እንኳን ለበዓለ ሆሣዕና በሰላም አደረሰን፡፡
አርኅዉ ኆኀተ መኳንንት፤
«መኳንንቶች ደጃችሁን ክፈቱ፡፡»
መኑ ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት፤ «ይህ የምስጋና ጌታ ማን ነው?»
እግዚአብሔር አምላከ ኃያላን ውእቱ ዝንቱ ንጉሠ ስብሐት፤ «ይህ የኃያላን አምላክ የምስጋና ንጉሥ እግዚአብሔር ነው፡፡»
ይባእ ንጉሠ ስብሐት ይባእ አምላከ ምሕረት፤ «የምስጋና ጌታ ይግባ የምሕረት አምላክ ይግባ፡፡»
ሆሣዕና፦ የዐቢይ ጾም ስምንተኛና የመጨረሻው ሳምንት፦
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው የጌታችን፥ የመድኃኒታችንና የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኝ ዐበይ በዓላት አንዱ የሆነው የሆሣዕና በዓል ነው፡፡ ሆሣዕና ቃሉ ዕብራይስጥ (הושענות – ሆሻዕኖት) ሲሆን ትርጉሙም አቤቱ አሁን አድን ማለት ነው፡፡
ሆሣዕና የሚለው ቃል ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ በነቢያት ዘንድ የተለመደ ነው፤ ንጉሥ ዳዊትም « ኦ እግዚኦ አድኅንሶ፤ ኦ እግዚኦ ሠርሕሶ፤ ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፡፡ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፥ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፤ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፡፡» (መዝ.፻፲፯፥፳፭-፳፮) በማለት የተቀኘው ይገኝበታል፡፡ ለበዓሉም ሆሣዕና የሚለው ስያሜ የተሰጠው ሕፃናት «ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሣዕና በአርያም በማለት ካዜሙት በመነሣት ሲሆን በሌላም በኩል ሕዝቡ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ድል አድራጊነት ለማብሠርና መልካም ምኞታቸውንም ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው በመውጣታቸው ዕለቱ ጸበርት እሑድ ማለትም የዘንባባ እሑድ (Palm Sunday) ተብሎም ይጠራል፡፡
የክብር ባለቤት የሰላም ንጉሥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታሰረችውን አህያ ፍቱና አምጡ በማለት በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ በመንገዱ ላይ ልብሱንና ዘንባባ እያነጠፉ «ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም» እያሉ እንዳመሰገኑ፥ ጌታም ወደ መቅደስም ገብቶ ነጋዴዎችን የአባቴ ቤት የጸሎት ቤት ነው በማለት በተጻራሪው ያሉትን ገርፎ እንዳስወጣና ድውያንንም እንደ ፈወሰ አራቱም ወንጌላውያን በሰፊው ጽፈውልናል፡፡ (ማቴ.፳፩፥፩-፲፯; ማር.፲፩፥፩-፲፱; ሉቃስ ፲፱፥፳፰-፵፰; ዮሐ.፲፪፥፲፪-፲፱)
በነቢዩ ዘካርያስ «አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።» (ዘካ.፱፥፱) ብሎ በትንቢቱ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ የጽዮን ንጉሥ ጌታችን፥ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅድስት ኢየሩሳሌም በአህያይቱ ውርንጫ ላይ ሆኖ ሲገባ ወቅቱ የአይሁድ ፋሲካን (פֶּסַח ፔሳህ የቂጣ በዓል) ለማክበር ከየአገራቱ ሁሉ የመጡ ብዙ እንግዶችን ኢየሩሳሌም የምታስተናግድበት ወቅት ስለነበር ጌታችን በአህያ ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ ከተማዋ ሲገባ ደቀመዛሙርቱ፥ ሕጻናት፥ ወጣቶችና አረጋውያን በአጠቃላይ ሕዝቡ ሁሉ «ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም» እያሉ በመዘመር ልብሳቸውንና የዘንባባ ዝንጣፊ በሚሄድበት መንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር፡፡ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም ወደ መቅደስ ገብቶ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፏል እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት፡፡» ብሎ በመቅደስ የማይገባ ድርጊት ይፈጽሙ የነበሩትን ሁሉ አስወጣቸው፥ በዚያ የነበሩትን ድውያንንም ፈወሳቸው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፩-፲፯)
