የ7ቱ ጊዜያት የጸሎት መጽሐፍ
የንጋት ጸሎት
መዝሙር 5
አቤቱ፥ ቃሌን አድምጥ፥ ጩኸቴንም አስተውል፤
የልመናዬን ቃል አድምጥ፥ ንጉሤና አምላኬ ሆይ፥ አቤቱ፥ ወደ አንተ እጸልያለሁና።
በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ፥ እጠብቃለሁም።
አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፤ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም።
በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ።
ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል።
እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ።
አቤቱ፥ ስለ ጠላቶቼ በጽድቅህ ምራኝ፤ መንገዴን በፊትህ አቅና።
በአፋቸው እውነት የለምና፥ ልባቸውም ከንቱ ነው፤ ጕሮሮአቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ይሸነግላሉ።
አቤቱ፥ ፍረድባቸው፥ በምክራቸውም ይውደቁ፤ ስለ ክፋታቸውም ብዛት አሳድዳቸው፥ እነርሱ ዐምፀውብሃልና።
በአንተ የሚታመኑት ሁሉ ግን ደስ ይላቸዋል፤ ለዘላለሙ ደስ ይላቸዋል፥ እነርሱንም ትጠብቃለህ፤ ስምህንም የሚወድዱ ሁሉ በአንተ ይመካሉ።
አንተ ጻድቁን ትባርከዋለህና፤ አቤቱ፥ እንደ ጋሻ በሞገስ ከለልኸን።
ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን፡ መቼም መች ለዘላለሙ አሜን።
• • •
ሃሌ ሉያ ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ሃሌ ሉያ በየጊዜው፣ በየሰአቱ ምስጋና ለአማኑኤል አምላካችን ይሁን።
አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ ምስጢር አውቅ ዘንድ ጸጋህን ለማግኘት አብቃኝ፤ ያጋንንትን ተንኮላቸውን ግለጥልኝ፣ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት በጸሎት በምለምንህ ጊዜ፣ ከፊቴ አርቃቸው፣ አሳፍራቸው፣ ይህም በምሕረትህ ይሁንልኝ፣ ይደረግልኝ።
እናቴ፣ መመኪያዬ፣ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ ተስፋዬ አንቺ ነሽና የተቀደሰውን ጸጋሽን በመተማመን፣ ወደ ልጅሽ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድታማልጂኝ እለምንሻለሁ። የመለኮታዊ ልጅሽ ቸርነት እንዳይለየኝ ሁል ጊዜ ጸልዪልኝ። ያንቺም ረድኤት እንዲጎበኘኝ ፍቅርሽ እንዲበዛልኝ አድርጊልኝ። የተወደድሽ ርኅርኅት ድንግል ማርያም ሆይ ተስፋዬን በአማላጅነትሽ ላይ አደርጋለሁ፤ በየጊዜውም ሁሉ ጥበቃሽ እንዳይለየኝ የጸጋሽ ብርሃን ይብራልኝ።
አቤቱ የኃያላን አምላክ ዓለም ሳይፈጠር የነበርክ፣ ዓለሙን ሁሉ አሳልፈህ ለዘላለሙ የምትኖር የፍጥረት ሁሉ ጌታ፤ ፀሐይን ለቀን ብርሃን፣ ሌሊትን ለሰው ልጅ ዕረፍት የፈጠርክ፤ አቤቱ አንተን አመሰግናለሁ፤ አንተ ሌሊቱን በሰላም አሳልፈህ ወደቀኑ መጀመርያ ጠዋት ስለአደረስከኝ አመሰግንሃለሁ፤ የዓለሙ ሁሉ ንጉሥ ወደሆንክ ወደ አንተ ልመናዬን አቀርባለሁ። እውነት የሆነውን የእውቀትን ብርሃን ግለጥልኝ፤ የልቦናዬን ፀዳል አብራልኝ፤ መለኮታዊ ብርሃንህን በልቦናዬ ይበራልኝ ዘንድ የጀመርኩትንም መዓልት በጽድቅና በንጽሕና እንዲሁም በመልካም ሥርዓት ፈጽሜ ያለ እንቅፋት በሕይወት እንዳሳልፈው አድርገኝ። አንተ ብሩክ ነህና ክብር፣ ምስጋና፣ ስግደት ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አቀርባለሁ፤ ዛሬም ዘወትርም በየጊዜያቱ ሁሉ እስከዘላለም ፤ አሜን።
የሦስት ሰዓት ጸሎት
መዝሙር 129/130
አቤቱ፥ አንተን ከጥልቅ ጠራሁህ።
አቤቱ፥ ድምፄን ስማ፤ ጆሮህ የልመናዬን ቃል የሚያደምጥ ይሁን።
አቤቱ፥ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፥ አቤቱ፥ ማን ይቆማል?
ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና።
አቤቱ፥ ስለ ስምህ ተስፋ አደረግሁህ፤ ነፍሴ በሕግህ ታገሠች።
ከማለዳው ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ነፍሴ በእግዚአብሔር ታመነች።
ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረት፥ በእርሱም ዘንድ ብዙ ማዳን ነውና እስራኤል በእግዚአብሔር ይታመን።
እርሱም እስራኤልን ከኃጢአቱ ሁሉ ያድነዋል።
ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን፡ መቼም መች ለዘላለሙ አሜን።
• • •
ሃሌ ሉያ ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ሃሌ ሉያ በየጊዜው፣ በየሰአቱ ምስጋና ለአማኑኤል አምላካችን ይሁን።
አቤቱ የምሕረት አምላክ፣ የሁሉ ጌታ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሰጭነት ሁሉን ያስደሰትህ፤ በዚች ሰዓት እንዳማሰግንህ፣ በፊትህ ቆሜ፣ በተቀደስችው በዚች ሰዓት የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ፣ ንጹሓን ቅዱሳን በሆኑት ሐዋርያት ላይ፣ እንደ እሳት ላንቃ ባፈሰስክበት (በዚህች) ሰዓት አመሰግንሃለሁ።
አቤቱ ሰውን የምትወድ አምላክ ሆይ፣ ጽሎቴን ተቀበል፤ ኃጢአቴን አስተሰርይልኝ፤ከሥጋና ከነፍስ እንቅፋት አድነኝ፤በሕይወቴ ሁሉ ለአምልኮትህ እንድገዛ ዝግጁ አድርገኝ። ወደ መንፈሳዊ ጥበብና ገድል ምራኝ፤ ሁል ጊዜ የባሕርይ ሕይወትህ የሚሆን መንፈስ ቅዱስን አሳደርብኝ፤ የሥጋዬን ምኞት ብቻ እንድከተል አታድርገኝ።
አቤቱ፣ ሁሉን የምትገዛ፤ የጌታችን፣ የመድኃኒታችን፣ የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ስጦታ እፈልጋለሁ።
ሰውን የምትወድ አምላክ ሆይ፤ ኃጢአተኛ የምሆን የእኔን የባርያህን ልመና ስማኝ፤ ጸሎቴ ወደፊትህ ትቅረብልኝ፤ ልመናዬ ወደ አንተ ነው።
አቤቱ ጌታዬ አምላኬ ሆይ፤ እኔ በአንተ ተመካሁ፤ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ስጠኝ። ክፉ አሳብና ኃጢአት ከሥጋዬና ከመንፈሴ እንዲርቅ፤ የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ እንድሆን፤ ምሕረትህንና ቸርነትህን እንድሻ፤ ትዕግሥትንና ትሕትናን አድለኝ። የሚመጣብኝን ፈተና ሁሉ፤ በትዕግሥትና በምስጋና እንድቀበል፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን የመስቀል መከራ በማሰብ፤ እንድሸከም አድርገኝ። ቅድስት በረከትህን ለሰውነቴ አጎናጽፋት፤ ይቅርታና ምህረትን በፊትህ እንዳገኝ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በግርማ መለኮት፤ በክበበ ትስብእት፤ በይባቤ መላእክት ለፍርድ በሚመጣበት ሰዓት፤ ከሚፈረድባቸው ጋር እንዳልወገድ ምሕረትህ ይሰጠኝ። ለአንተና ለልጅህ ለክርስቶስ ለባሕርይ ሕይወትህ ለመንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።
የስድስት ሰዓት ጸሎት
መዝሙር 53/54
አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኃይልህም ፍረድልኝ።
አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፤
እንግዶች ቁመውብኛልና፥ ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም።
እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታዬም ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው።
ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል፤ በእውነትህም አጥፋቸው።
