኑ ጥቂት ጊዜ በአዲስ አበባ ከቆዩ በኋላ የሚያስተምሩበት ሰፋፊ የስብከት አገር ተደረገላቸው።
ከዚህ በኋላ ሁሉም በየተሰጡበት የስብከት አገራቸው እየሄዱ ደስ በሚያሰኝ አኳኋን ሕዝቡን ማስተማርና መስበክ ዠመሩ። ከነዚሁም አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል የተባሉት ባ1928 ዓ.ም ለኢጣልያ አንገዛም ሲሉ ሕዝቡን እያጽናኑ ካርበኛው ጋራ ተሰልፈው በጠላት እጅ ሞቱ።

ባ1923 ዓ.ም በጥር 23 ቀን ከንጉሠ ነገሥቱ ለጳጳሳቱ ስለ ሀገረ ስብከታቸው የተጻፈ፦
የኢትዮጵያ የመላው ሊቀ ጳጳሳት በአቡነ ቄርሎስ ሆኖ ከውስጡ ክፍል ስብከትም ኢትዮጵያ መኻል ሆኖ ደቡቡ ለአቡነ ሳዊሮስ፣ ምዕራቡ ለአቡነ አብርሃም፣ ምሥራቁ ለአቡነ ጴጥሮስ፣ አዜቡ ለአቡነ ሚካኤል፣ ሰሜኑ ለአቡነ ይሥሕቅ ይሁን።

ሀ) አቡነ ሳዊሮስ ዘደቡበ ኢትዮጵያ።
ራሱ የወበሪ ድንበር እግሩ የጎዣም ድንበር።

ለ) አቡነ ይሥሕቅ ዘሰሜነ ኢትዮጵያ።
ራሱ ጨጨሆ እግሩ አስከ ኤርትራ ወሰን።

ሐ) አቡነ አብርሃም ዘምዕራበ ኢትዮጵያ።
ራሱ ጎንደር እግሩ መተማ እንግሊዞች ወሰን ድረስ።

መ) አቡነ ጴጥሮስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ።
ራሱ በሽሎ በመለስ እግሩ አቦክ ፈረንሳዊ ወሰን ድረስ።

ሠ) አቡነ ሚካኤል ዘአዜበ ኢትዮጵያ።
ራሱ ጉደር ወንዝ እግሩ እንግሊዝ ወሰን ድረስ።

ከባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል።
ዝክረ ነገር 1942 ዓ.ም

Close Menu