የኦርቶዶክስ ነገረ መለኮትና የፕሮቴስታንት ነገረ መለኮት ልዩነት
( በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ)
( ክፍል አራት)
እምነትና ሥራ በመዳን ታሪክ ውስጥ
( Faith and Work in Salvation Story)
ማሳሰቢያ፦ ስለ ነገረ ሰብእ እንጽፋለን ያልነውን ለጊዜው አቆይተነው፥ እምነትና ሥራ በመዳን ውስጥ ስላላቸው ሚና እንነጋገራለን።
በኦርቶዶክስ ነገረ መለኮትና በፕሮቴስታንት ነገረ መለኮት መካከል ከሚታዩት ልዩነቶች አንዱ የእምነትና የሥራ ግንኙነት ነው። ለፕሮቴስታንት አስተምህሮ የእምነት አእማድ የሆኑት፥ ጸጋ ብቻ፥ እምነት ብቻ፥ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ፥ ክርስቶስ ብቻ የሚሉት አስተምህሮዎች ናቸው። በኦርቶዶክሳዊ ነገረ መለኮት ውስጥ ግን ፥ እምነትና ሥራ፥ መጽሐፍ ቅዱስና ትውፊት፥ ክርስቶስ እና ቤተ ክርስቲያን የማይነጣጠሉ ናቸው። ለዛሬው በእምነት እና በሥራ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳየት፥ አበው « ነገር ከሥሩ. . .» እንዲሉ፥ ለክርክሩ መነሾ የሆነው ምን እንደሆነ እና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፥ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርታ እንዴት መልስ እንደሰጠች እናሳያለን።
፩. « እምነት ብቻ» የሚለው አስተሳሰብ የተገኘው ከየት ነው?
የፕሮቴስታንት እምነት መሥራች የሆነው ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር ነው። ማርቲን ሉተር የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መነኩሴ የነበረ ሲሆን፥ ከእግዚአብሔር ቁጣ ስለመዳን፥ ስለፍርድ በጣም ይጨነቅ ነበር። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረውን ችግርና የራሱን መንፈሳዊ ትግል አስመልክቶ ሲያጠና፥ « ሰው በእምነት ብቻ ይድናል» የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰ።
፪. ይህ « እምነት ብቻ» የሚለው ሐረግ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አለ ወይ?
በጭራሽ የለም። እነዚህ ሁለት ቃላት፥ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የቀየሩና ለብዙ ዲኖሚኔሽኖች መፈጠር ምክንያቶች ናቸው፥ነገር ግን ወደ ነገረ መለኮት ውይይት ውስጥ የገቡት፥ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመገኘታቸው አይደለም። ማርቲን ሉተር ለአሳቡ ደጋፊ የሆነ ንባብ አድርጎ ያሰበው፥ ሮሜ ፫፥፳፰ን «ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና።» የሚለውን ነው። እርሱ ከቀመረው አስተምህሮ ጋር ለማስማማት፥ ይህን ንባብ ወደ ጀርመን ቋንቋ ሲተረጉም «ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት ብቻ (allein) እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና።» ብሎ ነበር የተረጎመው። ነገር ግን « ብቻ ( allein)» የሚለው ቃል በግሪኩ ንባብም ሆነ በዓውዱም የለም።
፫. ይህ « እምነት ብቻ» የሚለው ቃል የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ነውን?
አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው በተቃራኒው ነው ። የሚገርመው « ብቻ » ወይም በላቲኑ ( sola) የሚለው አነጋገር፥ ከእምነት ጋር በተገናኘ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰው በአሉታ ነው። የሚገኘውም በያዕ ፪፥፳፬ ላይ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ «ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።You see that a person is considered righteous by what they do and not by faith alone.» ይላል። በጥንቃቄ አንብቡት። በሌላ አነጋገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኘው ሐረግ «እምነት ብቻ ( faith alone)» የሚል ሳይሆን፥ በእምነት ብቻ ሳይሆን not by faith alone)» የሚል ነው።
፬. ማርቲን ሉተር ሮሜ ፫፥፳፰ን በተሳሳተ መንገድ እንዲያነብ ያደረገው ምንድነው?
ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን የነገረ መለኮት ሊቃውንት እንደሚናገሩት፥ ማርቲን ሉተርን ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ የወሰዱት ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ናቸው። አንደኛ፥ በጊዜው በሮም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያያቸውን ስህተቶች ለማረም በሚል መነጽርነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ መሞከሩ። ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበው፥ በተቃውሞ (protest) መንፈስ መሆኑ ነው። ይህም አጠቃላይ የመጽሐፉን መንፈስ ከመገንዘብ ይልቅ፥ እርሱ መፍትሔ አድርጎ ያሰበውን አሳብ ደጋፊ ጥቅስ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲፈልግ አድርጎታል። ሁለተኛው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሌለ ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላነበበውን ( በግሪኩም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች የሌለ) ብቻ የሚለውን ቃል ጨምሮ ማንበቡ ነው።
፭. ሮሜ ፫፥፳፰ን ማርቲን ሉተር እንዳነበበው ማንበብ የማንችለው ለምንድነው?
ምክንያቱም ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስና ከሐዋርያቱ ትምህርት ጋር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን ስለሆነ ነው። ለምሳሌ እንደ ማርቲን ሉተር አተረጓጎም ካነበብን ሮሜ ፫፥፳፰ና ያዕ ፪፥፳፬ እርስ በእርሳቸው ይቃረናሉ። ሮሜ ፫፥፳፰ « ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና» የሚል ነው። ያዕ ፪፥፳፬ ደግሞ « ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ» ይላል።
፮ . ማርቲን ሉተር እነዚህን ሁለቱን እንዴት አስታረቃቸው?
እንደማርቲን ሉተር አተረጓጎም ከሆነ በጭራሽ ለማስታረቅ አንችልም። ምክንያቱም ማርቲን ሉተር « ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለን» የሚለውን የተረዳው « ያለሕግ ሥራ» የተባለው መልካም ሥራ በሙሉ እንደሆነ ነው። መፍትሔ አድርጎ ያቀረበውም፥ የያዕቆብ መልእክትን ሙሉ በሙሉ መቃወም ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ውጪ እንዲሆን ነበር ሐሳብ ያቀረበው። የያዕቆብ መልእክትን ሲቃወም « ይህ መልእክት፥ የቅዱስ ጳውሎስን መልእክታትና የተቀሩትን ቅዱሳት መጻሕፍት የሚቃወም፥ ጽድቅ በሥራ እንደሚገኝ የሚያስተምርና፥ አብርሃም በሥራ እንደጸደቀ የሚያወራ ነው። . . . በመሆኑም የያዕቆብ መልእክት ገለባ መልእክት ነው። . . . ምንም ዓይነት የወንጌል ጠባይ የለበትም።» ነበር ያለው። ይህ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተነገረ የድፍረት አባባል፥ በኋላ ዘመን ላየነው መጠነ ሰፊ ክህደት በር የከፈተ ነው።
