ስግደት ሰው አምልኮቱንና ተገዢነቱን ለመግለጥ ራሱን ዝቅ አድርጎ ግንባሩን መሬት በማስነካት ለፈጣሪው ተገዢነቱን የሚገልጽበት ተግባር ነው። ስለዚህ ሥርዓተ ስግደትን ጠንቅቆ ማወቁ መችና እንዴት የስግደት ተግባር ማከናወን እንዳለብን ይረዳናል።
ለክርስቲያኖች ዋና መሠረታችን የእግዚአብሔር ቃል ነውና ስግደት በመጽሐፍ ቅዱስ ምን መሆን እንዳለበት እስቲ እንመልከት፤ “…… ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ …. “ ማቲዎስ 4፡10።
እንግዲህ የጌታ ቃል የሚለን ይህን ነው። አምልኮና ስግደት ለክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ መሆን እንዳለበት ነው። በዮሐንስ ወንጌልም ምን ዓይነት ስግደት መስገድ እንደሚጋባን እንዲህ ያመለክታል።
እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኗል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፣ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ዮሐንስ 4፡ 22-24
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ትምህርት የስግደት ዓይነቶች ሦስት መሆናቸው በተለያዩ መጻሕፍት ተብራርቷል። ሆኖም እዚች ጽሁፍ ላይ የስግደት ዓይነቶች ምን እንደሆኑ በአጭሩ እንመለከታለን። እነርሱም ሰጊድ፣ ከመሬት ወድቆ ግንባርን ምድርን አስነክቶ መነሣት፤ አስተብርኮ፣ ጉልበትን ምድር አስነክቶ መነሣት፤ አድንኖ፣ ራስን ወደታች ዝቅ አድርጎ እጅ መንሳት ናቸው። እንዲሁም ስግደት የአምልኮ፣ የፀጋና የአክብሮት ስግደት ተብሎ ይለያል። ታዲያ እኛ ምን ዓይነት ስግደት፣ ለማንና ለምን እንደምንፈጽማቸው በትክክል እናውቃለን?
ኢያሱም ልብሱን ቀደደ፣ እርሱና የእስራኤል ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ፣ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነሰነሱ። ኢያሱ 7፤ 6። ይህን ሕያው የሆነ የእግዚአብሔር ቃል መሠረት በማድረግ በታቦተ ሕግ ፊት እንሰግዳለን ስለዚህ ወንድሞችና እህቶች ከመሬት ላይ በግንባራችን ተደፍተን ለማን የት ማድረግ እንዳለብን ጠንቅቀን እንወቅ።