ፀሀይ የማትጠልቀው!
የከለንበስ ሰማይ ፤ ደመና አጥቁሮታል
ቀኑ ቢጋመስም ፤ ጭጋግ ሸፍኖታል።
የደመናው ድባብ ፤ ሀሳቤን በትኖ
ናፍቆት እየጫረ ፤ ልቤን አብከንክኖ
በሚንጠባጠበው ፤ በካፊያው ወጨፎ
አየር ላይ አስቀረው ፤ ትዝታዬን ጠልፎ።
የሚጨሰው መሬት ፤ ጠረኑ አስጨነቀኝ
ፍቅሬን አጋጋመው አንተን አስናፈቀኝ።
ትልቁም ጎዳና ፤ ከሰመ ውበቱ
………………ፈዘዘ ድምቀቱ
መንገደኛ ሞልቶ ፤ ሰው በመታጣቱ።
መንገዱ ያለሰው ፤ ብቻውን መቅረቱ
ሳዬው አስጨነቀኝ ፤ አቤት ማስፈራቱ!
በደመናው ፈረስ…
በአየሩ ተጭነህ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ
እጠብቅሀለሁ …
ከበራፌ ቁሜ ፤ አንተ እስክትመጣልኝ።
ቶሎ ስትደርስልኝ …
ከአጠገቤ ስትሆን ፤ ጎ’ኔ ስትቆምልኝ
የቀኑን ጨለማ ፤ በአይንህ ስትገፍልኝ
ያኔ ነው…………………………
የጥርስህ ፈገግታ ፤ ጭጋግ የሚገልጠው
በረዶው የሚተን ፤ ውርጩ የሚሞቀው።
ያኔ ነው…………………………………
ህይወት የምትረካ ፤ የምትፈነድቀው
ጨረቃ ደምማ ፤ ፍቅር የምትደምቀው
አንተ ስትመጣ ነው ፤ ፀሀይ የማ’ጠልቀው ።
ፍቅርተ 7/29/16
Columbus Ohio