የሰካራም ፀሎት

የሰካራም ፀሎት
የሚወላገዱ እግሮቹን  አፅንቶ
የሚወናጨፉ እጁቹን  ዘርግቶ
ግንባሩን ወደ ላይ …
        ወደ አምላኩ አቅንቶ።
በኮልታፋ አንደበት ፤ አምላኩን ተጣራ
ተፀፅቶ ጮህ …
      ፀሎቱ እንዲሰምር ጌታው እንዲራራ
“ይቅር በለኝ ” …
          አለ ከሀጢያቱ ሊጠራ።
” ጨርቄን ማቄን ጥዬ…
          እኔም ልከተልህ ፤ ከነጴጥሮስ ጋራ
አብሬህ ልታደም ፤ መንገድክን ልጋራ
አልደፍርም ለጎንህ…
      በቀኝህ አልልም ፤ አኑረኝ በግራ።
የሰካራም አምላክ ፤ እውነተኛው ዳኛ
እድሜዬ እንዳታልቅ ፤ ስጠጣ መናኛ
ለአይን ሳይከሰት
          ከሚንቆረቆረው ፤ ከማርህ ወለላ
ታምርህ ሲገለፅ…
        ጠጅህን መፅውተኝ ፤ በቃና ገሊላ።”
“እንደ ማለዳዬ…ንጋት እንደ ቸርከኝ
በረፋዴም ድረስ…..
                  ሳልወድቅ አስተካክለኝ
ጌታ ሆይ ደግፈኝ
የመሸበት ጩኸት….
      የሰካራም ፀሎት…ብለህ አትለፈኝ”
 
ፍቅርተ ፀጋይ
2017
Close Menu