የምስጋና ሕይወት
የምስጋና ሕይወት የሚኖር ሰው የተደረገለትን ሥራ እና የተፈጸመለትን መልካም ነገር ሁሉ የማይረሳ ለዚህም ምስጋናውን በደስታ የሚገልጽ አዋቂ ሰው ነው። ለእግዚአብሔርና ለሰዎች የሚያቀርበው ምስጋና በልቡ ጽላት ላይ ተጽፎ የተቀመጠ በመሆኑ ምስጋና ከአንደበቱ ፈጽሞ ጠፍቶ አያውቅም።
ለተደረገልን ነገር ሁሉ ምስጋን ስናቀርብ እግዚአብሔርን እየባረክን፣ የሰጠንን ፍቅሩንና ትህትናውን እየገለጽን መሆኑም ልንረዳ ይገባል። እግዚአብሔር በምንም በኩል የተለያዩ መልካም ነገሮችን ካደረገልን ከእግዚአብሔር በተጨማሪ እነዚያን መልካም ነገሮች እንድንቀበል ምክንያት ለሆኑ ሰዎች ምስጋና መስጠት ተገቢ ነው። ስለተደረገልን ሁሉ ለምኜ ወይም ጠይቄ ሳይሆን ወደው ያደረጉት ነው የምንል ከሆነ የራሳችንን የምስጋና ሕይወት ቆም ብለን መመርምር ግድ ይሆናል።
ለተደረገልን ነገር ምን ማድረግ እንደሚገባን መጽሐፍ ቅዱስ በሉቃስ ወንጌል እንዲህ ያስተምረናል፦
“ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥ እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ። ኢየሱስም መልሶ። አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ።” ሉቃስ 17፡15-18
አንዳንዶቻችን ምስጋና በሕይወታችን በሚያጋጥሙን ዋና ዋና ጊዜያት ላይ ብቻ ለእግዚአብሔር ምስጋና እንሰጣለን። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል የሚያዘን እንዲህ ነው። “ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ።” ኤፌሶን 5፡20።
ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቅረበው ሁልጊዜ መሆን አለበት። ይህም ማለት የሕይወት ዘመናችንን ሁሉ ያጠቃልላል። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች በተጻፈው አንደኛው መልእክት፡- “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” 1 ተሰሎንቄ 5፡16-18 ተብሎ ተጽፏል። እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በማለዳ፣ በቀትር እና በማታ እናመሰግነዋለን። እንደ ልበ አምላክ ዳዊትም “ስለቅን ፍርድህ ለምስጋና በሌሊት እነሳለሁ” ልንል ይገባል።
በሰው ሕይወት ውስጥ ሀዘንና ደስታ በተለያየ ጊዜ ያጋጥማል። ቢሆንም በማንኛውም ጊዜ በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም ስለሁሉም ነገር እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባል። ምክንያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮሜ ሰዎች በላከው መልእክቱ “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ሮሜ 8፡28” እንዳለ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ በጎ ነገር ያደርግልናል።
የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን ሁልጊዜ ደስተኞች በመሆን ስለሁሉ ነገር ክርስቶስን እናመስግን። እግዚአብሔር መጥፎ የሆነ ነገር ሁሉ በእኛ ላይ እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ ከሚያጋጥሙን ችግሮች ሁሉ ክብር በመሆን እንደሚጠብቀንና በሥራችን ሁሉ እንደሚያግዘን ፍጹም የሆነ እምነት ይኑረን።
ወስብሃት ለእግዚአብሔር!