ሰሙነ ሕማማት
ሰሙነ ሕማማት ተብሎ የሚጠራው ወቅት ከዐቢይ ጾም መጨረሻ ከሆሣዕና ዋዜማ ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ባሉት ቀናት ውስጥ ያለው ሳምንት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ይህንን ወቅት አስመልክቶ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ‹‹ውእቱ ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፤ እርሱ በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፤›› በማለት የነገረ ሕማማቱን ምሥጢር አስቀድሞ ተናግሮአል፡፡ በዚህም መሠረት በኋለኛው ዘመን እግዚአብሔር ወልድ ስለኛ ስለ ሰው ልጆች ድኅነት ሲል ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋም ነፍስ ነሥቶ በፈቃዱ ሰው ሆኖ በፈቃዱ መከራ መስቀልን ተቀበለ፡፡ በመስቀሉም ላይ ሳለ በፈቃዱ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ በዚህም መሠረት እኛም በእርሱ በአምላካችን የሆነበትን መከራ መስቀሉን ሁሉ የምናስብበት ሳምንት በመሆኑ ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ (ኢሳ.፶፫፥፬፣ማቴ. ፰፡፲፯፣ዮሐ.፩፥፳፱)
ከ፻፹፰-፪፻፴ ዓ.ም የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ የነበረው ቅዱስ ድሜጥሮስ እግዚአብሔር አምላክ በገለጠለት የጊዜ ቀመር (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት ሰሙነ ሕማማት ከዐቢይ ጾም ቀጥሎ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በቀመረ ድሜጥሮስ ዓመታትን በንኡስ በማእከላዊና በዐቢይ ቀመር እየቀመረች አጽዋማት የሚገቡበትን በዓላት የሚውሉበትን ጊዜ ለምእመናን ታሳውቃለች፡፡ ይህን ሳምንት ላቲናውያንና ግሪካውያን ታላቁ ሳምንት ሲሉት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ ሰሙነ ሕማማት በማለት ትጠራዋለች፡፡
በዚህ ሳምንት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በሙሉ ያደረገውን ትድግና ቅዱሳት መጻሕፍት በተለይም ግብረ ሕማማት የተባለው የቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ነገረ ሕማማቱን መከራ መስቀሉን በሰፊው ይናገርለታል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም መድኃኒታችን ክርስቶስ አንዳች በደል ሳይኖርበት በሰውነቱ የደረሰበትን ሕማሙንና መከራውን ሞቱንም እያሰብን ይህንን የዐቢይ ጾምን መጨረሻ ወቅት ወይም ስምንተኛውን ሳምንት በካህናቱ መሪነት ሁላችን ምእመናን በተረጋጋ ኅሊና አብዝተን በመጾም፣ በመጸለይና በመስገድ እንድናከብር ሥርዓትን ሠርታልናለች፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሁሉ ይህንን የጌታን የሕማማት ሰሙን ከተድላ ከደስታ በመራቅ ነገረ መስቀሉን እያሰቡ በኀዘንና በልቅሶ ሆነው የሚያሳልፉት፡፡
የሰሙነ ሕማማት ዕለታት ስያሜዎች
፩. ዕለተ ሰኑይ
ሀ. አንጽሖተ ቤተ መቅደስ፡– በዚች ዕለት መድኃኒታችን ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፡፡ በዚያም በደረሰ ጊዜ ቤተ መቅደሱ የጸሎት የመሥዋዕት ቤት መሆኑ ቀርቶ የንግድ ቤት ሆኖ ቢያገኘው ‹‹ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው ገርፎም አስወጣቸው፡፡ ይኸውም የእርሱ ቤተ መቅደስ የሆነውን ሰውነታችንን ኃጢአት ሰፍኖበት ቢያገኘው ራሱ ተገርፎ ተገፍፎ መከራ መስቀልንም ሁሉ ተቀብሎ ከሰውነታችን ኃጢአትን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ (ሉቃ.፲፱፥፵፮)
ለ. መርገመ በለስ፡– ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግስቱ ከቢታንያ ሲወጣ ተራበ፤ በመንገድም ሲያልፍ ቅጠል ያላት በለስን ከሩቁ ተመለከተ፡፡ ወደ በለሲቱም በቀረበ ጊዜ ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ያንጊዜም ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ከአንቺ ፍሬ የሚበላ አይኑር›› ሲል በለሲቱን ረገማት፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ይህንን ሰሙት፡፡ በዚህም ምክንያት ይህች ዕለት በለሲቱ የተረገመችባት ቀን ናትና መርገመ በለስ ተብላ ትጠራለች፡፡ (ማር.፲፩፥፲፩-፲፬)
