ጥምቀት ረቡዕ/ ዐርብ ባይውልም ዋዜማው (ጾመ ገሃድ) ይጾማል ?
†††ጾመ ገሃድ/ጋድ†††
Memeher Mehreteab Assefa Page
ገሃድ ማለት ለውጥ ወይም ልዋጭ ማለት ነው። በርግጥ የቃሉ ፍቺ ከዘይቤው ጋር አይገናኝም። ይህ ማለት “ገሃድ” የሚለውን ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ከተመለከትን “ግልጥ” ማለት ነውና። ለምሳሌ በግልጽ ለማለት በገሃድ እንላለን። የቃሉን ፍቺ በዚህ ገትተን ወደ ጾምነቱ ስንመለስ ቤተ ክርስቲያናችን ከሏት አጽዋማት አንዱ “ጾመ ገሃድ” መሆኑን እናገኛለን።
የገሃድ ጾም የሚጾመው በጥምቀት ዋዜማ ብቻ ነው። አንዳንድ ሰዎች ግን ባለማወቅ የልደትን ዋዜማም “ገሃድ” ብለው ይጾማሉ። ነገር ግን የልደት (ገና) ዋዜማ መጀመሪያውኑ በጾመ ነቢያት ውስጥ ያለ በመሆኑ ድርብ ጾም የለምና ለብቻው አይጾምም። በተለምዶ ግን ጾመ ነቢያትን ሳይጾሙ ቆይተው ዋዜማዋን ብቻ የሚጾሙ አሉ። ጾመ ገሃድ ግን የጥምቀት ዋዜማ ብቻ መሆኑን መረዳት ይገባናል። ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ በሚውሉበት ጊዜ ቀድመው ያሉት ማክሰኞና ሐሙስ የፍስክ ቀንነታቸው ወደ ጾምነት ተለውጦ ይጾማሉ። በነሱ ለውጥ ጥምቀት የሚውልባቸው የጾም ቀናት (ረቡዕና ዐርብ) የፍስክ ቀን ሆነው ይከበራሉና።
ገሃድ የረቡዕና ዐርብ ለውጥ ነው ብለናል። ነገር ግን ጥምቀት በሌላም ቀን ቢውል የጥምቀት ዋዜማ ይጾማል። በዓለ ጥምቀት እሑድ ቢውል ቅዳሜ ጥሉላት አይበላም። ጥምቀት ሰኞ ቢውል እሑድ ጥሉላት አይበላም። እንደሌሎች የአጽማዋት ቀናት እህልና ውሃ ግን አይጾሙም። አንዳንድ ሰዎች ግን ጥምቀት ሰኞ ሲውል ከቅዳሜና እሑድ አዋጥተው በመጾም ቅዳሜና እሑድ ጥሉላት አይበላባቸውም ይላሉ። ነገር ግን “ገሃድ” አንድ ስለሆነ (ስንክሳር ጥር 10 “ሰላም ለዕለት ዋሕድ ዘስሙ ገሃድ” እንዲል) ጥምቀት ሰኞ ሲውል ቅዳሜን መጾም አጉል የገባ ልማድ ነው።
ምንጭ፦ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ታላቁ ያዘጋጁት “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” መጽሐፍ፤ ገጽ 130።