ከፈቃዴ እሠዋልሃለሁ፤ አቤቱ፥ መልካም ነውና ስምህን አመሰግናለሁ፤
ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና።
ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን፡ መቼም መች ለዘላለሙ አሜን።
• • •
ሃሌ ሉያ ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ሃሌ ሉያ በየጊዜው፣ በየሰአቱ ምስጋና ለአማኑኤል አምላካችን ይሁን።
አቤቱ ክርስቶስ ፈጣርዬ፤ አዳም በገነት ከሰራው ኃጢአት የተነሳ፣ በስድስት ሰዓት በፈቃዱ በመስቀል ላይ ተቸነከርህ። ስለዚህ በኔ ላይ የተጻፈውን የዕዳ መጽሐፍ ቀደህ፣ ኃጢአቴን ይቅር በለኝ። እኔ ወደ አንተ ወደ ፈጣሪዬ ልመናዬን አቀርባለሁ፤ አንተም ልመናዬን ቸል ሳትል ተመልክተህ ስማኝ። በነግህና በመዓልት፤ በሰርክ እነግርሃለሁ፤አስረዳሃለሁ፤ አቤቱ ቃሌን ሰምተህ፤ ነፍሴን በሰላም አድናት፤ ስለበደሌ ብዛት፣ ወደ አንተ የምቀርብበት በጎ ሥራ የለኝምና።
አምላክን የወለድሽ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ፤ ልመናሽ በልጅሽ በወዳጅሽ ፊት ተወዳጅ ነውና፤ እኔ ኃጢአተኛው በምለምንበት ጊዜ፤ ልመናዬን ሳትጥዪ እርሱ መሐሪ በመሆኑና ስለ እኔ መከራ በመቀበሉ ይቅር እንዲለኝ ለምኚልኝ።
አቤቱ ይቅርታህ ፈጥኖ እንዲደረግልኝ እለምናለሁ፤ አንተ በማእከለ ምድር መድኃኒት ለመሆን የተቀደሱ እጆችህን በመስቀል ላይ ዘረጋህ፤ ስለዚህ ፍጥረት ሁሉ ወደ አንተ ይጮሃል።
ሰውን የምትወድ አምላክ ሆይ፤ ምስጋና ላንተ ይገባል። ለማይጠወልገውና ለማይጠፋው መልክህ እሰግዳለሁ፤ አንተ ቸር ነህና የኃጢአቴን ሥርየት እለምናለሁ።
ዓለሙን የያዝህ፤ የጌታችን፣ የአምላካችን፣ የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት ሆይ፤ አመስግንሃለሁ አከብርሃለሁ። ያንድ ልጅህን መከራ በማሰብ የማቀርበውን ጸሎት ተቀብለህ፤ የበደሌን መጽሐፍ ደምስስልኝ፤ በአዳም ላይ እኩይ ሰይጣን የጻፈውን የእዳ ደብዳቤ፣ በልጅህ መከራ መቀበል እንደደመሰስህ፣ አሁንም በልጅህ መስቀል ጠብቀኝ፤ የተባረከ ዘመን ስጠኝ፤ ያለ ነወር፣ ያለ ነቀፋየሚኖር ሕይወት አድለኝ። ስምህን በማመስገን፤ ላንተ በመስገድ፤ በልጅህ መንበር ፊትከፍርድ ነጻ ሆኜ ከቅዱሳን ጋር ለማመስገን እንፍችል አድርገኝ።
አቤቱ በአንተ ተመክቼአለሁ፤ ለዘላለም እንዳላፍር፤ ጠላቶቼም እንዳይዘባበቱብን፤ እንዳይታበዩብኝም አትተወኝ፤ በፈቃድህ በዚያች በመከራ ሰዓት ሠውረኝ፤ በጽኑ ክንድህ ጠብቀኝ። ለከሐሊነትህ ክብር ምስጋና እንዳቀርብ። አንተ ከዘላለም እስከ ዘላለም በእውነት ብሩክ፤ ምስጉን ነህና ክብር ምስጋና ይግባህ (ይድረስህ)፤ አሜን።
የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት
መዝሙር 85/86
አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ችግረኛና ምስኪን ነኝና።
ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው።
አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ።
የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።
አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና።
አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ።
ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ።
አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም።
ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ፤
አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።
አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።
አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤
ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና።
አቤቱ፥ ዓመፀኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት፤ በፊታቸውም አላደረጉህም።
አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤ መዓትህ የራቀ ምሕረትህም እውነትህም የበዛ፤
ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም፤ ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።
ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋር አድርግ፤ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽንተኸኛልምና።
ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን፡ መቼም መች ለዘላለሙ አሜን።
• • •
ሃሌ ሉያ ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ሃሌ ሉያ በየጊዜው፣ በየሰዓቱ ምስጋና ለአማኑኤል አምላካችን ይሁን።
ክርስቶስ አምላኬ ሆይ፤ ስለ እኔ በዘጠኝ ሰዓት በሥጋ ሞትን የቀመስህ፣ ጥልቅ ኃጢአቴን ግደል።
አቤቱ ጸሎቴ ወደፊትህ ትቅረብ፤ እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ፤ ልመናዬ ወደፊትህ ትድረስ፤ እንደ ዋልህም አድነኝ።
አቤቱ በመስቀል ላይ በተሰቀልኽ ጊዜ፤ ነፍስህን ለባሕርይ አባትህ እንዳማጸንህ፤ በቀኝህ ለተሰቀለው ወንበዴም የገነትን መክፈጫ ሰጥተህ ወደ ገነት እንዳስገባኸው፤ በኃጢአት የወደቅሁ እኔንም በቸርነትህ አስበኝ፤ ነፍሴንና ሥጋዬን አክብረህ ብርሃነ ጸጋህን አብራልኝ። የማትሞት ስጦታህን በረቂቅ ምስጢር አድለኝ። ከበጎነትህ ሥራ ሁሉ በተሳተፍሁ ጊዜ፤ ላንተ ያለማቋረጥ ምስጋና ለማቅረብና የመልክህን ደመ-ግባት አብልጬ ለማየት እንድችል፤ በክርስቶስ አምላኬ በሕይወት ጠብቀኝ።
ስለ እኔ ከድንግል ማርያም በትሕትና ተወልደህ መስቀልን የተሸከምህ፤ ሞትን በመለኮትህ ድል የነሳህ፤ ከሙታን ተለይተህ በመነሣት ትንሣኤህን የገለጥህ፤ ቸር ክርስቶስ አምላኬ ሆይ፤ በእጅህ የፈጠርከኝን እኔን ቸል አትበለኝ፤ ፍቅርህን ግለጥልኝ።
መሐሪ አምላክ ሆይ፤ እናትህ ድንግል ማርያም፤ ስለ እኔ የምታቀርበውን ልመና ተቀብለህ፤ ከሞተ ነፍስ አድነኝ፤ ስለ ቅዱስ ስምህ ብለህ፤ ፈጽሞ አትርሳኝ፤ ኪዳንህንና ምሕረትህን ከእኔ አታርቅ። ስለ ወዳጆችህ ስለ አብርሃም፤ ስለ ይስሐቅ፤ ስለ ያዕቆብ ብለህ ምሕረትሕን ከእኔ አታርቅ። በቀኝህ የተሰቀለውን ወንበዴ እምነት እንደተቀበልህ፤ ከሃጢአቴ ብዛት የተነሳ ለሞት ፍርድ የተዘጋጀሁና በደሌም ብዙ መሆኑን በማውቅ፤ መለኮታዊ ጸጋህን ለማግኘት የምጮህ እኔንም በጌትነትህ በተገለጥህ ጊዜ እንደ እሱ ሁሉ፤ እኔንም በምሕረትህ አስበኝ እላላሁ።
የጌታችን የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት፤ እግዚአብሔር አብ ሆይ፤ አንድ ልጁ የሆነ፤ ቤዛችን ክርስቶስ፤ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ፤ ከመርገመ ኃጢአት በለየን ቅዱስና ቡሩክ ዐቢይ በሆነ ስሙ እማልድሃለሁ። ከኅሊናዬ ምድራዊ ምኞትን አስወግደህ፤ ሰማያዊ ሀብትን አድለኝ፤ ቸርነትህም ይፈጸምልኝ።