በዚህ አገላለጽ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ስትሆን ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባር ነው፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈልጎ አላገኘባቸውም፡፡ እስራኤል፦ ሕዝበ እግዚአብሔር፣ የአብርሃም ዘር መባልን እንጂ የአብርሃምን ሥራ በመሥራት በምግባር በሃይማኖት ጸንተው መኖር አይፈልጉምና ደግ ሰው አልተገኘባቸውም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በለስ የተባለች ኦሪት ናት፡፡ ኦሪት በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛትም አማናዊ ድኅነትን የምታሰጥ ሆና አላገኛትም፡፡ ይሁን እንጂ በእርሷ ድኅነት ባይገኝባትም ‹‹ኦሪትና ነቢያትን ከመፈጸም በቀር ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ›› በማለት ሕገ ኦሪትን ፈጽሟታል፡፡ ከዚህም ባሻገር በለስ የተባለች ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አግኝቷታል፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ለጊዜው ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም በአንቺ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ሲል ነው፡፡ በለሲቱ ስትረገም ፈጥና መድረቋም በአዳም ምክንያት ያገኘን በደል በእርሱ እንደጠፋልን ለመግለጽ ነው፡፡
፪. ዕለተ ሠሉስ
ሀ. የጥያቄ ቀን፡– ዕለተ ሠሉስ የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፤ ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰኞ ዕለት ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ በዚች ዕለት ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋል፡፡ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያቀረቡለት ጥያቄም ‹‹ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለ ትምህርት በማስተማር ተአምራት ማድረግ ገበያ መፍታትን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?›› የሚል ነበር፡፡ እርሱም መልሶ ‹‹እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፣ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፣ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል ከሰው ነው ብንልም ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያከብሩታል እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን›› ተባባሉና ‹‹ከወዴት እንደሆነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፤ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እንደዚሁ እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው፡፡ ልቡናቸው በክፋት ሥራና በጥርጥር ስለተሞላ ነው እንጂይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንደሚያደርግ ሳያውቅ ቀርቶ አልነበረም፡፡ (ማቴ.፳፩፥፳፫-፳፮፣ማር.፲፩፥፳፯-፴፫፣ሉቃ. ፳፥፩-፰)
ለ. የትምህርት ቀን፡– ይህቺ ዕለት ዕለተ ትምህርት ወይም የትምህርት ቀን በመባልም ትጠራለች፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት በማስተማር የተሰጠው ስያሜ ሲሆን ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ መክሮ መመለስ እንደሚገባን ሲገልጽልን ነው፡፡ (ማቴ.፳፩፥፳፰፣፳፭፥፵፮፣ማር.፲፪፥፪፣፲፫፥፴፯፣ ሉቃ.፳፥፱፣፳፩፥፴፰)
፫. ዕለተ ረቡዕ
ሀ. ምክረ አይሁድ፡– ይህቺ ዕለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ፈሪሳውያን ጌታ ኢየሱስን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው ምክር የመከሩበት ምክራቸውንም ያጸኑበትና ሰቅለው ይገድሉት ዘንድ የወሰኑበት ቀን በመሆኗ የአይሁድ የምክር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ ምክራቸው ወቅት ጌታ ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚይዙት በጣም ይጨነቁ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ወቅት በመሆኑ በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ብዙ ሕዝብ ትምህርቱን ያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጠር ከመፍራታቸው የተነሣ ነው፡፡ በዚህ ጭንቀትም ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው ተገኝቶ ጌታ ኢየሱስን እርሱ በመሳም አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ለዚህ ተግባሩም ሠላሳ ብር ወረታውን እንዲከፍሉት ከእነርሱ ጋር በመስማማቱና የምክራቸው ተባባሪ በመሆኑ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ (ማር.፳፮፥፩-፭፣፳፮፥፲፬-፲፮፣ማር.፲፬፥፩-፲፩፣ሉቃ.፳፪፥፩)
