የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል የታኅሣሥ ክብረ በዓል

[የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል የታኅሣሥ ክብረ በዓል]
ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ
💥 ቅዱስ ገብርኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲኾን፤ የሚኖርበት ሰማይም ራማ ነው። አርባብ በተባለ ነገድ ላይ የተሾመ በእግዚአብሔር ፊት በባለሟልነት የሚቆም ብርሃናዊ መልአክ ነው (ሉቃ 1:19)።

💥 በግእዝ ገብርኤል፤ በዕብራይስጥ גַּבְרִיאֵל‎ በአረማይክ ܓ݁ܰܒ݂ܪܺܝܐܝܶܠ‎, በቅብጥ Ⲅⲁⲃⲣⲓⲏⲗ ሲባል ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ኃይሌ ነው” ማለት ነው።

💥 ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክን ሰው መኾን ደስ ብሎት ያበሠራት መልአክ ስለኾነ ከግብሩ (ከሥራው) የተነሣ
✍️ “መጋቤ ሐዲስ፣
✍️ ጸዋሬ ዜና ወምክር፣
✍️ መልአከ ፍሥሐ፣
✍️ እግዚእ ወገብር” በመባል ይታወቃል፡፡

💥 ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በድጓው ላይ፦
“ጸዋሬ ዜና ወምክር ገብርኤል
ክቡር ምጽአቶ ለቃል ዜነዋ ለድንግል”
(የብሥራት ዜናና ምክርን የሚሸከም ገብርኤል የክቡር የባሕርይ አምላክ የአካላዊ ቃል አመጣጥን ለድንግል ነገራት) ይላል።

💥 የመልክአ ገብርኤል ደራሲም፦
“ሰላም ለዝክረ ስምከ ዘኢየተረጎም ምስጢር
ባሕቱ ይመስል ብሂለ እግዚእ ወገብር”
(የማይተረጎም ምስጢር አባባሉ ፍቺው ጌታም አገልጋይም የሚመስል ለኾነ ስም አጠራርህ ሰላምታ ይገባል) ይለዋል።

💥 የታኅሣሥ 19 ክብረ በዓሉን ስናስብ ነቢዩ ዳንኤል ለንጉሡ ለናቡከደነጾር ሕልሙን ከተረጐመለት በኋላ ዳንኤልንና ሠለስቱ ደቂቅን በባቢሎን አውራጃ ላይ ከፍተኛ ሹመትን በየደረጃቸው ሹሟቸዋል (ዳን ፪፥፵፰‐፵፱)፡፡

💥 ኾኖም ግን ናቡከደነጾር ቁመቱ ስሳ ክንድ ወርዱ ስድስት ክንድ የኾነውን የወርቁን ምስል አሠርቶ በባቢሎን አውራጃ በዱራ ሜዳ ላይ በማቆም ኹሉም ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰብስበው ሳሉ፤ ዐዋጅ ነጋሪው የዘፈን ድምፅ ሕዝቡ ሲሰሙ ንጉሡ ላቆመው ምስል ተደፍተው እንዲሰግዱ ትእዛዝን የማይቀበሉ ግን በሚነድደው እሳት እቶን እንደሚጣሉ ሲናገር ሕዝቡም አሕዛቡም ለምስሉ ይሰግዱ ይረበረቡ ዠመር (ዳን ፫፥፩‐፯)፡፡

💥 ሦስቱ ሕፃናት አናንያ አዛርያ ሚሳኤል ግን አንሰግድም በማለታቸው “እሉ እደው ዘሤምኮሙ ለግብረ በሐውርተ ባቢሎን አበዩ ሰጊደ ለምስል ዘወርቅ ዘገበርከ” በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምካቸው እነዚኽ ሰዎች ወንዶች ላቆምኸው ምስል አይሰግዱም በማለት ነገሩት።

💥 ናቡከደነጾርም በብስጭትና በቊጣ እንዲመጡ በማዘዙ፤ መጥተው ከፊቱ ሲቆሙ “ላቆምኹት ለወርቁ ምስል አለመስገዳችኊ እውነት ነውን? ባትሰግዱ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችኊ፤ ከእጄስ የሚያድናችኊ አምላክ ማን ነው?” በማለት ሲናገራቸው የሚያመልኩት አምላክ ከሚነድደው እሳት ሊያድናቸው እንደሚችል ገለጹለት።