መሐሪ ሆይ፤ በዚህች ሰዓት የሚቀርበውን ጸሎት፤ በፊትህ ተወዳጅ አድርገህ ተቀበልልኝ፤ በሕግህና በትእዛዝህ ጸንቼ እንድኖር፤ ደስ የሚያሰኝህንምበጎ ሥራ እንድሠራ የተዘጋጀሁ አድርገኝ፡ ከዚህ ፈራሽ ከሆነው ስጋዬ ተለይታ፤ ነፍሴ ወደ አንተ በምጠራበት ጊዜ፤ በእውነት በጎ ሥራ ሠርተው ደስ ካሰኙህ ቅዱሳን ጻድቃን ጋር ዕድል ፈንታ ስጠኝ፤ ዛሬም ዘወትርም እስከ ዘላለሙ ምስጋና ላንተ ይሁን፤ አሜን።
የአሥራ ሁለት ሰዓት ጸሎት
መዝሙር 140/141
አቤቱ፥ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ስማኝ፤ ወደ አንተ ስጮኽም የልመናዬን ቃል አድምጥ።
ጸሎቴን በፊትህ እንደ ዕጣን ተቀበልልኝ፥ እጅ መንሣቴም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ትሁን።
አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ።
ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው፥ ዓመፃን ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ለኃጢአት ምክንያት እንዳልሰጥ፤ ከምርጦቻቸውም ጋር አልተባበር።
ጻድቅ በምሕረት ይገሥጸኝ፥ ይዝለፈኝም፥ የኃጢአተኛ ዘይት ግን ራሴን አይቅባ፤ ጸሎቴ ገና በክፋታቸው ላይ ነውና።
ኃያላኖቻቸው በዓለት አጠገብ ተጣሉ፤ ጣፋጭ ናትና ቃሌን ይሰማሉ።
በምድር ላይ እንደ ተሰነጠቀ እንደ መሬት ጓል፥ እንዲሁ አጥንቶቻችን በሲኦል ተበተኑ።
አቤቱ ጌታ፥ ዓይኖቼ ወደ አንተ ናቸውና፤ በአንተ ታመንሁ፥ ነፍሴን አታውጣት።
ከሰወሩብኝ ወጥመድ፥ ዓመፅንም ከሚያደርጉ ሰዎች ዕንቅፋት ጠብቀኝ።
እኔ ብቻዬን እስካልፍ ድረስ ኃጢአተኞች በወጥመዳቸው ይውደቁ።
ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን፡ መቼም መች ለዘላለሙ አሜን።
• • •
ሃሌ ሉያ ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ሃሌ ሉያ በየጊዜው፣ በየሰዓቱ ምስጋና ለአማኑኤል አምላካችን ይሁን።
አቤቱ ጌታዬ፤ ወደ አንተ ስጣራ ስማኝ፤ የልመናዬንም ቃል አድምጥ። እንደ በደለው ልጅ በመጸጸት፤ “አቤቱ በሰማይ፤ በፊትህ በደልሁህ” እላለሁ፤ (ሉቃስ 15፣18)
በእውነት ሰውን የምትወድ አንተ በፊትህ ተቀበለኝ፤ ጸሎቴንም እንደ ሠርክ መሥዋዕት ተቀበለኝ፤ እንደ ቀራጩ ሰው በንሥሐ ይቅር በለኝ፤ ጌታዬ ብዬ ለምንሁህ። እኔ ኃጢአተኛ ነኝ፤ ባንተ ዘንድ ግን፤ ብዙ ይቅርታና ምሕረት አለ።
አቤቱ ጌታዬ፤ እንደ ዘማዊትዋ ሴት በጭንቅ አላለቅስም፤ ወይም እንድቀራጩ ወደ አንተ አልጮህም፤ ብቻ በደሌ ብዙ ስለሆነ፤ ምሕረትህ በእኔ ላይ ይብዛ።
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ መድኃኒቴና አምላኬ እንደ ቸርነትህ ብዛት ጸሎቴን ስማ። እኔ ከአሥራ አንደኛው ሰዓት በኋላ የድካማቸውን ዋጋ እንደተቀበሉት ነኝ። ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈት ሆኜ፤ ወደ ኃጢአት ተሰማርቼ ከዋልሁ በኋላ፤ በምሽት ጊዜ ተመልሼ ይቅርታህን ፈለግሁ። ወደ አንተ ቤት ለሚገቡት መድኃኒታቸው ስለ ሆንኽ እጄን ዘርግቼ፤ ወደ አንተ ወደ መድኃኒቴ እጮሃለሁ፤ አንተን በድያለሁና ጸሎቴን ስማ። ባለ ዘመኔ ሁሉ፤ ገንዘቤን በኃጢአት ሥራ አዋልኩት፤ ስለዚህ ልጅህ እባል ዘንድ አይገባኝም፤ ነገር ግን በቸርነትህ ወደ አንተ እንድታቀርበኝ እጣራለሁ። በመከራዬ ጊዜ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ ጸሎቴን ስማኝ፤ እንደ ክፋቴ አትጣለኝ፤ ወይም እነደ ረከሰው ምግባሬ አትናቀኝ፤ በምሕረትህ ብዛት አድነኝ።
ንጹሐን የሆናችሁ ሰማዕታት፤ ስለ ክርስቶስ ብላችሁ ደማችሁን በማፍሰስ ኃጢአታችሁን አስወግዳችሁ ንጹሐን ሰማያዊ መሥዋዕት (መሥዋዕትነትን) በእውነት የተቀበላችሁ እናንተም፤ ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያምና ከነቢያት፤ ከሐዋርያት፤ ከጻድቃን ከምእመናን ጋር ነፍሴን እንዲያጸናት፤ ከመቅሰፍት ከርኩስ ሥራ ሁሉ በቸርነቱ እንዲጠብቃት ጸልዩልኝ።
