የኅዳር 21 የታቦተ ጽዮን ምስጢርና የአምላክ እናት
በመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
❖ ፈጣሪያችን ክርስቶስን የወለደችልን ቅድስት ድንግል ማርያም በልዑል እግዚአብሔር ትእዛዝ ጥበብና ማስተዋልን በተቀበለ በባስልኤል እጅ በተሠራችው በቃል ኪዳን ታቦት ትመሰላለች (ዘጸ ፳፭፥፱-፳፤ ፴፯፥፩-፲፭)፡፡
❖ በመጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ ምዕራፍ ፪ ቊጥር ፲፪ትን እንደምናነበው፤ ታቦተ ጽዮንን ያገለግሉ የነበሩት የካህኑ የኤሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በሠሩት ታላቅ ኀጢአት ምክንያት እግዚአብሔር አዝኖባቸው የክብሩ መገለጫ የኾነችው ታቦት በፍልስጤማውያን እጅ እንድትማረክ አደረገ፤ ፍልስጤማውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቤንኤዘር ወደ አዛጦን በመውሰድ በድፍረት ከዳጎን አጠገብ አኖሯት፡፡
❖ ነገር ግን ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ወድቆ ተገኘ፤ እነሱም እንደገና ዳጎንን ወደ ስፍራው መልሰው ኼዱ፤ በነጋታው ለማየት ሲመጡ የዳጎን እጅ እግሩ ተቆራርጠው ደረቱ ለብቻው ወድቆ ተገኘ፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽነን ታሪክ ይዞ “የእግዚአብሔር ታቦትንስ በጣዖት ቤት ውስጥ የሚያኖር ማን ነው?” (፪ቆሮ ፮፥፲፮) በማለት የታቦትን ክብር አስተምሮበታል፡፡
❖ ኢትዮጵያዊዉ ሊቅም በሰቈቃወ ድንግል መጽሐፉ ላይ የአምላክ ማደሪያ የኾነችው ታቦት ወደ ፍልስጤም ሀገር ኼዳ ዳጎንን ሰባብራ እንዳጠፋች ኹሉ፤ አማናዊት የጌታ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታን ይዛ ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ኹሉ እየተሰባበሩ መውደቃቸውን እንዲኽ በማለት ገልጿል፤-
“ታቦተ አምላከ እስራኤል ጽዮን ዘነገደት ምድረ ኢሎፍሊ
ወቀጥቀጠቶ ለዳጎን ነፍሳተ ብዙኃን ማህጎሊ
አመ ነገደት ቊስቋመ በኀይለ ወልዳ ከሃሊ
ወድቁ አማልክተ ግብጽ መናብርተ ሰይጣን ሐባሊ
ወተኀፍሩ ኲሎሙ ዘቦሙ አስጋሊ”
(ወደ ኢሎፍሊ ምድር ተማርካ የኼደች የእስራኤል አምላክ የቃል ኪዳኑ ታቦት ታቦተ ጽዮን፤ የብዙዎችን ነፍሳት ያጠፋ ዳጎንን ሰባበረችው፤ በዚች ታቦት የተመሰለች ድንግል ማርያምም ኹሉን ማድረግ ከሚችል ከልጇ ጋር ግብጽ ወደሚባል አገር በኼደች ጊዜ፤የሐሰተኛ ሰይጣን ዘፋኖች የኾኑ የግብጽ ጣዖታት ፈረሱ፤ጠንቋይ አስጠንቋይ ያላቸው ኹሉ ዐፈሩ) በማለት አነጻጽሯል፡፡
❖ በእግዚአብሔር ታቦት ላይ ስለሠሩት ታላቅ የድፍረት ኀጢአት እግዚአብሔር ቀጣቸው ብዙዎቹ ሞቱ፤ ያልሞቱትም በእባጭ ተመቱ፤ የአይጥ መንጋም ምድራቸውን አጠፋባቸው፤ ያን ጊዜ በእግዚአብሔር ታቦት ላይ ምን እናድርግ? ወደ ስፍራው በምን እንስደደው? ብለው በመማከር፤ የሚያጠቡ ቀንበር ያልተጫነባቸው ኹለት ላሞችን በመውሰድ፤ በዐዲስ ሠረገላ ጠምደው እንቦሶቻቸውን (ጥጆቻቸውን) ከቤት ዘግተው በማስቀረት፤ ታቦተ ጽዮንን እጅ መንሻውን በሠረገላው ላይ ጫኑ፤ ያን ጊዜ እነዚኽ ላሞች ጥጆቻቸውን ሳይናፍቁ ወደቀኝ ወደግራ ሳይሉ እምቧ እያሉ ወደ ቤተ ሳሚስ ወደሚወስደው መንገድ ታቦተ ጽዮንን ይዘው ገሠገሡ::
