ቀሲስ መላኩ ባወቀ
ጸሎትና ትህትና ( ክፍል አንድ)
ጸሎትና ትህትና አብረው የሚያያዙ ነገሮች ናቸው። ወደ እግዚአብሔር በጸሎት መቅረብ ያለብን በትህትና ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጸሎት በተናገረበት ክፍል በሉቃ ፲፰፥፩_፲፬ ላይ ያስተማረን፥ትህትናን ከጸሎታችን ጋር እንድናዋህድ ነው። ፈሪሳዊው ራሱን በመካብ በሌላው ላይ ጣቱን በመቀሰር « እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤» ይል ነበር። ፈሪሳዊው ከሌላው ለመብለጡ ማስረጃ አድርጎ ያስቀመጠው፥ ጦሙንና አሥራቱን ነበር። ቀራጩ ግን ወደ እግዚአብሔር የቀረበው በተለየ መንገድ ነበር፤ በትህትና ነበር የቀረበው፤ « ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም፥ ነገር ግን፦ አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር።» ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌውን ሲደመድም፥ ከፈሪሳዊው ይልቅ ያ ቀራጭ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ እንደተመለሰ በመናገር እንዲህ ይለናል። «ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል።»
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ እንዲህ ይላል፤ « ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ » ( ፩ ጴጥ ፭፥፭-፮) በትሕትና ውስጥ የእግዚአብሔርን ጸጋ እንቀበላለን። በትህትና ውስጥ ከፍታን እናገኛለን።
እዚህ ላይ ትህትና ያይደሉ ትህትና መሰል ነገሮችን እናንሣ፤ ራስን ማንቋሸሽ ትህትና አይደለም። በእግዚአብሔር ዘንድ የከበርን « ግሩምና ድንቅ» ሆነን የተፈጠርን ነንና። ስለራስ መጠራጠር ትህትና አይደለም። የበታችነት ስሜት ትህትና አይደለም። የበታችነትም ሆነ የበላይነት ስሜት በውስጣችን የሚፈጠረው፥ ከሌላው ለመብለጥ በምናደርገው የፉክክር ስሜት ነው።
ትህትና በአንጻሩ ራስን ከእግዚአብሔር በታች ማስገዛት ነው። እግዚአብሔር ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ እንደሆነ ለሰዎችም ሁሉ ጸጋውን የሚያድል ቸርና ለጋስ አምላክ እንደሆነ ማሰብ ነው። በመሆኑም በሰዎችም ፊት ሆነ ስለራሳችን በምናስብበት ወቅት፥ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ስናደርገው፥ የዚያን ጊዜ ትህትናን እንለማመዳለን። መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ፥ ከሴቶች ከተወለዱት እርሱን የሚያህል እንደሌለ የተነገረለት ቢሆንም፥ እርሱ ግን ለጌታው ራሱን ዝቅ በማድረግ እንዲህ አለ፦ «እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል።» ( ዮሐ ፫፥፴)
ጸሎትና ትህትና ( ክፍል ሁለት)
ትህትናን በጸሎት ሕይወታችን ውስጥ እንዴት መለማመድ እንደምንችል እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ እንዴት ወደ ትህትና እንደሚመራን፥ታላቁ ገዳማዊ አባት ቅዱስ መቃርዮስ በ፲፱ኛው ድርሳኑ ላይ ያስተምረናል። ከዚህ ቅዱስ ትምህርት ውስጥ አራት ዋና ዋና ነጥቦችን እናገኛለን።
በመጀመሪያ፥ የእውነተኛ ትህትና ምንጭ በእግዚአብሔር ላይ ሙሉ በሙሉ መደገፍ ነው። በእግዚአብሔር ላይ የተደገፈ ሰው ኃይሉና ብርታቱ እግዚአብሔር እንደሆነ ይረዳል። በሕይወቱ የሚያያቸው አስደናቂ ነገሮች በሙሉ፥ በእግዚአብሔር የተከናወኑና ከእግዚአብሔር ያገኛቸው እንደሆነ ስለሚረዳ፥ ትምክህቱን የሚያደርገው በራሱ ማንነት ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ ነው። « የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ» ተብሎ እንደተጻፈ፥ በራሱ ዕውቀት ወይም ችሎታ አይመካም።
