መዐዛ ስዋስው ዕጣን ወጼና ትምህርት ከርቤ፣
ለእለ ያጼንዉ ምክረ ወይሰምዑ ዘይቤ፤
የግጥም ስብከት፣ ወይም ይባቤ ።
በዶሮ ሥጋ አምሳል ምስጢሩ እንዲጥም፣
ዐጭሬ ረዥሜ ይባላል ግጥም፣
ዐጭሬው ስውስው ረዥሜው ግስ፣
የሦስት ፊደል ሥጋ የርባ ቅምር ነፍስ፤
ለልጆች እንዲተርፍ ያዋቆች መብል፣
ያቡን ወጥ በሚሉት በተማቲም ቃል፣
ሠርቶ ያቀረበው የግእዝ ወጥ ቤት፣
ላስነባቢው ምሳ ላንባቢው እራት።
ለወጣቶች ኹሉ ከታች ወደላይ፣
ስዋስው እንጂ ነው መንገደ ሰማይ፣
ያዕቆብና ዕዝራ የግዜር ጉበኞች፣
ቀድሞ የሰለሉት ከላይ እስከ ታች።
የስዋስው ትምርት ሥጋውን ዐጥንቱ፣
ባጭሬው ተከቷል ረዥሜነቱ።
ላንቀጹ ፍልሰታ ለርባታው ሑዳዴ፣
የተለቀመውን ጥሩ ፊደል ስንዴ፣
አስተውል ተመልከት ጸሓፊና አንባቢ፣
ያማርኛ ገበዝ የግእዝ ዐቃቢ።
የግእዝን ትምርት አባይን በጭልፋ፣
ቀድቶ የሚጨርስ ማነው ባለተስፋ፣
ቀድቶም ባይጨርሰው ከርሱ ለሚጠጣ፣
ለሚሻገረውም እየተቀናጣ፣
ካዋቆች ራስ ቅል የተከፈለው፣
ፋጋውና ሜዴው እንሆ ይኸው።
ዐዞውም ስንፍና ተማሪ እንዳይነጥቅ፣
ዋነተኛው መምህር ተግቶ ይጠብቅ።
በቀለም ገበያም ጣፊው ብር ሲቀርጥ፣
ፊደሉ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ።
ነቢያት የዘሩት የፊደላት ገብስ፣
ስሙ ልጅ አልቅሶ ቶሎ የሚደርስ፤
ገብሱም ደረቅ ትንቢት ገበሬው ዘመን፣
ዐጭዶና ከምሮ ያሳየን አኹን።
ነዶውም ክምሩም የጎግ ማጎግ ሥጋ፣
ለአዕዋፍ መርዔት ለአራዊት መንጋ፣
እግዜር የወሰነው በሕዝቅኤል አፍ፣
ሰባት ዓመት ብሎ መንፈቅ ሳያተርፍ።
ይህም ሰባት ዓምት ዘመነ ማእረር፣
ከበጉ ዐይንና ቀንድ የሚተባበር፤
የግእዝም ፊደል በሰባትነቱ፣
ከትንቢት ከራእይ ወየው መስማማቱ።
ጊዜ ባስረገጠው በትምርት ዐውድማ፣
ተንጣሎ ነበረ የግእዝ ምርትማ፤
ፈልገን ስላጣን አፋሽ አጎንባሽ፣
ድካማችን ሁሉ እንዳይቀር ብላሽ፣
ከምርቱ ቆንጥረን ይኸው ስዋስው፣
ስሙን ለኋላ ልጅ ዘር ይኹን አልነው።
የዛሬማ ልጆች ብስሉን ግእዝ ቋንቋ፣
ባለመማራቸው አስመሰሉት ጨርቋ፤
ጠጅ ነውም ብለን ብንሰጣቸው ቅሉ፣
እንደ ጌታ ቀምሰው መጠጣት እንቢ አሉ።
አጥብቆ ጠያቂም ሲመረምራቸው፣
ስለ ግእዝ ቋንቋ ይህ ነው ምላሻቸው፤
ምንም ቢንደረከክ የሴም ቋንቋ ፍሕም፣
እንደ ያፌት ኮኛክ ሆድ አያሞቅም፤
ስለ ሥጋ ጥበብ ስለ ደመወዝ፣
ኮኛኩ ይሻላል ከጠጁ ግእዝ።
አብዝቶ ሲጠጡት በሽልም ፊደል፣
ሆድ ስላላሞቀ ጠላ ነው ብንል፣
አያስነቅፈንም በዛሬው ክረምት፤
መስከረም ሲጠባ እንጃ ምናልባት።
የመለኪያውም ስም አፈ ድስቱ ግብጥ፣
ማብረጃ ይባላል ሙቀት እንዳይሰጥ፤
ከማኽልም ገብቶ እንደ ሰው ቢቆም፣
ዐላፊ አሳላፊ መኾን አልቻለም።
ዐላፊም ከሌለው ለቋንቋ ትምርት፣
ራስ የነበረው ይኾናል ዥራት።
ብርሃኑ ጠፍ ኾኖ የግብጥ ጨረቃ፣
ስንኳን ለኛ ይተርፍ ለራሱም አልበቃ፤
እስላሞች ሳይቀሩ የሚስዮን ዠግና፣
ሕዝቡን እንደ ምርኮ ተካፍሎታልና።
የውጭ አገር ጳጳስ ርባታው ሕጹጽ፣
የገንዘብ ሳቢ ዘር ወይም ቦዝ አንቀጽ፤
ዘርፉና ቅጽሉም ባዕድ አታላይ ስም፣
የማይሰማማ ከግእዝ ቀለም።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