በዓለ ጰራቅሊጦስ

በዓለ ጰራቅሊጦስ (በዓለ መንፈስ ቅዱስ)
በዓለ ጰራቅሊጦስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሥርዓት (በቀኖና) ወስና ከምታከብራቸው የጌታችን፥ የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት* ውስጥ አንዱ ሲሆን የሚከበረውም ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በኀምሳኛው ቀን፥ በዐረገ በአሥረኛው ቀን ለቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ የወረደበትን ዕለት ለመዘከር ነው፡፡ (*ይህ በዓል የመንፈስ ቅዱስ በዓል ሆኖ ሳለ ከዘጠኙ ዐበይት የኢየሱስ ክርስቶስ አንዱ ሆኖ የተቆጠረው ለቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ሁሉ የተፈጸመበት ዕለት ስለሆነ ነው፡፡)
ጰራቅሊጦስ παράκλητος የጽርእ ቋንቋ (የጥንት ግሪክ Koine Greek) ቃል ሲሆን ትርጉሙም የሚናዝዝ (ናዛዚ)፥ የሚያጸና (መጽንዒ)፥ የሚያስደስት (መስተፈሥሒ)፥ አጽናኝ፥ ጠባቂ፥ ረዳት የሆነ ልዩ መንፈስ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ፥ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፤ ይኸውም ጰራቅሊጦስ ወይም መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ አካላት የአንዱ አካል የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡
በዓለ ጰራቅሊጦስ ማለትም በዓለ መንፈስ ቅዱስ በየዓመቱ የትንሣኤ በዓል በተከበረ በኀምሳኛው ቀን የሚውል በመሆኑ የጥንቱን ትውፊት በመያዝ በዓለ ኀምሳ ይባላል፡፡ የዘንድሮው የትንሣኤ በዓል ተከብሮ የነበረው ሚያዝያ ፳፬ ቀን ስለ ነበር ኀምሳኛ ቀን የሚሆነው እሑድ ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. ስለ ሆነ በዚህ ዕለት በዓለ መንፈስ ቅዱስ (በዓለ ጰራቅሊጦስ) ወይም በዓለ ኀምሳ (በዓለ ጰንጤቆስት) ይከበራል፡፡
በዓለ ኀምሳ ማለትም በዓለ ጴንጤቆስት (የኀምሳኛው ቀን በዓል) በዓለ ጰራቅሊጦስ ማለትም በዓለ መንፈስ ቅዱስ የተሰኘበትም ጌታችን፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከማረጉ ቀደም ሲል «እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።» (ሉቃስ ፳፬፥፵፱) ብሎ ለቅዱሳን ሐዋርያት በሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት [በራሱ መንገድ ሄዶ በተለየው በአስቆሮቱ ይሁዳ ቦታ ማትያስ ተተክቷል] (ሐ.ሥ.፩፥፳፮)፥ ሰባ ሁለቱ አርድእት፥ ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት እንስት ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ጋር በአንድነት በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ [ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ] እናት በማርያም ቤት [ጽርሐ ጽዮን] (ሐ.ሥ.፲፪፥፲፪) ሆነው በጸሎት በሚተጉበት ሰዓት በእሳት አምሳል መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው በልዩ ልዩ ልሳናት ወንጌልን የሰበኩበት ታላቅ ዕለት ስለሆነ ነው፡፡ (ሐ.ሥ.፪፥፩-፱) ይህች ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ትባላለች፡፡
በዓለ ኀምሳ፥ በግሪክ ጴንጤቆስት ወይም ፔንቴኮስት Πεντηκοστή እርሱም የኀምሳኛው ቀን በዓል መነሻው የብሉይ ኪዳን ሲሆን የብሉይ ኪዳን ሥርዓቶች ለሐዲስ ኪዳን ምሥጢረ ድኅነት ጥላና ምሳሌዎችም ናቸውና በኦሪት ዘሌዋውያን እንዲህ የሚል ትእዛዝ እናገኛለን «የወዘወዛችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ፤ እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ።» (ዘሌ. ፳፫፥፲፭-፲፮) በዚሁም ትእዛዝ መሠረት እስራኤላውያን ከፋሲካ (በዓለ ፍሰሓ) ጀምረው ሰባት ሱባኤ በመቁጠር (7 X 7=49+1=50) በማግስቱ እሑድ ኀምሳኛው ቀን በዕብራይስጥ השבועות ሻቮት ተብሎ የሚታወቀው አዲስ የእህል ቁርባን (እሸት) የሚያቀርቡበት ዕለት በዓለ ሰዊት (የእሸት በዓል) ሲሉት፤ በግሪኩ (በጽርእ) ጴንጤቆስት ወይም ፔንቴኮስት Πεντηκοστή በዓለ ኀምሳ ተብሎ ይታወቃል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ስለወረደላቸው ሐዋርያት በልሳናት ተናገሩ የምትለውን ኃይለ ቃል በመምዘዝና እንዳሻቸው በመተርጎም በልሳን እየተናገርን ነው በማለት ሰሚ የሌለው ቅብጥርጥር ታራራም ጳራራም ሲሉ የደመጣሉ፤ ለቅዱሳን ሐዋርያት የተገለጸላቸው ልሳን ማለትም ቋንቋ እነርሱ እንደሚሉት ዓይነት ሳይሆን ቅዱስ ሉቃስ ሰው በሚሰማው ቋንቋ እንደተናገሩ እንዲህ በማለት ጽፎልናል፤ «እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?» (ሐ.ሥራ ፪፥፯-፰) በማለት ልሳን ሰሚና ተናጋሪ ያለው ቋንቋ መሆኑን በግልጽ ያስረዳልና፡፡