❖ የመልክአ ማርያም ደራሲ የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ የኾነችውን የኻያ መንፈቅ ማለት ዐሥሩ ቃላት የተጻፉባቸው ጽላት የተቀመጡባትን የእግዚአብሔርን ታቦት ጊደሮቹ ከልጆቻቸው ይልቅ በማስበለጥና በመውደድ ይዘዋት ወደፊት እንደነጎዱ፤ እሱም የልዑል ማደሪያ ለኾነችው ለቅድስት ድንግል ማርያም ያለውን ጥልቅ ፍቅር በድርሰቱ ላይ:-
“ማርያም ጽዮን ታቦት ቃለ ጽድቅ መንፈቀ ዕሥራ
ዕጐላት እምዕጐሊሆን ከመ ኪያኪ አፍቀራ
አፍቀርኩኪ አፍቅርኒ እምይእዜ ለግሙራ”
(የኻያ እኩሌታ የሚኾን የእውነት ቃል ማደሪያ ጽዮን ማርያም ሆይ፤ ጊደሮች ከጥጆቻቸው ይልቅ አንቺን እንደአፈቀሩ፤ ወድጄሻለኹና ከዛሬ ዠምሮ ፈጽሞ ውደጅኝ) በማለት ገልጦታል፡፡
❖ ይኽቺም የእግዚአብሔር ታቦት በቤተ ዐሚናዳብ ኻያ ዓመት ተቀምጣለች፤ ከዚያም የሳኦል ዘመን ዐልፎ የእግዚአብሔር ወዳጅ ዳዊት በነገሠ ጊዜ በዐዲስ ሠረገላ አድርገው ከቤተ ዐሚናዳብ አውጥተው በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በነጋሪት፣ በጸናጽል እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ይዘዋት ሲመጡ፤ የእግዚአብሔርን ታቦት ኦዛ በድፍረት በመያዙ እግዚአብሔር ቀሥፎት ወዲያውኑ በታቦቷ አጠገብ ሕይወቱ አልፏል።
❖ ያን ጊዜ ነቢዩ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት ያደረገችውን ተአምራት ተመልክቶ፤ እግዚአብሔር በእርሷ እንዳደረ በማመን በፍርሃት ተውጦ “የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል?” በማለት ለታቦቷ ያለውን ታላቅ ክብር ገልጧል (፪ ሳሙ ፮፥፮-፲)።
❖ በዘመነ ሐዲስም በተመሳሳይ መልኩ ጌታን በማሕፀኗ የተሸከመች የልዑል እግዚአብሔር ማደሪያ አማናዊት ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በኼደች ጊዜ፤ ኤልሳቤጥ ልክ እንደ ዳዊት መንፈስ ቅዱስ መልቶባት፤ የጌታ ታቦት (ማደሪያው) መኾኗን ተረድታ፤ ድምፅዋን አሰምታ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጪ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል?” በማለት ለቅድስት ድንግል ማርያም ያላትን ታላቅ አክብሮት እንደ ዳዊት ገልጣለች (ሉቃ ፩፥፵፫-፵፮)፡፡
❖ ከዚያም ዳዊት ይኽነን ታላቅ ቃል ከተናገረ በኋላ የእግዚአብሔር ታቦት በአቢዳራ ቤት ለሦስት ወር ያኽል እንደተቀመጠች (፪ ሳሙ ፮፥፲)፤ በተመሳሳይ መልኩ የአምላክ ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያምም በካህኑ በዘካርያስ ቤት ለሦስት ወር ተቀምጣለች (ሉቃ ፩፥፶፮)፡፡
❖ ኦዛ ተቀሥፎ ከሞተ በኋላ የእግዚአብሔር ታቦት ወደ አቢዳራ ቤት ገብታ ቤቱ ለሦስት ወር በበረከት እንደተመላ ኹሉ፤ በተመሳሳይ መልኩ ዘካርያስም የመልአኩን ቃል ባለመቀበሉ ከተረገመ በኋላ (ሉቃ ፩፥፳)፤ እውነተኛዪቱ የአምላክ ታቦት ድንግል ማርያም ቤቱ ለሦስት ወር ተቀምጣለች፡፡
❖ እግዚአብሔር በታቦቷ ምክንያት የአቢዳራን ቤት እንደባረከ ኹሉ የዘካርያስንም ቤት በእመቤታችን ምክንያት የባረከው መኾኑን ሊቁ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ በመጽሐፉ ሲገልጽ ‹‹ድንግል በምስጢር የተመላ ታቦትን ኾና ትኖራለች፣ የካህናት ወገኖችም ደስ ይላቸዋል፣ ያከብሯታልም›› በማለት ታቦትነቷን አጒልቶ አስተምሯል፡፡
