መስቀል ኃይላችን ነው

መስቀል ኃይላችን ነው

መስቀል በብሉይ ኪዳን የወንጀለኛ መቅጫ የእርግማናን  የሞት ምልክት ሆኖ የቆየ ነበር። ዓመተ ፍዳ በዓመተ ምሕረት ሲተካ የእርግማን፣ የፍርሃትና የሞት ምልክት የነበረው መስቀል፤ የበረከትና የእርቅ፣ የተስፋና የፍቅር፣ የሕይወትና የድኅነት ለመሆን በቅቷል። መስቀል የሕይወት ምልክት መሆኑን የአዳም ልጆች በዘመነ ብሉይ ባይገነዘቡም፤ እስራኤላውያን በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ በማንጎራጎራቸው በእባቦች በመነደፋቸው፤ ሙሴ በነሃስ እባብ ሰርቶ በመስቀል ላይ እንዲሰቅልና ያንን ያዩ ሁሉ እንዲድኑ በማድረግ አስቀድሞ ምሳሌ አሳይቷቸው ነበር።

ይህም በኦሪት ዘኁልቁ ምዕርፍ 21 እንዲህ ተጥቅሷል፤

“ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ። ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ። ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው። በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት። ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን። እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው። ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ። ዘኁ 21፡4-9። (ዮሐንስ 3፡14-15)

ነቢዩ ዳዊት በትንቢት “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው።” (መዝ 59/60፡4) ማለቱ ይታወሳል። ይህም ትንቢት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎልን ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ በታላቅ ተአምራት ስለተገለጠ፤ መስቀል የድኅነታችን ዓርማ መሆኑን ያስገነዝባል።

የቅዱስ ዳዊት ትንቢትም ከብዙ ዓመት በኋላ ተፈጽሞ የመስቀሉ ምልክት ለአብርሃም የሥጋ ልጆች ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ክርስቲያን ለምንባል ለኛም ተሰጠን። ክርስቶስ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት ከሲዖል እስር ቤት፣ ከዲያቢሎስ ግዛት ነጻ አወጣን። በዘመነ ሀዲስ ደኅንነታችን የተፈጸመው በመስቀል ላይ በመሆኑ፤ መስቀል የድል አድራጊነት ዓርማችን ነው እንላለን። ዛሬ በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀሉን ዓርማ በመያዝ ለሕሙማን ፈውስ እንደምትሰጥ እናያለን። አባቶች ካህናትም ጠላትን ድል የሚያደርጉበትን መስቀል በእጃቸው ይይዛሉ ምእመናንም ይባረኩበታል።

በቅድስት ቤተ ክርስቲያንችን፤ ስለ መስቀል በዘወትር ጸሎት መጽሐፍ እንደተጻፈው እንዲህ በማለትም እንጸልያለን፦

“ መስቀል ኃይላችን ነው፤ ኃይላችን መስቀል ነው፤ የሚያጸናን መስቀል ነው፤ መስቀል ቤዛችን ነው፤ መስቀል የነፍሳችን መዳኛ ነው፤ አይሁድ ይክዱታል፤ እኛ ግን እናምነዋለን፤ ያመነው እኛም በመስቀሉ እንድናለን ድነናልም።”

መስቅል/የመስቀሉ ምልክት ከአማኞች ልብና ሕሊና በፍጹም መጥፋት የለበትም። ቅዱስ ጳውሎስ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤” (ገላ.3፡1-2) ብሏል። ስለዚህ ነገረ መስቀሉን ዘወትር ልናሰላስል ይገባል።

ምስጋና ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም፣ ዘወትርም እስከ ዘላለሙ አሜን።

 

 

 

 

 

 

Close Menu