ይህ ዕለት ሁላችንንም የሚጠብቅ፥ የሚያጠነክር፥ የሚመራ፥ የሚያጸና፥ የሚያጽናና መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ የወረደበት፥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ተመሥርታ በሐዋርያት ተሰባስባ በይፋ ሥራዋን የጀመረችበት ታላቅ ዕለት ስለሆነ ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ከጌታችን ትንሣኤ በዓል [ፋሲካ] በዋለበት በኀምሳኛው ቀን እሑድ በዓለ ጰራቅሊጦስ በዓለ መንፈስ ቅዱስ በማለት በታላቅ መንፈሳዊ ዝግጅት ታከብረዋለች፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሰረጽ ብላ ስታምን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጋ ነው፤ ሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚሰርጽ ለመሆኑ ጌታችን፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ የሰጠውን ትምህርት በመጥቀስ እንዲህ ይለናል፦ «ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤»
(ዮሐንስ ፲፬፥፲፭-፲፮) «አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።» (ዮሐንስ ፲፬፥፳፮) «ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤»
(ዮሐንስ ፲፭፥፳፮) በማለት በማያሻማ ሁኔታ ጰራቅሊጦስ παράκλητος አጽናኝ- መንፈስ ቅዱስ ከአብ የሚሰርጽ መሆኑን ጌታ ራሱ አስተምሮናል፡፡
በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ውስጥ የተከሰቱ የልዩነት ምእራፎችን ስንመለከት የመጀመሪያው በ፬፻፶፩ ዓ.ም. የኬልቄዶን ጉባኤ ወልድን ሁለት ባህሪ በማለት የተጀመረው ምንፍቅና፥ በ፲፻፶፬ ዓ.ም. መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሰርጻል በማለታቸው ሁለተኛው ልዩነት ሲታከል በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተነሣው የተሐድሶ እንቅስቃሴ «ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤» (፪ኛ ጴጥሮስ ፩፥፳) የሚለውን ቃል ወደ ጎን በመተው መጽሐፍ ቅዱስን እንዳሻቸው የሚተረጉሙ ክፍሎች በየቦታው በመፍላታቸውና ቃሉን በመሸቃቀጣቸው ምክንያት በክርስቶስ ስም ግን ቃሉን የማይጠብቁ አብያተ ክርስቲያናት ነን የሚሉ በብዛት ተስፋፍተው ለእግዚአብሔር ሕዝብ መሰናክል ሆነዋል፡፡
በተለይ በአሁኑ ጊዜ ሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ «ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።» (፩ኛ ዮሐንስ ፬፥፩) በማለት አስቀድሞ እንደጻፈልን አጽናኝ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ አስጭናቂ፥ የሚያረጋጋውን መንፈስ ቅዱስ አንዘፍዛፊና አስጯሂ፥ የሚያበረታውን መንፈስ ቅዱስ አሽመድማጅ፥ እውነትን የሚናገረውን መንፈስ ቅዱስ የሐሰት ቋት፥ አመስጋኙን መንፈስ ቅዱስ ከሳሽ አድርገው የሚያቀርቡ በምእመናን መሀከል ጥላቻንና ጸብን የሚዘሩ በወደቀው በጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ የጥንቆላና የዛር መንፈስ የሚመሩ ሐሰተኛ ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ሲዘባበቱ የሚታዩበት ዘመን ላይ ስለሆን ከአሕዛብና ከመናፍቃን የሐሰት ትምህርት ራሳችንን ለመጠበቅ የሃይማኖት ትምህርታችንን ማጠናከር ግድ ይለናል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና አስተምህሮ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ቀጥተኛ ስለሆነ የአጽናኛችንን የመንፈስ ቅዱስ በረከት በሁላችንም ላይ ሥራውን ይሠራ ዘንድ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ጸንተን በጸሎት ተግተን በምግባር ጎልብተን ከጥላቻና ቂም ርቀን መገኘት ይኖርብናል፡፡
በዕለቱም ቅዱሳን ሐዋርያት፥ እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም እና ሌሎችም አርድእት መቶ ሀያ የሚያህሉ ሰዎች በተገኙበት (ሐ.ሥ.፩፥፲፭) የተፈጸመውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በተመለከተ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነው ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ እንዲህ ብሉ ጽፎልናል፡፡
«በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።» (ሐ.ሥራ ፪፥፩-፬)
የአብ ጸጋ፥ የወልድ ፍቅር፥ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡
የሰላም አምላክ ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ለአገራችንን፥ ለሕዝባችንንና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ፍጹም ሰላምን ይስጥልን፡፡
May be an image of 11 people
ከመ/ር ሸዋንዳኝ አበራ
Close Menu