ለ. የመልካም መዓዛ ቀን፡– ዕለተ ረቡዕ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ተቀምጦ ሳለ በመላ ዘመንዋ ራስዋን በዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ ዕፍረት ኃጢአትን ይቅር የሚል መልካም መዓዛ ያለው አምላክ መጣ ስትል ውድ የሆነ ዋጋ ያለው ወይም የሦስት መቶ ዲናር ሽቱን ገዝታ ወደ እርሱ በመምጣትና በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው የመልካም መዓዛ ቀንም ትባላለች፡፡ በዚህም ምክንያት ከኃጢአትዋ የተነሣ መልካም መዓዛ ያልነበራት ማርያም እንተ እፍረት በዚህ በጎ ተግባርዋ መልካም መዓዛ ያለት ሆና ወደቤትዋ ተመልሳለች፡፡ (ማቴ.፳፮፥፮፣ዮሐ.፲፪፥፩-፰)
ሐ. የዕንባ ቀን፡– ይህቺው ማርያም እንተ ዕፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በዕንባዋ እግሩን እያጠበች በፀጉሯም እግሩን እያበሰች ስለ ኃጢአቷ ሥርየት ተማጽናዋለችና የዕንባ ቀን ትባላለች፡፡ (ማቴ.፳፮፥፮-፲፫፣ ማር.፲፬፥፫-፱፣ዮሐ.፲፪፥፩-፰)
፬. ዕለተ ሐሙስ
ሀ. ጸሎተ ሐሙስ፡- በዕለተ ሐሙስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የዓለም መድኃኒት የሰው ልጆችንም ልመና የሚቀበል አምላክ ሆኖ ሳለ በዚች ቀን በአትክልቱ ቦታ ገብቶ አይሁድ መጥተው እስከሚይዙት ድረስ ሥጋን የተዋሐደ ፍጹም አምላክ፤ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ለአርአያነት ይጸልይ ስለነበረ ይህች ዕለት ጸሎተ ሐሙስ ተብላ ትጠራለች፡፡ (ማቴ.፳፮፥፴፮-፵፮)
ጌታችን በዚች ዕለት ደቀ መዛሙርቱን አብዝቶ ሲያስተምራቸው ሲመክራቸውም ቆይቶ ነበር፡፡ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ አቅንቶም እርሱ ከአባቱ ጋር አንድ እንደሆነም ነግሮአቸዋል፡፡ ከዚያም ለብቻው ፈቀቅ ብሎ ወዙ እስኪፈስ ከሰገደና ከጸለየ በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲመለስ ተኝተው ስለአገኛቸው ከተኙበት ቀስቅሶ ‹‹አንድ ሰዓት ያህል እንኳን ከእኔ ጋር መትጋት አቃታችሁን? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ›› ብሎአቸዋል፡፡ (ሉቃ.፳፪፥፲፬-፵፮)
ከዚህም በኋላ እርሱ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ስላለው አንድነትና ክብር ለሐዋርያት ካስተማራቸው በኋላ ‹‹ኢየሱስም ይህን ተናግሮ አትክልት ወደ አለበት ሥፍራ ወደ ቄድሮስ ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፤ በዚያም ገባ›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለጸሎት ወደ አትክልቱ ሥፍራ ሄደ፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳም ይህችን ሥፍራ ቀድሞ ጌታ ይወዳት እንደነበር ያውቃልና የካህናት አለቆችንና ጸሐፍት ፈሪሳውያንን እንደዚሁም ሌሎች ፋና ጋሻና ጦርም የያዙትን ጭፍሮች አስከትሎ ወደ እርሱ መጣ፡፡ በዚህም ጊዜ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ተነሡ እንሂድ! እነሆ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል›› አላቸው፤ ከዚያም ወደ እነርሱ ቀርቦ ‹‹መነሃ ተኀሥሡ ማንን ትፈልጋላችሁ›› አላቸው፤ እነርሱም ‹‹ንሕነሰ ነኀሥሥ ኢየሱስሃ ናዝራዌ፤ ናዝራዊውን ኢየሱስን እንፈልጋለን›› አሉት፡፡ (ዮሐ.፲፰፥፩-፯)
ያንጊዜም ይሁዳ ወደ እርሱ ቀርቦ፤ ‹‹መምህር ሆይ ቸር አለህን፤ ሰላም ላንተ ይሁን›› ብሎ ሳመው፤ መሳሙም ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል የትኛው እንደሆነ ለአይሁድ ለይቶ ለማሳየት የተጠቀመው የጥቆማ ምልክት ነበር፡፡ ምክንያቱም የጌታ መልክና የወንጌላዊው የዮሐንስ መልክ ይመሳሰልባቸው ነበርና ለይቶ ሲያሳያቸው ነው፤ ያንጊዜም ጌታችን ‹‹በስኢምኑ ታገብኦ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጠዋለህን?›› ብሎታል፡፡ (ሉቃ.፳፪፥፵፰)
