አክርመው

አክርመው

አንድነታችን ኮስምኖ…
ልዩነታችን ከደራ
ፍቅራችን አበባው ረግፎ…
ጥላቻችን ከጎመራ
በቋንቋ “ምንዝር” አምልኮ…
የዕምነት ዋልታችን ከነቃ
አንተው ፍረደን ክርስቶስ…
የሊቀ ሊቀ ካህናት…
የሰማይ የምድሩ አለቃ ::
የልባችንን ምርምር…
የ”አጣራሁ” ባዩን ኩላሊት
የአውሎ ነፋሱን ድርሻ…
የማዕበል ውሎውን ሌሊት
የክፋታችንን አቀበት…
የስፋት ጥበቱን ጥልቀት
የተንኮላችንን ተራራ….
የጥቃት ሾተላይ ርቀት
ልኩን የምትመረምር….
መጠኑን የምታውቅልን
ገደቡን የምትሰፍርልን
ጌታ-ሆይ ! አንተ መርምረን
ጌታ-ሆይ ! አንተው ፍረደን ::
የአንድነትችን ዝማሬ…
በቋንቋችን ሲጠራረስ
የዕምነታችን ፅኑ መሰረት…
በምግባራችን ሲራከስ።
አንተው ውቀሰን!
አንተው መልሰን!
በስቅለትህ አበርትተህ
በደምህ ፅዋ አብሰን
በጎንህ ቁስል
በህመምህ
በስቃይህ ፈውሰን።
በጎሰኝነት ልሳን
እመነታችን ከሚፈርስ
የካቻምናው ምህላችን
ዎዮታችን ከሚመለስ
እንደገ “ገባዎ” ሰማይ ..
ፀሃይን እንደ እንዳደረቀው
በአዲስ ዓመት ተለያይተን ..
ዓመቱን አታ – ሻግረው ::
ስቅታውን እንዳያዘንብ
ሰማይን እንደለጎመው
እንደ አርማጌዶ ጦርነት
ሰዓቱ ይቁም ገዝተው ::
መላከ ሞትን በደጁ
ለዓመታት እንደገተረው
መስከረም አይባት አይጣባ..
በጷግሜ ፀበል አክርመው።
የክረምቱ ዝናብ ይውረድ
በወጨፎው ይግረፈው
አፈር ምን ጊዜም ባይጠራም
በዕንባ ጅረቱ ይጠበው።
መለያየት ከሆነ
የአዲሱ ዓመት ግባችን
መበታተን ከሆነ…
የትውልድ ዕጣ ፋንታችን
ጎሰኝነት ከሆነ …የጉያ አመል ዛራችን
ፀሐይዋ ከዚሁ ትጥለቅ…
በዳዋ ይዋጥ ገበናችን ::
በለመለሙ መስካችን ላይ…
እንስሶች አይቦርቁበት
በቆሎው እንዳሞሸረ
እሸቱ አይበላበት።
የስንዴው እንኩቶ ፍልፍል..
ከገለባው አይለያይ
እንቁጣጣሽም አታብብ
የመስቀል ወፍም አይታይ።
ቄጤማውም አይጎዝጎዝ..
ለምለምነቱ ይራቀው
ፌጦ ልሞ አይዘጋጅ
እንጀራውንም ያድርቀው።
ኑጉ፣ ፈንድሻው ጣዕም ይጣ..
ዳቦውም አይቆረስ
ከግራዋ ከዕሬት ይምረር..
የቡና ስኒው ይፈርከስ ::
ጠላውን “ጠላ” አያ’ርገው
ደሮውም ከድስቱ አይውጣ
የኮረዳዎች ከበሮ
አበባ አዬሁሽ አይምጣ።
ሀበሻ አፉን ለጉሞ
በሱባኤ ይታሰር
ከሉን እንደደረበ
ከአመድ
ከድብዳብ ይደር።
ወዮታውን ያቅልጠው
እግዞታውን ያውርደው
ፀሎቱን ክርስቶስ ሰምቶ
“በመንግስቱ” ቢያስበው
ለሚብረገረግ መንፈሱ
ጰራቅልጦስን ቢያድለው።
ጌታ ሆይ!
በአረጀ ቁርበት አቁማዳ..
ዓመቱን አታ-ሻግረን
የይቅርታ ድርብ ሸማህን…
ፀጋ ፍቅርህን አልብሰን
በቋንቋ ብንለያይም
በአምላክነትህ አጣምረን
በዘረኝነት አድፈናል
በኢትዮጲያዊነት እጠበን ::
የርኩሰት ምኞት ጥንስሱ
ከነገ ራዕይ ተስፋችን….
እንዳይከለስ መንፈሱ
በሆታ ! በሆያ ሆዬ !…
በአበባ እንዳይዘከር
በአበባዬሆሽ ቄጠማ…
ይዘነው እንዳንሻገር
በአሮጌው ላይ አምክንልን…
በቃልህ ፈቃድ ይታጠር ::
ምህረትህ ለዕንባችን ይዋስ …
በደም በስጋህ አክመው
አባቶች ያወረሱንን…
አንድነታችንን አክርመው ::
——————————
ፍቅርተ ፀጋይ
9/6/2019

Close Menu