ይቅር ባይ የሆንህ ጌታና አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ይህን ዕለት በደህና አሳልፈህ እስከ ሠርክ ለምስጋና ስላበቃኸኝ፤ ብርሃኑን በማየት ስለ አስፈጸምከኝ አመሰግንሃለሁ። አሁንም ይህን ምስጋናዬን ተቀብለህ፤ ክፉ ከሚሆን ከሰይጣን ሥራ ጠብቀኝ፤ በኔ ላይ የዘረጋውን ወጥመድ ቆርጠህ፤ ይህችን ሰዓተ ሠርክ ከምትመጣው ሌሊት ጋር አስማምተህ፤ ያለ ሕማም፤ ያለ ድካም፤ ያለ ችግር ነቅቼ በደህና እንዳሳልፋትና ለጸሎት፤ ለምስጋና በየሰዓቱ፤ በየጊዜው ሁሉ ዝግጁ ለመሆን አብቃኝ። ላንተ ምስጋና ክብር፤ ስግደት በእውነት ለዘላለም ይገባሃል።
ከመተኛት በፊት የሚጸለይ ጸሎት
መዝሙር 142/143
አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ በእውነትህ ልመናዬን አድምጥ፥ በጽድቅህም መልስልኝ።
ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባሪያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ።
ጠላትህ ነፍሴን አሳድዶአታል፥ ሕይወቴንም በምድር ውስጥ አጐስቍሎአታል፤ ቀድሞ እንደ ሞተ ሰው በጨለማ አኑሮኛል።
ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።
የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ።
እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች።
አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፤ ነፍሴ አልቃለች፤ ፊትህን ከኔ አትመልስ፥ ወደ ጕድጓድም እንደሚወርዱ አልሁን።
አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ።
አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ።
አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ።
አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት።
በምሕረትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባሪያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው።
ለአብ ለወልድ ወመንፈስ ቅዱስም ምስጋና ይሁን፤ መቼም መች ለዘላለሙ ይሁን።
• • •
ሃሌ ሉያ ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ሃሌ ሉያ በየጊዜው፣ በየሰዓቱ ምስጋና ለአምላካችን ይሁን።
እነሆ መዓልቱ አልፎ፤ ሌሊቱ ተተካ፤ ስለዚህ ቅዱስ ሆይ፤አመሰግንሃለሁ። ወደ አንተ እማልዳለሁ፤ የምትመጣውን ሌሊት ያለፍርሃት እንዳሳልፋት ጠብቀኝ። አንተ እግዚአብሔር የማይታዩትን ጠላቶቼን ምክር ታውቃለህ፤ የሥጋዬም ደካማነት በአንተ በፈጣሪዬ ዘንድ የታወቀ ነው፤ ስለዚህ በቸርነትህ በክንፍህ ጥላ ሸፍነህ እንድትጠብቅኝ፤ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ። ለመሞት እንዳልተኛ ዓይነ ልቦናዬን በመለኮታዊ ቃልህ አብራልኝ። ከጨለማው እንቅልፍ አንቅተህ፤ አንተን ለማመስገን አዘጋጀኝ። አንተ ሰውን የምትወድ ቸር ነህና።
ምንም ጊዜም ቅድስት ድንግል፤ ንጽሕት የሆንሽ የክርስቶስ እናቱ ድንግል ማርያም ሆይ፤ ነፍሴን ያጸናት ዘንድ፤ ጸሎትሽን ወደ ልጅሽ አቅርቢልኝ።
