በዓለ ቅዱስ ገብርኤል

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ  

ታኅሣሥ ፲፰፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? ሳምንቱ እንዴት አለፈ? በሰንበት ቤተ ክርስቲያን ሄዳችሁ መንፈሳዊ ትምህርት እየተማራችሁ እንደሆነ ተስፋችን እሙን ነው፤ ታዲያ በመንፈሳዊ ሕይወታችሁ እንደተማራችሁት ታዛዥ፣ ቅንና ጎበዝ ልጆች መሆን እንደሚጠበቅባችሁ አትዘንጉ! ዘመናዊውስ ትምህርት እንዴት ነው? የዓመቱ አጋማሽ ደርሶ የፈተና ጊዜ ተቃርቧልና በርትታችሁ በመማር የመመዘኛውን ፈተና በሚገባ መሥራት ይቻላችኋል!  ጊዜው ገና ነውና በርቱ! ከአሁኑ ጀምራችሁ ስትማሩ የነበረውን እየከለሳችሁ አጥኑ!

ታዲያ ጥናታችሁ ለፈተና ብቻ መሆን የለበትም፤ እውቀቱንም ለመያዝ ጭምር ሊሆን ይገባል፤ ወደ ፊት መሆን የምትፈልጉትን ለመሆን አሁን ጠንክራችሁ ተማሩ፤ ሁል ጊዜ እንደምንነግራችሁ በመንፈሳዊውም ሆነ በፍልስፍና ዓለም (በዘመናዊ ትምህርትም) ጎበዞች መሆን አለባችሁ፡፡

መልካም! ለዛሬ ልንነግራችሁ የተዘጋጀነው ቅዱስ ገብርኤል ከእሳት ስላዳናቸው ሦስቱ ሕፃናትና እና ይህን በዓል አስመልክቶ ክብረ በዓል ከሚከበርባቸው ቅዱሳን መካናት መካከል አንዱ ስለ ሆነው ስለ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው!

በቅደስት ቤተ ክርስቲያን በዓላት የሚከበሩት አምላካችን ለእኛ ያደረገልንን፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱሳን መላእክት እንዲሁም ቅዱሳን አባቶችና እናቶቸ ከፈጠሪ አማልደው ለእኛ ያደረጉልንን ድንቅ ውለታ ለማስታወስ ነው፡፡ በዓላት በተለያየ መልኩ ይከበራሉ፤ በታኅሣሥ ወር ከሚከበሩ ዓመታዊ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ቅዱስ ገብርኤል በእምነታቸው ጽናት በአማላጅነቱ ከፈጣሪ ተልኮ ከእሳት ያወጣቸው የሦስቱ ሕፃናት የአናንያ፣ የአዛርያና የሚሳኤል ታሪክ አንዱ ነው፡፡

ናቡከደነጾር የተባለ በባቢሎን ነግሦ የነበረው ንጉሥ ጣዖትን እንዲያመልኩ ለሕዝቡ አዋጅን ነገረ፤ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ጣዖት እየተባለ የሚጠራው የሰው ልጅ ራሱ እንጨት እያለዘበ፣ ወይም ደግሞ ድንጋይ እየጠረበ፣ ሐውልት ባመቆም አምላክ እያለ የሚያመልከው ነው፤ ታዲያ ልጆች! እነዚህ ሦስቱ ሕፃናት “እኛ የምናመልከው አምላክ ሰማይና ምድርን በውስጣቸው ያሉትንም የፈጠረ እግዚአብሔርን ነው፤ አንተ ላቆምከው ጣዖት አንሰግድም” አሉት፤ በዚህን ጊዜ “ለጣዖት ካልሰገዳችሁ ከሚነድ እሳት እጨምራችኋለው” በማለት አስፈራራቸው፤ እነርሱም “አንተ ወደ እሳት ብትከተን የምናመልከው አምላክ ያድነናል” አሉት፤ ንጉሡም በዚህ ተናደደና ሦስቱንም ሕፃናት በገመድ አስረው ከሚነደው እሳት እንዲጨምሯቸው አዘዘ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች ይገርማችኋል! ሕፃናቱን አሥረው ከእሳት ከተቷቸው፤ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው፤ ቅዱስ ገብርኤልም ከሚነደው እሳት አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን አዳናቸው፤ በዚያች ቀንም የእግዚአብሔር አምላክነት ተገለጠ፤ የሦስቱ ሕፃናትም እምነታቸውና ጽናታቸው ንጉሡን ጨምሮ ብዙዎችን በእግዚአብሔር እንዲያምኑ አደረጋቸው፤ የቅዱስ ገብረኤልም ተራዳኢነት ታየ፤ የጣዖታት ከንቱነት የዲያቢሎስ ሐሰተኛነትም ተጋለጠ፡፡ (ትንቢተ ዳንኤል ፫፥፫-፴)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ታዲያ ይህ ድንቅ ተአምር የተደረገበትን ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ታኅሣሥ ፲፱ (ዐሥራ ዘጠኝ) ቀን በቅዱስ ገብርኤል ስም በታነጹ አብያተ ክርስቲያናት በድምቀት ይከበራል፤ ከእነዚህም አብያተ ክርስያናት አንዱ የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡

ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል

የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከአዲስ አበባ ከተማ ፬፻፷፩ (አራት መቶ ስድሳ አንድ)  ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምዕራብ ሐረርጌ ይገኛል፤ ታቦቱ በዚህ ቦታ መገኘቱና ቤተ ክርስቲያን የታነጸበት ምክንያት በአገራችን ኢትዮጵያ በዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን  ዮዲት ጉዲት የተባለች ሴት የክርስትናን ሃይማኖት የምትቃወም፣ ቤተ ክርስቲያን በግፍ ስታፈርስ፣ አባቶችንንና ምእመናንንም ለመግደል ስታሳድድ በወቅቱ የነበሩ ክርስቲያኖች  ከአክሱም ከተማ ብዙ ታቦታትንንና ንዋያተ ቅዱሳትን ከጥፋት ለማዳን ይዘው ወደ ዝዋይ ተሰደዱ፡፡

ከዚያም የመከራው ጊዜ ሲያልፍና ዮዲት የተባለችው ጨካኝ ሴት ስትሞት ክርስቲያኖች ወደ ነበሩበት አክሱም ከተማ ተመልሰው በቅዱስ ገብርኤል ስም የተሰየመውን ጽላት (ታቦት) ከነበሩበት ቦታ እንደተቀመጠ ሳያመጡት ሄዱ፤ ከቀድሞ ቦታቸው ሲደርሱ ደግሞ አጡት፤ ከዚያም አባ ሌዊ የተባሉ አባት ልከው እንዲያመጡ አዘዟቸው፤ አባ ሌዊም  ሄደው ታቦቱን ይዘው ሲጓዙ ቅዱስ ገብርኤል ተገልጦ “እኔ ወደማሳይህ ቦታ ይዘህ ሂድ” አላቸው፤ አባ ሌዊም በቅዱስ ገብርኤል እየጠመሩ አሁን ቤተ ክርስቲያኑ ካለበት ቦታ ደረሱና ወደፊት ድንቅ ድንቅ ተአምራት በዚህ ቦታ እንደሚደረግና  በዚያም እንዲያስቀምጡት ነገራቸው፤ እርሳቸውም በክብር ከዋሻ አስቀመጡት፡፡

ከብዙ ዘመን በኋላ ልዑል ራስ መኮንን በቦታው ላይ ሰዎች አልስማማ እያሉ ይጣሉበት ነበርና በቦታው ላይ ሰላም ከሆነ ቤተ ክርስቲያንህን እሠራለው ብለው ለቅዱስ ገብርኤል ተሳሉ ቦታው ላይ ሰላም ሆነ ግጭት ቀረ ልዑል ራስ መኮንንም በተሳሉት መሠረት የቅዱስ ገብርኤልን ቤተ ክርስቲያን ጊዜያዊ ማረፊያ  (መዳረሻ) ሠሩ፤  ሐምሌ ፲፱ ቀን ፲፰፻፹፬ ዓ.ም ታቦቱ ገባ፡፡ በዚሁ ዕለት የዋናው ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ሥራ የመሠረቱ ድንጋይ ተጥሎ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፰፻፹፰ ዓ.ም የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ተፈጽሞ በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቴዎስ ተባርኮ ታቦቱ ገብቷል። ፡፡ (የቤተ ክርሰቲያን መረጃዎች- በዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፪፻፫)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! አሁን ያለውን የቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ያሠሩት ንጉሥ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፤ ምእመናን ተአምራቱን እየሰሙና ከብዙ ቦታዎች እየመጡ በዓሉን ስለሚያከብሩ የቦታ ጥበት መኖሩን በመመልከታቸው ንጉሥ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በ ፲፱፻፶፯ ዓ.ም ብዙ ምእመናንን የሚይዝ ተደርጎ እንዲሠራ አደረጉ፡፡ (የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ወርቃማ ዘመን ገጽ ፪፻፵፫)

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከነገርናችሁ ታሪክ በርካታ ትምህርት እንዳገኛችሁ ተስፋችን እሙን ነው፤ ሦስቱ ሕፃናት በእምነታቸው በመጽናታቸው የታመኑበት እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ ከእሳት እንዳወጣቸው እኛም በእምነታችን ከጸናን፣ በምግባር ከታነጽን መከራ በሚገጥመን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ከጸለይን ቅዱሳን መላእክትን ልኮ ያድነናል፡፡

ሌላው ወደፊ ትልቅ ሰዎች ስንሆንና ሁኔታዎች ሲያመቹን ቤተ ክርስቲያን ማሠራት እንዳለብንም ከነገሥታቱ እንማራለን፤ እንግዲህ ይህንን ድንቅ በዓል ከቤታችን አቅርቢያ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ፣ በበዓላት ወቅት ማድረግ ባለብን ተሳትፎ በጸሎት፣ በዝማሬ፣ አባቶቸ የሚሰጡንን ምክር በመስማት፣ በዓላትን ልናከብር ያስፈልጋል፤ አሁን ያለንበት ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የሠራልንን ውለታ እያሰብን፣ እኛም ለሰዎች መልካም በማድረግ፣ አብዝተን ለአገራችን ሰላም፣ ለሕዝባችን ፍቅር እየጸለይን እናሳልፍ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በረከቱን ያድለን! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!

Close Menu