ወርኃ ጽጌ

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስደት በወርኃ ጽጌ (ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭)

 

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በወርኀ ጽጌ ወደ ግብፅና ኢትዮጵያ ተሰዳ ነበር ፡፡ ጌታን ፀንሳ በነበረች ጊዜ ለዮሴፍ አንዳንድ ጊዜ እንደ ጽጌረዳ አበባ ቀይ ሁና፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ሮማን አበባ ነጭ ሁና ስትታየው፤  ቀይ የነበረው መልኳ ተለውጦ እንደ ሮማን አበባ ጸዓዳ ነጭ፣ ነጭ የነበረው እንደ ጽጌረዳ ቀይ ሲሆንና የሚያውቀው መልኳ ሲለዋወጥበት ዮሴፍ እየደነገጠ እርሷ መሆኗን ‹‹ማርያም›› እያለ ያረጋገጠጥ ነበር፡፡  (ነገረ ማርያም) ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ‹‹የበኩር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም›› ያለውን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲተረጉመው ‹‹መልኳ እንደ ጽጌረዳና እንደ ሮማን አበባ ይለዋወጥበት ስለነበር በአንድ ዓይነት መልክ አላወቃትም›› ብሏል፡፡ (ማቴ. ፩፥፳፭) ያንን ለማውሳት ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ያለው ወቅት ወርኀ ጽጌ ተባለ፡፡

የእመቤታችን ወደ ግብፅ መሰደድ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችንን ከመውለዷ በፊት ከፅንሰቱ እስከ ዳግም ምጽአቱ ድረስ ስለሚሠራው ሥራ አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት ተነግሯል፡፡ ጌታ ከመወለዱ ሃያ አራት ቀን በፊትም መካነ ልደቱ ቤተ ልሔምን በመላእክት አስጠበቃት፡፡ ጌታችን ሁለት ዓመት ሲሞላው ሄሮድስ ሕፃኑ ክርስቶስን ሊገለው እንደፈለገ መልአኩ ባወቀ ጊዜ  ‹‹ተነስተህ እናቱንና ብላቴናውን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ›› ብሎ  ለዮሴፍ ነገረው፡፡ (ማቴ.፪፥፲፫) እመቤታችንም ከዮሴፍ ጋር ልጇን ይዛ ወደ ግብፅ ተሰደደች፡፡

እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ወደ ግብፅ በተሰደደችበት ጊዜ ብዙ መከራ አጋጥሟታል፡፡ ልጇን ከሞት ለማዳን ብዙ ችግር አይታለች፡፡ የቀን ሐሩር፣ የሌሊት ቊር እየተፈራረቀባት፣ እሾሁ እየወጋት፣ እንቅፋቱ እየመታት፣ መውጫና መግቢያው በማይታወቅ በረሃ ውስጥ ብዙ ተሰቃይታለች፡፡