💥 ርሱም በቊጣ የእቶኑ እሳት ከሚነደው ይልቅ ሰባት እጥፍ ማለት 49 ክንድ አድርገው እንዲያነዱ በማዘዝ አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል፣ ታሥረው እንዲጣሉ በሰራዊቱ ውስጥ ላሉት ኀያላን መመሪያ ስላስተላለፈ፤ ወርዋሪዎቹም ከሰናፊላቸውና ከቀሚሳቸው ከመጐናጸፊያቸው ጋር በእሳቱ ላይ ሲጥሏቸው ከወላፈኑ ከፍተኛነት የተነሣ ወታደሮቹ ተቃጥለዋል (ዳን ፫፥፲፫‐፳፫)፡፡

💥 ያን ጊዜ “ወወረደ መልአከ እግዚአብሔር ወዘበጦ ለነበልባለ እሳት ወረሰዮ ከመ ነፋስ ቆሪር ዘጊዜ ጽባሕ” ይላል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወርዶ በበትረ ብርሃን ቢመታው እንዳረረ ውርጭ ኾኗል፤ ያን ጊዜ ወአንሰሶሰዉ ማእከለ እሳት ወአእኰቱ እግዚአብሔርሀ ወባረክዎ ይላል በእሳቱ ጒድጓድ መኻከልም በመመላለስ እግዚአብሔርንም ፈጽመው አመስግነውታል (መዝሙረ ሠለስቱ ደቂቅ ቊ ፩)፡፡

💥 ይኽም ከእሳቱ መኻከል ሳሉ የተገለጸላቸው አስደናቂ ምስጋና ልዩ የኾነ የነገረ ሥጋዌ ምስጢርን የያዘ እንደኾነ የነገረ ነቢያት ሊቃውንት አስተምረዋል፤ ይኸውም 49 ክንድ ወደ ላይ በወጣው በእሳቱ መኻከል ኹነው ለስድስት ጊዜ ብቻ፦
 “ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለም”

★ (የአባቶቻችን ፈጣሪ እግዚአብሔር ይመስገን፤ የተመሰገነ ነው፤ ለዘለዓለሙም የከበረ ነው) በማለት አመሰገኑ (መዝሙረ ሠለስቱ ደቂቅ ቊ ፳፯‐፴፪)።

 49 ክንድ ወደ ላይ የወጣው እሳት እና እሳት ውስጥ ኾነው 6 ጊዜ “ይትባረክ” (ይመስገን) ያሉት ቢደመር 55 ይኾናል (49+6=55)፤ ይኽም የ5500 ዘመን ምሳሌ ነው፤ ይኽም 5500 ዘመን ተፈጽሞ በ6ኛው ሺሕ አምላክ ሰው ኾኖ ከሲኦል እሳት ነፍሳትን ነጻ እንደሚያወጣ ያመለክታል።

 በመቀጠልም፦
 “ይባርክዎ ኲሉ ግብረ እግዚእ ለእግዚአብሔር ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለም”

★ (እግዚአብሔር የፈጠራችው ፍጥረቶች ኹሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ ርሱ የተመሰገነ ነው ለዘላለሙም ከፍ ከፍ ያለ ነው) እያሉ “ያመሰግኑታል” የሚለውን ቃል ለ 33 ጊዜ ብቻ ያኽል ተናግረዋል (መዝሙረ ሠለስቱ ደቂቅ ቊ ፴፫‐፷፭)፡፡

💥 በሊቃውንቱ ትንታኔ ሠለስቱ ደቂቅ ስድስት ጊዜ መላልሰው መናገራቸው ከ600 ዘመናት በኋላ ምስጉን የኾነው የባሕርይ አምላክ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን ማጠየቃቸው ሲኾን፤ ከዚያው ቀጥለው ደግሞ ሠላሳ ሦስት ጊዜ “ያመሰግኑታል” እያሉ ቃሉን ደጋግመው ማለታቸው፤ ምስጉን የኾነው አምላክ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከተወለደ በኋላ ሠላሳ ሦስት ዓመት በዚኽ ዓለም የሚኖር እንደኾነ ተገልጾላቸው የተናገሩ መኾኑን አስተምረዋል፡፡

💥 ይኽነንም ምስጢር ቀደምት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ሲተነትኑ፦
“…ወተነበዩ ስድስተ ጊዜያተ ለአጠይቆ ከመ እምድኅረ ስድስቱ ምእት ዓመት ይትወለድ ክርስቶስ፡፡ ወእምድኅሬሁ ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር እንዘ ይብሉ ይባርክዎ ኲሉ ግብረ እግዚእ ለእግዚአብሔር ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለም ዘንተኒ ተነበዩ ሠላሳ ወሠለስተ ጊዜያተ ለአጠይቆ ከመ እምድኅረ ተወልደ ክርስቶስ ይነብር ውስተ ዓለም ሠላሳ ወሠለስተ ጊዜያተ ለአጠይቆ”

