ፀሀይ የማትጠልቀው!

ፀሀይ የማትጠልቀው!
የከለንበስ  ሰማይ ፤ ደመና አጥቁሮታል
ቀኑ ቢጋመስም ፤ ጭጋግ ሸፍኖታል።
የደመናው ድባብ ፤ ሀሳቤን በትኖ
ናፍቆት እየጫረ ፤ ልቤን አብከንክኖ
በሚንጠባጠበው ፤ በካፊያው ወጨፎ
አየር ላይ አስቀረው ፤ ትዝታዬን ጠልፎ።
የሚጨሰው መሬት ፤ ጠረኑ አስጨነቀኝ
ፍቅሬን አጋጋመው አንተን አስናፈቀኝ።
ትልቁም ጎዳና ፤ ከሰመ ውበቱ
………………ፈዘዘ ድምቀቱ
መንገደኛ ሞልቶ ፤ ሰው በመታጣቱ።
መንገዱ ያለሰው  ፤ ብቻውን  መቅረቱ
ሳዬው  አስጨነቀኝ ፤ አቤት ማስፈራቱ!
በደመናው ፈረስ…
    በአየሩ ተጭነህ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ
እጠብቅሀለሁ …
      ከበራፌ ቁሜ ፤ አንተ እስክትመጣልኝ።
ቶሎ ስትደርስልኝ …
      ከአጠገቤ ስትሆን ፤ ጎ’ኔ ስትቆምልኝ
የቀኑን ጨለማ ፤ በአይንህ  ስትገፍልኝ
ያኔ ነው…………………………
የጥርስህ ፈገግታ ፤ ጭጋግ የሚገልጠው
በረዶው የሚተን ፤ ውርጩ የሚሞቀው።
ያኔ ነው…………………………………
ህይወት የምትረካ ፤ የምትፈነድቀው
ጨረቃ ደምማ ፤ ፍቅር የምትደምቀው
አንተ ስትመጣ ነው ፤ ፀሀይ የማ’ጠልቀው ።
  ፍቅርተ  7/29/16
Columbus Ohio
Close Menu