ምንም እንኳ ከማርቲን ሉተር አቋም ጋር ስለ ያዕቆብ መልእክት ባይስማሙ፥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሙሉ በሙሉ የፕሮቴስታንት ሊቃውንት ሮሜን የሚያነቡት እንደ ማርቲን ሉተር ነበር። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያልኩበት ምክንያት በቅርብ ጊዜ፥ በፕሮቴስታንቱ የአዲስ ኪዳን ሊቃውንት ዘንድ ከፍተኛ ነውጥ ያመጣ አዲስ እይታ መጥቷል። ይህም ስለ ቅዱስ ጳውሎስ አዲሱ እይታ The New Perspective on Paul የተሰኘ እንቅስቃሴ ነው። የዚህ እንቅስቃሴ አራማጆች፥ የአውሮፓ የተሐድሶ ሊቃውንት ማርቲን ሉተርንም ጨምሮ ሮሜን እና ገላትያን ያነበቡት፥ የመጀመሪያዎቹ የመልእክቱ ተቀባዮች ( first audience) መልእክቱን ሲቀበሉ ካነበቡበት ውጭ ነው። እንዲሁም በዚያ ዘመን የነበረውን ይሁዲነትና ከእርሱ ጋር ተያይዞ ያለውን ትውፊት የሚያመለክት አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ ጸጋንና ሕግን እምነትንና ሥራን አጣርሶ አላስተማረም፤ የሕግ ሥራ ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ለምሳሌ በዚህ በሮሜ ፫፥፳፰ ላይ የጠቀሰው፥ የማንነት መለያዎች ( identity markers) ተብለው የሚታዩትን ግዝረትን፥ ሰንበት ማክበርን፥ እና ሌሎችን እንጂ መልካም ሥራን አይደለም አይደለም ብለው ማስተማር ጀምረዋል።
ነገሩ ምዕራባውያን አሜሪካን ሲደርሱ፥ ከእነርሱ ቀድመው ለሁለት ሺ ዓመታት የኖሩትን ሕዝቦች ረስተው አዲስ ዓለም ( New World) እንዳሉት ነው እንጂ፥ አዲስ አተረጓጎም ሆኖ አይደለም። የጥንት መተረጉማን ይህን ዓይነት አተረጓጎም ተከትለው እናገኛለን። ለምሳሌ ታዋቂው መተርጉም አርጌንስ ( Origen of Alexandria, Commentary on Romans 8.7.6)የላቲኑን ቩልጌት የጻፈው ኢያሮኒሙስ (Jerome, Commentary on Galatians 1.3.2 ) አምብሮሲያስተር ( Abrosiaster, Commentary on Romans 3:28) የአንጾኪያውን ትርጓሜ አካሄድ የሚወክለው Theodret of Cyrrhus, Commentary on Galatians) መመልከት በቂ ነው።
፯ ። ሮሜ ፫፥፳፰ን እንዴት እንተርጉመው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በምናነብበት ወቅት የጥቅሶቹን አውድ ( context) መመልከት መልካም ነው። በመሆኑም ለምሳሌ ሮሜ ፫፥፳፰ን ለማንበብ፥ አንቀጹን ማለትም ሮሜ ፫፥፳፯_፴፩ ያለውን ማንበብ አለብን። አንቀጹን ለመረዳት ደግሞ እስከዚህ ንባብ ድረስ ድረስ ቅዱስ ጳውሎስ ምን እንዳስተማረ መመልከት አለብን ። ከሮሜ ፩፥፩-፲፯ ድረስ በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን የመዳን ወንጌል ( መልካም ዜና) ለአይሁድም ለአሕዛብ እንደተሰጠ ይናገራል። ከሮሜ ፩፥፲፰ እስከ ፫፥፳ ድረስ እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ የሚታየውን አመጽና በእስራኤላውያን ዘንድ ያለውን ለሕጉ አለመታዘዝ ዝም ብሎ እንደማያይ ወደ ፍርድ እንደሚያመጣ ይናግራል። ሮሜ ፫፥፳፩-፳፮ እግዚአብሔር ይህን በፍርድ ሥር ሊወድቅ ያለውን ዓለም ለማዳን፥ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጽድቁን እንዴት እንደገለጠ ያስተምረናል። ይህ በሌላ በኩል በዚያ ክፍል ላይ «በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፥ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና።» በማለት በሮሜ ፩፥፲፮-፲፯ ላይ የገለጠውን መልካም ዜና ሲያብራራ ነው።