ጌታዬ እብዚአብሔር ሆይ፤ በመዓልት ከሚወረወር፤ በሌሊትም ከሚጣል ክፉ ሥራ ሁሉ ሠውረኝ። አቤቱ ጌታዬ፤ በዚች ዕለት በቃልም ቢሆን፤ በማሰብም ቢሆን፤ በሥራም ቢሁን፤ በግልጥና በሥውር የበደልሁትን ሁሉ ይቅር በለኝ፤ በምሕረትህም አስተሥርይልኝ። ስለ ቅዱስ ስምህ ብለህ ሕይወት ያለው እንቅልፍ ስጠኝ። ከክፉ ነገር የሚጠብቅኝን የሰላም መልአክ ላክልኝ፤ ጸጋህንና ምሕረትህን አብዛልኝ። ላንድ ልጅህ፤ ለጌታችን፤ ለአምላካችን፤ ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ማሕያዊ (አዳኝ) ለሚሆን ለመንፈስ ቅዱስ ሁል ጊዜ ምስጋና አቀርባለሁ፤ አሜን።
የመንፈቀ ሌሊት ጸሎት
ከአይኔ የዕውርነትን እንቅልፍ አስወግደህ፤ በፊትህ ቆሜ ላንተ የሚገባ ምስጋና፤ ከኃጢአትም ሥርየት ልመና አቀርብ ዘንድ ንቃት ስጠኝ። ሰውን ለምትወድ ለአንተ ምስጋና ይሁን።
አቤቱ በሌሊት ስምህም አሰብሁ፤ ሕግህንም ጠበቅሁ፤ ትእዛዛትህንም ፈልጌአታለሁና ሆነችልኝም። በእኩለ ሌሊት አመሰግንህ ዘንድ እነሣለሁ። አቤቱ፤ ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትቅረብ፤ እንደ ቃልህም አድነኝ፤ ሥራትህን አስተምረኽኛንላ። ከንፈሮቼ ምስጋና አወጡ፤ ትእዛዛትህ ጽድቅ ናቸው፤ አንደበትህ ቃልህን ተናገረ፤ ትእዛዛትህን መርጫለሁና።እጅህ የሚያድነኝ ይሁን፤ አቤቱ ማዳንህም ናፈቅሁ፤ ሕግህም ተድላዬ ነው። ነፍሴ ትኑርልኝ ታመሰግንሃለች፤ ፍርድህም ይርዳኝ።
እንደጠፋ በግ ተቅበዘበዝሁ፤ ትእዛዝህን ግን አልረሳሁም፤ ባርያህን ፈልገው።
ሃሌ ሉያ ምስጋና ለእግዚአብሔር፤ ሃሌ ሉያ በየጊዜው፣ በየሰዓቱ ምስጋና ለአምላካችን ይሁን።
ልዩ ሦስት የምትሆን ቅዱስ ሰማያዊ መድኃኒቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ በምድር ቆሜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበልልኝ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን፤መቼም መች ለዘላለሙ፤ አሜን።
ቸር ሰውን የምትወድ፤ እንደ ሰው አንተ፤ እንቅልፍ የሌለብህ ድካምና ስንፍናዬን በዓይንህ አይተህ ትሕትናን አድለኝ፤ ጸሎቴን ተቀበል፤ ለነፍሴም ዕረፍትን ስጥ፤ ስለ ኃጢአቴ ሥርየት የማቀርባት ልማና ከንቱ አትሁን፤ የቀድሞ ፍጥረትህ ነኝና። መላእክት ከቅዱሳን ጋር እንዲያመሰግኑህ እንዳደረግህ፤ እኔም ከእነርሱ ጋር እንዳመሰግንህ ዕድል ፈንታ ስጠኝ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ዛሬም፤ ዘወትርም እስከ ዘላለም ምስጋና ይሁን በእውነት።
የእመቤታችን የማርያም ጸሎት
ሉቃስ 1፤46
ማርያምም እንዲህ አለች።
ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤ የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና። እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።
ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል።
በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤ ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤
ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤ ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን፤ መቼም መች ለዘላለሙ፤ አሜን።
እናቴ፤ ንግሥት ድንግል ማርያም ሆይ፤ ስለ እኔ ጌታዬን ኢየሱስ ክርስቶስን ለምኚልኝ፤ ሁል ጊዜም ጸሎት የማዘወትርና እሱን የመውደድ ሀብት አሰጭኝ።
• • •
አቤቱ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ ከዚህ ዓለም ተለይተው ስለሞቱት አባቶቻችንና እናቶቻችን፤ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ነፍሶች በቸርነትህ በበጎ ዕረፍት ታሳርፋቸው ዘንድ እንለምንሃለን፤ በፊትህ ንጹሕ የሚሆን የለምና። ሰውማ (ሰውስ) በኃጢአት የጨቀየ አይደለምን? ኃጢአትን ብትጠባበቅማ አቤቱ በፊትህም መቆም የሚችል ማን አለ? አቤቱ፤ አንተ በምሕረትህ አስባቸው፤ ስማቸውንም በኢየሩሳሌም ሰማያዊት፤ በሕይወት መጽሐፍ ከቅዱሳን ወገኖች ጋር ሁሉ ጻፍ።
