ንስሐ ምንድን ነው ?
ንስሐ ማለት አንድ ሰው በሠራው ጥፋት፣ ባደረገው ስህተት፣ በፈጸመው ኃጢአት ማዘኑና መቆርቆሩ፣ መፀፀቱ፣ ዳግመኛም ያንን የመሰለ ኃጢአት ላለማድረግ የሚወስነው ውሳኔ ነው። በአጭሩ ንስሐ ማለት ትርጉሙ ይህ ሲሆን፤ በሰዎች ሕይወት ውስጥ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስገነዝበን ቀጥሎ የተጠቀሱትን ፍችዎች ያጠቃለለ ሆኖ እናገኘዋለን።
- ንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ሚልኪያስ 3፡7
- ንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነው። 2 ቆሮንቶስ 6፡19
- ንስሐ ከኃጢአት እንቅልፍ መንቃት ነው። ሮሜ 13፡11
- ንስሐ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት መመለስ ነው። ኤፌሶን 5፡14
- ንስሐ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ እግዚአብሔርን የሚያስወድድ ከንጹህ ልብ የሚመነጭ ጸጋ ነው። ሕዝቅኤል 36፡25-27
- ንስሐ ከኃጢአትና ከዲያቢሎስ ባርነት ነጻ መውጣት ነው። ዮሐንስ 8፡34-36
- ንስሐ ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ስለ ቅድስና ብሎ ኃጢአትን መተው ነው። ምሳሌ 28 13
- ንስሐ ኃጢአትን ከተዉ በኋላ በፍጹም መልሶ አለመስራት ነው።
- ንስሐ ስለ አለፈው ስህተት አብዝቶ ማልቀስ፤ ያለፈውን የኃጢአት ኑሮ ማውገዝና መኮነን ነው። ኢዩኤል 2፡12
- ንስሐ ፍጹም የሆነ የሕይወት ለውጥ እንጂ ጊዜያዊ ስሜት አይደለም፤ ሮሜ 12፡2
- ንስሐ ኃጢአትን ሲሠሩ ከመኖር ይልቅ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን መሻት ነው። መዝሙር 73፡28
- ንስሐ የአዕምሮ መታደስ ነው። ሮሜ 12፡2
- ንስሐ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያስችል ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚያስገባ ቁልፍ ነው። ማቴዎስ 25፡1-13
- ንስሐ በቀራንዮ መስቀል ላይ እኛን ለማዳንና ከኃጢአት ባርነት ነጻ ለማውጣት የፈሰሰልንን የክርስቶስን ደም እንድናስብ የሚያደርግ መንፈሳዊ ሃብት ነው።
- ንስሐ ከኃጢአት የሚያነጻ ሱራፌል ከመንበረ ሥላሴ የወሰዱት የእሳት ፍም ነው። ኢሳያስ 6፡4
- ንስሐ ከሚመጣው የመጨረሻ መከራና ሃዘን መዳኛ ወይም ማምለጫ መንገድ ነው። ዮናስ 3፡10
- ንስሐ እግዚአብሔር የሰውን ኃጢአት ይቅር የሚልበትና ከኃጢአት ውጤት የሚያድንበት መሳርያ ነው።
- ንስሐ ከሰዎች ጋር ለመታረቅ የተዘረጋ የእግዚአብሔር እጅ ነው። መዝሙር 50/51
- ንስሐ እግዚአብሔር ወደ ሰው የሚጣራውን ጥሪ ሰምቶ ወደ እርሱ መመለስ ነው። ዮሐንስ 7፡51። ኤፈሶን 4፡30
- ንስሐ ስለ አለፈው ኃጢአት ከመፀፀት የተነሳ የተሰበረ ልብ ነው። መዝሙር 50/51፡17
- ንስሐ ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው ተፀፅተው ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይታረቁ በብርቱ በሚጥረው ሰይጣን ላይ የተገኘ ድል ነው። መዝሙር123/124፡ 6-7::
ወስብሃት ለእግዚአብሔር !
ዋቢ መጽሐፍ፦ የንስሐ ሕይወት