ሁለተኛ፥ ትሕትናን ገንዘብ ለማድረግ መጋደል አለብን። ቅዱስ መቃርዮስ እንዲህ ይላል። አንድ ሰው፥ የዋህነትን፥ ትህትናን፥ ፍቅርንና ሌሎቹንም የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ከልቡ ሳይፈልግ፥ ምርጫውና ነጻ ፈቃዱን ለማስተካከል፥ መከራን ሳይቀበል ፥ መንፈሳዊ ተጋድሎ ሳያደርግ መንፈሳዊ ውጊያ ሳይዋጋ፥ ዝም ብሎ መጸለይ የፈለገውን ነገር ቢጸልይ፥ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደፈቀደለት፥ የጠየቀውን የጸሎቱን ስጦታ ሊያገኝ ይችላል፤ ነገር ግን በፊት የነበረው ባሕርዩ ሳይለወጥ እንደቀድሞው ነው። የዋሕነት አይኖረውም፥ ምክንያቱም የዋሕነት በሕይወቱ እንዲታይ ጥረት አላደረገም፤ የዋህ ለመሆንም ራሱን አስቀድሞ አላዘጋጀም። እግዚአብሔርን ስላልጠየቀና፥ እንዲኖረውም ተጋድሎ ስላላደረገ ትህትና አይኖረውም። ትኩረት ስላልሰጠው ለዚያ ስላልታገለና በጸሎት ውስጥ የሚገኘውን ይህን ጸጋ ስላልጠየቀ፥ ሰዎችን ሁሉ የመውደድ ሕይወት አይኖረውም።» ቅዱስ መቃርዮስ በዚህ ትምህርቱ የሚያስጨብጠን ሁለት ዋና ዋና ነገር ነው። አንደኛው፥ ትህትናም ይሁን የዋህነት፥ ፍቅርም ይሁን ሌሎችም የመንፈስ ፍሬዎች የሚገኙት ከእግዚአብሔር ስለሆነ፥ በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር መጠየቅ አለብን። በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ስጦታዎች በእኛ ሕይወት ውስጥ እንዲገለጡ ተጋድሎ ማድረግ አለብን። ይህ ተጋድሎ ዝም ብሎ የሰው ጥረት ብቻ አይደለም። በእግዚአብሔር ላይ ከመመካት የሚመነጭ ነው። ይህ ተጋድሎ « በእግዚአብሔር መንገድ » ለመጓዝ የሚደረግ ተጋድሎ ነው። ውሳኔአችንን፥ ቁርጠኝነታችንን እግዚአብሔር ከላይ ከአርያም ሲመለከት፥ ጸጋውን ሙሉ በሙሉ ለእኛ ይሰጠናል። በእግዚአብሔር በመታመን በተጋድሎ ለጸና ሰው « እነዚህን ስጦታዎች ያለምንም ጥረትና ጉልበት፥ ጌታ ራሱ ያደርግለታል።» ሌላው ቀርቶ ከዚህ በፊት በሕይወቱ ሊያገኛቸው ያልቻላቸውን ሥጦታዎች ሁሉ በሕይወቱ ማየት ይጀምራል።
ሦስተኛ፥ በትህትና በሰዎች ሁሉ ፊት መመላለስ አለብን፤ ቅዱስ መቃርዮስ ስለዚህ ሲናገር እንዲህ ይላል። « ትሑት ሰው አይወድቅም፤ ራሱን ከሁሉም በታች ዝቅ ካደረገ፥ የት ይወድቃል? ትእቢተኛ አእምሮ፥ ታላቅ ውርደት ነው። ትህትና ደግሞ ታላቅ የኅሊና ከፍታና ክብር ነው።» ታዲያ ይህን እንዴት ማግኘት እንችላለን? አሁንም ቀደም ሲል ወደ አነሣነው ዋና ነገር እንመለሳለን። እግዚአብሔርን መጠየቅ። መንፈስ ቅዱስ እንዲያስተምረን መጠየቅ አለብን። መንፈስ ቅዱስ የትህትና መንፈስ ነውና እርሱ በእኛ ውስጥ በሙላት ሲያድር ፍሬው በእኛ ሕይወት ውስጥ እንዲገለጥ ያደርጋል።
አራተኛ፥ ሁል ጊዜ እግዚአብሔርንና የእርሱን ትእዛዛት በዓይናችን ፊት ማድረግ አለብን። ለብዙዎች በትዕቢት ውስጥ መውደቅ ምክንያቱ ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ማነጻጸራቸው ነው። « እኔ ከእገሌ የተሻልኩ ነኝ» የሚል መንፈስ ካደረብን፥ ለንስሐ ወይም ራስን ዝቅ ለማድረግ ወይም ለትሕትና ሥፍራ አይኖረንም። በአንጻሩ፥ ቅዱስ እና ልዑል የሆነውን አምላክና ቃሉን ሁል ጊዜ ከፊታችን ካስቀመጥን፥ ራሳችንን የምናስተያየው ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር ይሆናል። ኢሳይያስ በትንቢቱ እንዳመለከተን፥ የእግዚአብሔርን ክብር ዓይናችን ሲመለከት፥ ሁለት ነገሮች ይከናወናሉ። አንደኛ እግዚአብሔርን ማምለክ እንጀምራለን። እንሰግድለታለን፥ ማመስገን እንጀምራለን። ሁለተኛ የእኛ ጉድለት ስለሚገባን ፥ ንስሐ መግባት እንጀምራለን ራሳችንን « ከንፈሮቼ የረከሱ» በማለት፥ እግዚአብሔር በእሳቱ እንዲነካን መለመን እንጀምራለን። ( ኢሳ ፮፥፩-፯ )