ሕፃን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ያድን የነበረው ሄሮድስ አራት ወታደሮቹን ከእነጭፍሮቻቸው  ሸልሞ እመቤታችንን ከነልጇ ይዘው ከመጡ የበለጠ ሹመትና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ነግሮ ልኳቸው ነበር፡፡ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ይህንን ሰምቶ ሲነግራቸው እናቱ ማያርም ምርር ብላ አልቅሳለች፡፡ በግብፅ በርሃ ሲጓዙም እመቤታችን ወደ ትዕማን ቤት በሄደች ጊዜ የቤቱ እመቤት ስታያት ‹‹ከየት መጣሽ? ብላ ጠየቀቻት፤ እመቤታችንም መልሳ ‹‹ከይሁዳ ምድር የተሰደድኩ ስደተኛ ነኝ›› አለች፡፡ ‹‹አንቺ ሴት ደረቅ ነሽ መሰለኝ፤ በድርቅናሽ ቤትሽን ትተሽ ትዞርያለሽ፤ እንዳንቺ ያለች ቆንጆ ሴት ከአዳራሽ ወደ ዕልፍኝ ይላል እንጂ ሀገሩን ትቶ ሀገር ለሀገር አይንከራተትም›› ብላም ተተናኮለቻት፡፡ ዮሴፍም ‹‹ለለማኝ ቢኖር ይሰጡታል፤ ባይኖር ደግሞ ካለበት ያድርስህ ይባላል እንጂ እንዲህ እንደ ፍላፃ ልብ የሚወጋ ነገር ምን ያናግርሻል›› ብሎ በመለሰላት ጊዜ ኮቲባ የተባለችው የእመቤቲቱ ገረድ ‹‹ይህ ጀውጃዋ ሽማግሌ ደፍሮ እመቤቴን እንዲህ ይመልስላታል?›› ብላ ዮሴፍን በጥፊ ቃጥታ ሕፃኑን ደግሞ ነጥቃ ጣለችው፡፡ ሕፃኑም እሪ ብሎ ሲያለቅስ እመቤታችን እርሱን ተከተትላ ምርር ብላ አለቀሰች፤ ልታነሳውም በምትሞክርበት ጊዜ ዮሴፍ ‹‹ተይው፤ አምላክነቱ ይገለጽ›› አላት፡፡ በዚያም ሰዓት ትዕማንን ከእነ ገረድዋ መሬት ተከፍቶ ዋጣቸው፡፡ ከዛም ቤት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇና ከዮሴፍ እንዲሁም አብራት ወደ ስደት ከመጣችው ሰሎሜ ጋር ለስድስት ወር ያህል ከተቀመጡ በኋላ ጉዟቸውን ዱር ለዱር አደረጉ፡፡ ይህም እመቤታችን ልጇን እንዳይገሉባት ነበር፡፡(ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)

በበረሃውም ጥጦስና ዳክርስ የተባሉ ሁለት ወንበዴዎችም አገኟቸው፡፡ የጌታን ልብስ ገፈውም ቁመው ሲማከሩ ልጇን የሚገድሉባት መስሏት አለቀሰች፡፡ ሆኖም ግን ጥጦስ ካደረበት ፍቅርና ርኅራኄ የተነሳ ‹‹እነዚህ ሰዎች አሳዘኑኝ! ወደዚህ ቦታ የመጡት ያለ ምክንያት አይሆንምና አንቀማቸው እንተውላቸው›› ብሎ ልብሳቸውን መልሶላቸው ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ ረዳቸው፡፡

የእመቤታችን ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ

እናታችን ድንግል ማርያም ከልጇ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከኢየሩሳሌም ወደ ግብፅ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ  የተሰደደችወው ጌታ አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት ስለተሰደደ እርሱ ተሰዶ አዳም የተቀበለውን መከራ በመቀበል ሊያድነው በመፍቀዱ ነበር፡፡ አዳም ከገነት ከወጣ በኋላ ብዙ መከራ ደርሶበታል፡፡ ወደዚህ ዓለም ሲሰደድ የተቀበለውን መከራ ተቀብሎ ሊያድነው ስለወደደ ወደ ግብፅ ተሰደደለት፤ እንደተበረደ ተበረደለት፤ በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ያጣውን ክብሩን መለሰለት፤ ወደ ክብር ቦታው ገነትም መለሰው፡፡

ግብፃውያንና ኢትዮጵያውያንም ለጌታችን ፍቅር ከምንም በላይ ይሳሱ ስለነበር ተቀብለው አሳረፋቸው፤ አንዳንዶቹም ቤታቸውን በመልቀቅ አስተናገዷቸው፡፡ (ድርሳነ ዑራኤል) አንዳንድ ሰይጣን ያደረባቸው ሰዎች ቢያጋጥሟቸውም ብዙዎቹ ግን ለፍቅሩ በመሳሳት ‹‹ደም ግባቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ያምራል›› ተብሎ የተነገረለትን መልኩን በማየት ብቻ ለማመን በቅተዋል፡፡ በበረሃ ውስጥ የሚኖሩ ሽፍታዎችም ለጌታችን ያሳዩት ርኅራኄና ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ባሳይዋትም ደግነትና ፍቅር እመቤታችን በመደሰቷ ጌታችን ኢትዮጵያን በእመቤታችን ምልጃ ሊጠብቃት ስለፈለገ የዐሥራት ሀገር አድርጎ ሰጣት፡፡ ለፍቅሩ ለሳሱለት ኢትዮጵያውንና ግብፃውያንም ገዳማተ ግብፅንና ገዳማተ ኢትዮጵያን ባረከላቸው፤ ሌሎችንም ገዳማት መሠረተላቸው፡፡