ጸሎተ ሃይማኖት
ሁሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን።
ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።
ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፤ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል።
ሁሉ በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ የለም፤በሰማይም ያለ በምድርም ያለ።
ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ። በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ።
ሰው ሆኖ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን ስለእኛ ተሰቀለ፤ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ።
በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ።ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንንም ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል።ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም።
ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሰረፀ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፤ እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት የተናገረ።
ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን።
የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን።
የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ አሜን።
አባታችን ሆይ፤ በሰማይ የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን። የዕለት እንጅራችንን ስጠን ዛሬ በደላችንንም ይቅር በለን እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል። አቤቱ ወደፈታንም አታግባን ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይል ምስጋና ዛሬ ለዘላለሙ አሜን።
እመቤቴ ማርያም ሆይ፤ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ ሰላም እልሻለሁ፤ በሃሳብሽ ድንግል ነሽ፤ በሥጋም ድንግል ነሽ፤ የአሸናፊ እግዚአብሔር እናት ሆይ፤ ላንቺ ሰላምታ ይገባል። ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽና የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው። ጸጋን የተመላሽ ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ከተወደደው ልጅሽ፤ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ይቅርታን ለምኝልን ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ አሜን።
ይህ ጽሁፍ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በ1954 ዓ.ም. አሳትመውት ከነበረችው “የ7ቱ ጊዜያት የጸሎት መጽሐፍ” የተወሰደ ነው።