ኃጢአት ምንድን ነው?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልዕክቱ “ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች።”ብሏል። ያዕቆብ 1፡15. በሮሜ መልዕክቱ ደግሞ እንዲህ ብሎናል፤ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” ሮሜ 6፡23። ስለዚህ ኃጢአት የኅሊናና የመንፈስ ሞት ነው።
ኃጢአትን የሚሰራ ሰው በነፍሱ ሙት ነው፤ ከአባቱ ከእግዚአብሔርም የተለየና ወደ ዓለም የኮበለለ ሰው በኃጢአት ወድቋል። ከኃጢአቱ ያልተመለሰ ሙት መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጽ “ቅምጥሊቱ ግን በሕይወትዋ ሳለች የሞተች ናት።” ብሏል። 1 ጢሞ 5፡6።
በኤፌሶን መልዕክቱ ደግሞ እንዲህ ይላል፡ “ በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥” ኤፌሶን 2፡1-5። እንግዲህ ከዚህ ጥቅስ የምንማረው ኃጢአት መንፈሳዊ ሞት እንደሆነና ከዚህ መንፈሳዊ ሞት የሚያድነን እግዚአብሔር መሆኑን ነው።
ኃጢአት በዓለም መታለልና መጥፋት ነው። ለዚህም ምሳሌ ከሚሆኑን ጥቅሶች አንዱ በሉቃስ ወንጌል የተጻፈው የጠፋው ልጅ ታሪክ ነው።
አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን። አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ። እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና። አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ሉቃስ 15:7-20።
ኃአጢአት በአለም መሸንፈና መዋረድ ነው። በመታገስ ኃጢአትን ማሸነፍ አቅቶት ክፉ ሲናገርት ክፉ የሚመልስ ሰው ለኃጢአት ተሸንፏል። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ እንዲህ ይላል፤ “ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።” ሮሜ 12፡21
ኃአጢአት ከእግዚአብሔር መለየት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ በጻፈው መልዕክቱ ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት መሆኑን እንዲህ ብሎ መዝግቦታል። ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? 2 ቆሮንቶስ 6፡14-15።
ኃጢአት መንፈስ ቅዱስን መቃወም ነው። በውስጣችን ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ ለእግዚአብሔር ልጆች እንደሚገባ በቅድስና እንድንኖርና የጽድቅን ሥራም እንድንሠራ ይፈልጋል። በኃጢአት የምንመላለስ ከሆነ ግን መንፈስ ቅዱስን እንቃወማለን። በቅዱስ መጽሐፍም፦ “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ።” ተብሏል። ኤፌሶን 4፡30። ስለዚህ ኃጢአት የሚሠራ ሁሉ የእግዚብሔርን መንፈስ ያሳዝናል።
ኃጢአት መቆሸሽ፣ ርኩሰትና ውርደት ነው። ትንቢተ ኤርሚያስ ስለዝሙት እንዲህ ይላል፦ ዓይንሽን አንሥተሽ ወደ ወናዎች ኮረብቶች ተመልከቺ፤ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ዓረባዊ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸው ነበር፤ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። ኤርሚያስ 3፡2
ስለ ኃጢአት ብዙ የሚባል አለ። በአጠቃላይ ግን ኃጢአት ጉድለት፣ ሕፀፅ፣ መታወር፣ ጨለማና እግዚአብሔርን መርሳት ነው።
በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት። ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም። ውኃ አጠጪኝ አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ስለዚህ ሳምራዊቲቱ። አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ። የእግዚአብሔርን ስጦታና። ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት። ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው። ኢየሱስም መልሶ። ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው። ኢየሱስም። ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ አላት። ሴቲቱ መልሳ። ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስ። ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት። ሴቲቱ። ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም። ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት። አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ሴቲቱ። ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ኢየሱስ። የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት። ዮሐንስ 4:2-26
ወደ ኢያሪኮም ገብቶ ያልፍ ነበር። እነሆም ዘኬዎስ የሚባል ሰው፥ እርሱም የቀራጮች አለቃ ነበረ፥ ባለ ጠጋም ነበረ። ኢየሱስንም የትኛው እንደ ሆነ ሊያይ ይፈልግ ነበር፤ ቁመቱም አጭር ነበረና ስለ ሕዝቡ ብዛት አቃተው። በዚያችም መንገድ ያልፍ ዘንድ አለውና ያየው ዘንድ ወደ ፊት ሮጦ በአንድ ሾላ ላይ ወጣ። ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ፥ አሻቅቦ አየና። ዘኬዎስ ሆይ፥ ዛሬ በቤትህ እውል ዘንድ ይገባኛልና ፈጥነህ ውረድ አለው። ፈጥኖም ወረደ በደስታም ተቀበለው። ሁሉም አይተው። ከኃጢአተኛ ሰው ጋር ሊውል ገባ ብለው አንጐራጐሩ። ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታን። ጌታ ሆይ፥ ካለኝ ሁሉ እኵሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ፤ ማንንም በሐሰት ከስሼ እንደ ሆንሁ አራት እጥፍ እመልሳለሁ አለው። ኢየሱስም። እርሱ ደግሞ የአብርሃም ልጅ ነውና ዛሬ ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል፤ የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአለና አለው።
ሉቃስ 19:1-10
ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን። መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው። ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን ሄዳችሁ። ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው። ማቴዎስ9:9-13