አሁንም እኛን ከኃጢአት እስረኝነት ይፈታን ዘንድ አቤቱ አሁን አድነን እያልን በሃገራችንና በሕዝባችን
ውስጥ ሰርጎ የገባውን የሥጋ ሥራ የሆነውን ርኵሰት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥ መለያየት፥ ጎሰኝነት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ ክፋትንና ይህንም የመሰለውን ሁሉ ያጠፋልን ዘንድ በአንድነት ሁነን እንለምነው፡፡ (ገላትያ ፭፥፲፱-፳፩)
ልበ አምላክ ንጉሥ ዳዊት «እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልዐኒ፡፡ የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፤» (መዝ.፷፰፥፱) እንዳለው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጸሎት ቤት እንጂ የወንበዴዎች ዋሻ እንዳትሆን ሁላችንም ተግተን መሥራት ግድ ይላናል ዛሬ ላይ አንዳንዶች በፖለቲካው መስክ ያጡትን መድረክ ከቤተ ክርስቲያን ለማግኘትና ርካሽ የፖለቲካና የዘረኝነት ጽንሰ ሃሳባቸውን ለማሰራጨትና በተለይም አምላካቸው የሆነባቸውን ሆዳቸውን ብቻ ለመሙላት በክርስቲያን ካባ ተሸፋፍነው በየአድባራቱ የተሰገሰጉትንና እንዲሁም ሊሰገሰጉም አጋጣሚን በመጠበቅ ያደቡትን፥ ራሳቸውን የእግዚአብሔር ቤት ጠባቂ በማስመሰል ቤቱን ሊያራቁቱ፥ የእግዚአብሔርንም ሕዝብ እኛ ይልነውን ብቻ መስማት አለብህ በማለት የሚያሰናክሉ የቃየልን፥ የአስቆሮቱ ይሁዳን፥ የአርዮስን ልጆችንና እና የባእዳን ምንደኞችን ከቤተ ክርስቲያናችን ጠራርጎ በማስወጣት ትክክለኛ የጸሎት ስፍራ ብቻ እንዲሆንልን እርሱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለቤት መድኃኒ ዓለም ክርስቶስ ይርዳን፡፡
ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት «አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፥ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ፥» (መዝ.፻፭፥፵፯) እንዳለው ሁላችንም በንጹህ ልብ ሆነን በጾም በስግደትና በጸሎት ወደ አምላካችን ወደ ልዑል እግዚአብሔር ተመልሰን አቤቱ አሁን አድነን በማለት ከዚህ በዘመናችን ከተከሰተው መቅሰፍት ይሰውረን ዘንድ እንማጸነው፡፡ ምንም እንኳን ወደ እርሱ የሚያቀርብ ሥራ ምንም ምንም ባይኖረንም ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለእስራኤል በገባው ቃል መሠረት ይምረን ዘንድ እንለምነው ከበደላችን በንስሓ እንመለስ ስለ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ ነቢዩ ኤርምያስ የኢየሩሳሌምን መጥፎ ነገር እንዳያይ ለምኖህ አንተም የኤርምያስን ምልጃ ተቀብለህ አቤሴሎምን ለስድሳ ስድስት ዓመት በዛፍ ጥላ ከልለህ እንዳዳንከው፥ (ተረፈ ኤርምያስ ፱፥፩-፴) እኛንም ስለቅድስት ድንግል ማርያም፥ ስለቅዱሳን ነቢያት፥ ስለ ጻድቃን ሰማዕታት ብለህ በዓለማችን የመጣውን ኮቪድ19 ወረርሽኝ መቅሰፍት፥ ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላምና አንድነት ጠላት የሆነብንን የዘረኝነት በሽታንና የእርስ በእርስ ግጭትን ፈጽሞ ታጠፋልን ዘንድ እንለምንሃለን፤ አቤቱ አሁን አድነን አቤቱ አሁን አድነን ሆሣዕና ሆሣዕና ሆሣዕና፡፡
ምንባብ፦
ዕብ.፱፥፲፩- መጨረሻ
፩ኛ ጴጥ.፬፥፩-፲፪
ሐ.ሥራ ፳፰፥፲፩- መጨረሻ
ዮሐ.፭፥፲፩-፴፩
የዕለቱ ምስባክ፦
«ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፡፡ ባረክናክሙ እምቤተ እግዚአብሔር፡፡ እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ፡፡» (መዝ.፻፲፯፥፳፮)
«በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤ ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ። እግዚአብሔር አምላክ ነው፥ ለእኛም በራልን፤»
(መዝ.117/118፥26)
«እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ፡፡ በእንተ ጸላኢ፡፡ ከመ ትንሥቶ ለጸላኢ ወለገፋዒ፡፡»
(መዝ.፰፥፪)
«ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት።»
(መዝ.8፥2)
ሆሣዕና ሆሣዕና ሆሣዕና!
አሜን አምላካችን ሆይ አሁን አድነን፡፡
ከመ/ር ሸዋንዳኝ አበራ