ከዚህም በኋላ ከእርሱ ጋር የመጡት አይሁድና ጭፍሮቻቸው ጌታ ኢየሱስንም በስድስተኛው ሰዓተ ሌሊት ያዙት፡፡ ወደ ሽማግሌዎችና ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት፡፡ ጴጥሮስ ግን ከሩቅ ሆኖ ይመለከት ነበር፤ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ከአንድ ቅጥር ገብቶ ተቀመጠ፡፡ አይሁድም ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ›› ብሏል ብለው ከሰሱት፤ ለዚህም ሁለት የሐሰት ምስክሮችን በክርስቶስ ላይ አመጡ፡፡ ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ ‹‹እንዲህ ሲያጣሉህ አትሰማምን›› አለው፡፡ ጌታችን ግን ምንም አልመለሰለትም፤ ሊቀ ካህናቱም ‹‹ክርስቶስ ተብሎ የተነገረልህ የእግዚብሔር ልጅ አንተ እንደሆንክ ንገረኝ›› አለው፡፡ ጌታችንም ‹‹አንተ አልክ›› አለው፤ ያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ተናዶ ልብሱን ቀደደው፤ ራሱንም በብረት ዘንግ መቱት፤ ይህም ጊዜ የመከራው ጅማሬ ነበር፡፡ (ማቴ.፳፮፥፷፩-፷፬)
ለ. የምሥጢር ቀን፡– ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መካከል አንዱ የሆነው ምሥጢረ ቊርባን የተመሠረተው በዚች ዕለት ነውና ይህቺ ዕለት የምሥጢር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡ መድኃኒታችን ክርስቶስ በዚች ዕለት ኀሙስ ለዓርብ ምሽት በሁለተኛው ሰዓተ ሌሊት ኅብስቱን ባርኮ ለዐሥራ ሦስት ከፈተተ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቶአቸዋል፡፡ ‹‹እንጀራን አንሥቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና፡- እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ፡፡ ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖ ሰጣቸው፤ እንዲህም አለ፡- ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስሰው የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው›› ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ዐሥራ ሦስተኛውን ደግሞ ምንም እንኳን የሚጠቅመው ባይሆንም ለእርሱ የሚቀበለው አድርጎታል፡፡ ‹‹ጥዒሞ አጥዐሞሙ፤ ቀምሶ አቀመሳቸው›› እንዲል፡፡ አንድም አብነት ለመሆን እንደዚሁም ነገ በመልዕልተ መስቀል አሥራ ሦስቱን ሕማማተ መስቀል እቀበላለሁ ሲል ነው፤ ጌታ ይህን አርአያነት ባያደርግልን ኖሮ ዛሬ ካህኑ የጌታን ሥጋና ደም ሳይቀበል አቀብሎ ብቻ በሄደ ነበርና ይህን ሥርዓት ለማስተማር ነው፡፡ (አንድምታ ቅዳሴ ማርያም)
በዚህም መሠረት እኛ ከእርሱ ከመድኃኒታችን ክርስቶስ ጋር፣ አንድ የምንሆንበትን ምሥጢር ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠባት ዕለት በመሆንዋ ይህቺ ዕለት የምሥጢር ቀን ተብላ ትጠራለች፡፡
በዚች ዕለት የቅዳሴ አገልግሎት የሚፈጸም ሲሆን የቅዳሴው ሥርዓትም ዝቅ ባለ ድምጽ በለሆሳስ ነው፡፡ የቃጭሉን አገልግሎት የሚተካው ጸናጽል ሲሆን ይህም አይሁድ ጌታችንን ሊይዙት በመጡ ጊዜ ድምጻቸውን ዝግ አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፤ በቅዳሴውም ጸሎተ ተአምኆ፣ ሥርዓተ ኑዛዜ የማይደረግ ሲሆን ሥርዓተ ቊርባን ግን ይፈጸምበታል፡፡ ይህም የሚደረገው ጌታችን ለእኛ ለሰው ለምእመናን ወገኖቹ የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚችም ዕለት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ቀድመው ራሳቸውን በንስሓ በማዘጋጀት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ይቀበሉባታል፡፡
ሐ. የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፡– ይህቺ ዕለት መድኃኒት ክርስቶስ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ የገለጠባት በእንስሳት ደም ይቀርብ የነበረው መሥዋዕተ ኦሪትም አብቅቶ አማናዊው የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት ለድኅነተ ዓለም የተበሠረባትና የተጀመረባት ዕለት በመሆንዋ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ እየተባለች ትጠራለች፡፡ መድኃኒት ክርስቶስ ‹‹ይህ ጽዋዕ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ›› በማለት እንደተናገረው፡፡ (ሉቃ.፳፪፥፳)