❖ በተጨማሪም የእግዚአብሔር ታቦት ከቤተ አቢዳራ ወደ ዳዊት ከተማ ስትገባ፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ከደስታው ብዛት የተነሣ የጌታ የክብሩ መገለጫ በኾነችው በታቦቷ ፊት እየዘለለ እንዳመሰገነ ኹሉ (፪ሳሙ ፭፥፲፪-፲፭)፤ አካላዊ ቃልን በማሕፀኗ የተሸከመች የአምላክ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያምም ወደ ተራራማው ሀገር ወደ ይሁዳ ከተማ ወደ ኤልሳቤጥ ቤት በኼደች ጊዜ፤ ታላቁ ነቢይ መጥምቁ ዮሐንስ በእናቱ ማሕፀን ኾኖ ከደስታው ብዛት የተነሣ እየዘለለ አመስግኗል (ሉቃ ፩፥፵፩-፵፭)፡፡
❖ ዳግመኛም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በደስታ ሲያመሰግን አይታ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ብትንቀው እግዚአብሔር ተቈጥቷት በሕይወቷ ዘመን ኹሉ የልጅ ጸጋ እንዳታገኝ በምክነት ቀጥቷታል (፪ሳሙ ፮፥፳-፳፫)፡፡
❖ ይኸውም ማደሪያው የኾነች ታቦቷን በድፍረት ሊነካት የሞከረውን ኦዛን የቀሠፈ፤ ዳግመኛ የጌትነቱ መገለጫ በኾነች በታቦቷ ፊት ያመሰገነ ዳዊትን የናቀች ሜልኮልን በምክነት የቀጣ አምላክ፤ ዛሬም ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀኗ የተሸከመችውን፤ የድንግልና ጡቶቿን የመገበችውን፤ በጀርባዋ ያዘለችውና በደረቷ የታቀፈችውን ቅድስት እናቱን በድፍረት የሚነቅፉ፤ ለዚኽ ድፍረታቸው ንስሓ ድፍረታቸው ንስሓ ካልገቡ የዘላለም ቅጣትና፤ በዚኽ ዓለምም ከድንግል ማርያም አማላጅነት የሚገኘውን ታላቅ በረከት በማጣት እንደ ሜልኮል የበረከትና የጸጋ ምክነት ያጋጥማቸዋል፡፡
❖ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ጽዮንን የሚጠሉ ኹሉ ስለሚደርስባቸው ዘላለማዊ ምክነት በመዝ 128፥5-8 ላይ፦ “ጽዮንን የሚጠሉ ኹሉ ይፈሩ፤ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ፤ በሰገነት ላይ እንደበቀለ ሣር ሳይነቀል እንደሚደርቅ ለሚያጭደው እጁን፤ ነዶዎቹን ለሚሰበስብ ዕቅፉን እንደማይመላ ይኹኑ፤ በመንገድም የሚያልፉ የእግዚአብሔር በረከት በእናንተ ላይ ይኹን በእግዚአብሔር ስም እንመርቃችኋለን አይሉም” በማለት እንደተናገረ ጽዮን የተባለች የድንግል ማርያም አማላጅነት የሚቀዋወሙ ሜልኮል ከእግዚአብሔር ጸጋ የራቁ ናቸው፡፡
❖ ከሊቃውንትም አባ ጽጌ ድንግልና አባ ገብረ ማርያም በማሕሌተ ጽጌ መጽሐፋቸው:-
“እስከ መነነቶ ሜልኮል ቅድመ ታቦት ሕግ ከመ ዘፈነ
ንጉሠ እስራኤል ኪያኪ ዘጸገየ ሥነ
ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ
ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐተኪ ቊርባነ
በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ”
(አንቺን ያስገኘ የእስራኤል ንጉሥ ዳዊት ሜልኮል እስከናቀችው ድረስ በእግዚአብሔር የሕግ ታቦት ፊት እንዳመሰገነ፤ ድንግል ሆይ እኔም በሥዕልሽ ፊት እዘምራለኍ፤ ድንቅ ታምርሽንና የቀረበ መንፈሳዊ ምስጋናሽን የሚንቅ በመላእክትና በሰው አንደበት የተናቀ ይኹን) በማለት አስተምረዋል፡፡
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ (በድጋሚ ፓስት ያረኩት)
ምንጭ፡- ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን ክፍል ሁለት የሚለው መጽሐፌ የተወሰደ
እናንተም በጌታ ፊት የምትለምንልን የብርሃን እናት ቅድስት ድንግል ማርያምን በአስተያየት መስጫው ላይ አመስግኗት።