በዚያን ዘመን በምናኔ ይኖር የነበረው ከካም ወገን የሆነው መልከ ጼዴቅም በሥጋ ዘመዶቹ የሆኑትንና የማይዘመዱትን እንዲምርለት መሥዋዕት እያቀረበና እየጸለየ እግዚአብሔርን ይማጸን ነበር፡፡ ሲጸልይም ‹‹አቤቱ ለዲያብሎስ ከመገዛት ለአንተ ወደ መገዛት መልሰኸኛልና ከሀገሬም አውጥተህ አንተን ወደ ማመልክበት ቦታ አምጥተኸኛልና በደሌንም ይቅር ብለኸልኛልና አመሰግንሃለሁ፤ ነገር ግን እኔን ይቅር እንዳልከኝ ዘመዶቼንም ማርልኝ››፡፡ እግዚአብሔርም ልመናውን ተቀብሎ ‹‹ልጄን ወደ ግብፅ በጠራሁት ጊዜ ዘመዶችህን እምርልሃለሁ›› አለው፤ ቃለ ኪዳንም ገባለት፡፡ ዘመኑ በደረሰ ጊዜም እግዚአብሔር የገባለትን ቃለ ኪዳን ለመፈጸም የመልከ ጼዴቅ አባት ወገኖች የካም ዘሮች ናቸውና ጌታችን ወገኖቹን ሊምርለት ወደ ግብፅ ተሰደደለት፤ (ተረፈ ቄርሎስ ፳፭፥፩-፱)፡፡

አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ድርሰቱ ላይ ‹‹አዘክሪ ድንግል ንግደቶ ዘምስሌኪ እንዘ ትጐይዪ ምስሌሁ እምሀገር ለሀገር በመዋዕለ ሄሮድስ ርጉም አዘክሪ ድንግል አንብዐ መሪረ ዘውኅዘ እምአዕይንትኪ ወወረደ ዲበ ገጸ ፍቁር ወልድኪ አዘክሪ ድንግል ረኀበ ወጽምዐ ምንዳቤ ወኀዘነ ወኵሎ ዐፀባ ዘበጽሐኪ ምስሌሁ፤ ርጉም ሔሮድስ በነገሠበት ወራት ከአንቺ ጋር ከአንዱ ሀገር ወደ አንዱ ሀገር የተሰደደውን መሰደድ አሳስቢልን፤ በፊትሽና በልጅሽ ፊት የወረደውን መሪር ዕንባ አሳስቢልን፤ ረኀቡን ጥሙን ችግሩንና ኀዘኑን ያገኘሽንም ልዩ ልዩ መከራ አሳስቢልን›› (ቅዳሴ ማርያም) ሲል ይዘክራል፡፡

ሄሮድስ በነገሠበት ወራት ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር መሰደዷንና በዓይኗ የሚፈሰው ዕንባ ከመብዛቱ የተነሣ በልጇ ፊትም ይወርድ ስለነበረው ዕንባም እንድታሳስብልን የጌታ ፍቃድ ሆነልን፡፡ ይህንም በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን ካህናቱ ሥጋውንና ደሙን አቀብለው ከተመለሱ በኋላ እንጸልያለን፡፡ ምእመናንም ምንም ጾሙ የፈቃድ ቢሆንም የእመቤታችንን ስደት ለማስታወስ ይህን ጾም ይጾሙታል፤ በስሟም ማኅበር መሥርተው፣ ዝክር በመዘከር ያከብሩታል፡፡

 

Close Menu