መ. የሕፅበተ እግር ቀን፡– በዚች ዕለት በመጀመሪያው ሰዓተ ሌሊት በመጽሐፍ ‹‹ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበት ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ። ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ እርሱም፦ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም፥በኋላ ግን ታስተውላለህ አለው። ጴጥሮስም የእኔን እግር ለዘለዓለም አታጥበኝም አለው። ኢየሱስም ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ ሆይ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም አለው። ኢየሱስም፦ የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም፥ ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሓን ናችሁ፤ ነገር ግን ሁላችሁም አይደላችሁም አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና፤ ስለዚህ፦ሁላችሁ ንጹሓን አይደላችሁም አለ። እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፥ እንዲህም አላቸው፦ያደረግሁላችሁን አስተውላችኋልን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ፤ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ መምህርና ጌታ ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፥ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና›› ተብሎ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደተጻፈ፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፬-፲፭)
እንግዲህ ከዚህ በላይ ከተጠቀሰው ከወንጌላዊው ቃል እንደምንረዳው ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጥብ ዘንድ በጴጥሮስ ጀምሮአል፡፡ ጴጥሮስ ግን እኔ የአንተ ደቀ መዝሙር ስሆን ባንተ በመምህሬ ልታጠብ አይገባኝም አለ፤ ጌታችንም መልሶ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ እኔ እግርህን ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል ፈንታ የለህም››፡፡ ከዚህም በኋላ ሌሎቹንም ሐዋርያት አጥቦአቸዋል፡፡ አሳልፎ የሚሰጠውን ይሁዳን እንኳን ሳይቀር እግሩን አጥቦታል፡፡ ጌታም ይህንን ያደረገው አሳልፎ እንደሚሰጠው ሳያውቅ ቀርቶ አልነበረም፤ ፍቅርን ሲያስተምረው ለንስሓም ጊዜን ሲሰጠው እንጂ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እኛንም ለሚወዱን ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉን እንኳን በጎ ማድረግ እንደሚገባን ሲያስተምረን ነው፡፡ (ዮሐ.፲፫፥፰)
ጌታችን ተጠምቆ ተጠመቁ ጾሞም ጹሙ እንዳለን ጸልዮ ጸልዩ፤ ሰግዶም ስገዱ ሲለን እንደዚሁም የደቀመዛሙርቱን እግር አጥቦ እናንተም እንዲህ አድርጉ ብሎ አርአያነቱን ሲያሳየን መምህረ ትሕትናነቱን ሲገልጥልን ነው፡፡ ዛሬም ከፓትርያርኩ ጀምሮ ሊቃነ ጳጳሳቱና ካህናቱ ሁሉም በየመዓርጋቸው የምእመናኑን እግር ዝቅ ብለው የሚያጥቡት የጌታን የትሕትና ሥራ ለማሰብ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ይህንን ሥርዓቱን አብነት በማድረግ በዚች ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን የሕፅበተ እግር ሥርዓቱ በሚከናወንበት ጊዜ ዲያቆኑ ውኃን ያቀርባል፤ በቀረበውም ውኃ ላይ ጸሎተ አኰቴት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነብቦ ውኃው በካህኑ ወይም በሊቀ ጳጳሱ እጅ ይባረክና የሕጽበተ እግር ሥርዓቱ ከካህናት እስከ አናጕንስጢስ እንደዚሁም ከወንዶች እስከ ሴቶች ላሉት ምእመናን ሁሉ በካህናቱ እጅ ይከናወናል፡፡
በዚህም ጊዜ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፤ ምሥጢሩም ወይራ ጽኑዕ ነው፡፡ ይህም ክርስቶስ ጽኑ መከራ መቀበሉን የሚያስረዳ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እኛም የእርሱን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ የወይኑ ቅጠል ደግሞ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ሲሆን በዚች ዕለት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ የፈጸመው የኅጽበተ እግር ሥርዓትም ለካህናትና ለምእመናን የትሕትና ሥራን ለማስረዳት መሆኑን ‹‹አንትሙሰ ከመዝ ግበሩ ለቢጽክሙ፤ እናንተም ለባልንጀሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉ›› በማለት ነግሮናል፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም በቀኝና በግራ በመቆም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ምእመናን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ (ማቴ.፳፮፥፳፮፣ዮሐ.፲፫፥፲)
ይቆየን
EOTC MK