 (የሚነድደው እሳት ፈጽሞ አልነካቸውም የሚነድደውን እሳት እንደ ውሃ የቀዘቀዘ አድርጎታልና፤ በዚያን ሰዓት እግዚአብሔርን እንዲኽ እያሉ አመሰገኑት፤ የአባቶቻችን ፈጣሪ እግዚአብሔር ይክበር ይመስን፤ ለዘለዓለሙ ክቡር ምስጉን ነው፤ እንዲኽ እያሉ ስድስት ጊዜ ተናገሩ፤ ከስድስት መቶ ዘመን በኋላ ክርስቶስ እንዲወለድ ለማጠየቅ። ከዚኽም በኋላ እንዲኽ እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እግዚአብሔርን ፍጥረቱ ኹሉ ያመሰግኑታል ክቡር ምስጉን ነውና ለዘላለሙ ይክበር ይመስገን እያሉ፤ ይኽነንም ሠላሳ ሦሰት ጊዜ ተናገሩ፤ ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ በዚኽ ዓለም ሠላሳ ሦስት ዓመት እንዲኖር ለማጠየቅ) በማለት ልዩውን ምስጢር አስተምረውናል፡፡

💥 ንጉሡ ናቡከደነጾርም ባለመቃጠላቸው፤ በእሳት ውስጥ ኹነው በማመስገናቸው ተደንቆ አማካሪዎቹን “ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረም? እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መኻከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለኊ፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል” በማለት፤ ስማቸውን ጠርቶ እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ውጡ ሲላቸው ሦስቱ ሕፃናት ከእሳቱ ወጡ፤ ያን ጊዜ መሳፍንቱ ኹሉ የራሳቸው ጠጒር እንዳልተቃጠለ፤ ሰናፊላቸው እንዳልተለወጠ፤ የእሳቱ ሽታ እንኳ እንዳልደረሰባቸው አዩ፡፡

💥 ያን ጊዜ ንጉሡ “በርሱ የታመኑ ባሪያዎቹን ያዳነ የሲድራቅ የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ” በማለት ምስጋናውን አቅርቧል (ዳን ፫፥፳፱‐፴)፡፡ እነዚኽ ሦስቱ ሕፃናት አናንያ፣ አዛርያ፣ ሚሳኤል በእቶነ እሳት ቢጣሉም እንኳ፣ ስለ እምነታቸው ብርታት ምስጢር ተገልጾላቸው በ፮፻ ዘመን አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ፴፫ ዓመት በዚኽ ዓለም ኖሮ ነፍሳትን ከሲኦል እሳት ነጻ እንደሚያወጣ የተገለጸላቸውን ልዩ ምስጋና፣ ዛሬ ኹላችን በቃል ኪዳኗና በምልጃዋ ከገሃነመ እሳት ከምንድንባት ከምትራራልን እናት ከቅድስት ድንግል ማርያም አምላክ ተወልዶ ፈጽሞታልና፤ ታላቁ ሊቅ አባ ጊዮርጊስ በኆኅተ ብርሃን የነገረ ማርያም መጽሐፉ ላይ ሠለስቱ ደቂቅን ዛሬ ባለነው በምእመናን በመመሰል:-

 “መሃኪቶሙ እምውስተ እቶነ እሳት ለአናንያ ወአዛርያ ወሚሳኤል በእደ ቅዱስ ገብርኤል” (በቅዱስ ገብርኤል እጅ አናንያን፣ አዛርያን፣ ሚሳኤልን በእቶን እሳት ውስጥ የራራሺላቸው አንቺ ነሽ) በማለት ምስጢሩን እንደወርቅ አንከብሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ ገልጾታል፡፡

💥 በተጨማሪም ሠለስቱ ደቂቅ በብሉይ ዘመን ያሉ የጻድቃን ምሳሌ፤ በውጪ ያሉት በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ የኃጥአን ምሳሌ፤ የእሳቱ ጉድጓድ የሲኦል ምሳሌ፤ በውስጡ ያሉትን ትቶ በውጪ ያሉትን እንዳቃጠለ ኹሉ በተመሳሳይ መልኩ የእግዚአብሔር ረድኤት ጻድቃንን ይጠብቅ ነበርና ምንም ሲኦል ቢወርዱ በብሉይ ኪዳን ዘመን መከራው እንዳላገኛቸው፤ ኃጥአንን ግን መከራው የማግኘቱ ምሳሌ እንደኾነ መተርጉማን ያመሰጥሩታል፨

[የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አይለየን]
 ከመጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ

Close Menu