በሮሜ ፫፥፳፯-፴፩ ሐዋርያው ይህን የተገለጠውን ጽድቅ አይሁድም አሕዛብም በእኩልነት በእምነት እንደሚያገኙት እንጂ አይሁድ በማንነታቸው መገለጫ በሆነው በግዝረታቸው እንደማያገኙት በዚህም መኩራራት እንደሌለባቸው ያብራራል። እስቲ ቍጥር በቍጥር እንመልከተው። ቍ ፳፯ እንዲህ ይላል፦ «ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ።» ሁለት ዓይነት ትምክህትን እዚህ ላይ እናያለን። የመጀመሪያው « በሥራ ሕግ» መመካት ነው። በሮሜ ፪ ላይ የተገለጠውና በአይሁዳዊ ማንነት ላይ የተመረኮዘ ነው፤ክርስቲያን ለመሆን መጀመሪያ አይሁዳዊ መሆን አለብህ የሚለው ትምክህት። ነገር ግን «የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ » ( ፫፥፳) ይህ ትምክህት ቀርቷል። አስተውሉ ቍ.፳ እና ቍ. ፳፯ ላይ የምናገኘው « የሕግ ሥራ ወይም የሥራ ሕግ» አይሁዳዊ ማንነትን የሚያመለክት ነው። ይህ ትምክህት ቀርቷል። ሌላው ትምክህት « የእምነት ሕግ» ነው። ይህ በክርስቶስ በማመን የሆነ ትምክህት ነው። አይሁድም አሕዛብም ሁሉም ወደዚህ የእግዚአብሔር ጽድቅ የሚገቡት፥ የእግዚአብሔር ጽድቅ ሆኖ በተገለጠው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ነውና።
ቍ ፳፰ እንዲህ ይላል። « ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና።» እስከ አሁን ያብራራነውን አሳብ በሚገባ ከተመለከትን፥ እዚህ ላይ « ያለ ሕግ ሥራ» ሲል ያለ መልካም ሥራ ማለቱ አይደለም። አይሁዳዊ ሳይሆኑ ማለቱ ነው። አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ጽድቅ ለመግባት አይሁዳዊ መሆን ወይም አይሁዳዊ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ሥርዓቶች መፈጸም የለበትም። ወደዚያ ጽድቅ ለመግባት የሚያስፈልገው በክርስቶስ ማመን ነውና። ሐዋርያው ይህን ሲያስረግጥ፥ በሚቀጥለው ቍጥር ላይ፥ « ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን? አዎን፥ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አምላክ አንድ ስለ ሆነ የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው።» በማለት እግዚአብሔር ወንጌልን ለሁሉም ማለትም ለአይሁድም ለአሕዛብም እንደሰጠ አድልዎ እንዳላደረገ ይናገራል።
፰. ቅዱስ ጳውሎስ ጽድቅን ከእምነት ጋር ብቻ አላያያዘውም?
ቅዱስ ጳውሎስ ጽድቅን ከእምነት ጋር «ብቻ» አላላያዘም። ለምሳሌ በሮሜ ፮፥፫-፮ በ፩ ቆሮ ፮፥፮ ይህ ጽድቅ በእኛ ሕይወት እውን የሚሆነው በጥምቀት እንደሆነ ይናገራል። ይህ ወደ ጽድቅ የሚወስድ እምነትም ባዶ እምነት አይደለም። ወይም የአእምሮ ምጥቀት (intellectual assent)አይደለም። መልካም ሥራ ያለው « በፍቅር የሚሥራ እምነት » (ገላ ፭፥፮) መታዘዝን በውስጡ ያዘለ እምነት ( ሮሜ ፩፥፭) ነው።
፱. የቅዱስ ጳውሎስን መልእክታን ስናነብ ልንከተለው የሚገባን መመሪያ ምንድነው?
የቅዱስ ጳውሎስን ብቻ ሳይሆን ማናቸውንም የቅዱስ መጽሐፍ ክፍል ስናነብ፥ አንደኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከሌላው ጋር ማገናዘብ ይኖርብናል። በተለይም የእምነታችን ጀማሪና ፈጻሚ የሆነውን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ወንጌል በጥንቃቄ ማንበብ አለብን። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ያስተማራቸውን ትምህርቶች ወደጎን ካደረግን፥ ዛሬ በምዕራቡ ዓለም የክርስትና መሥራች ቅዱስ ጳውሎስ ነው ተብሎ እስኪነገር ድረስ እንደሆነው፥ ሚዛናዊነትን ያጣ አስተምህሮ ወደ መቅረጽ እንደርሳለን። ይህ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን፥ ገና በሐዋርያት ዘመን ችግር ሆኖ እንደነበር፥ በ፪ ጴጥ ፫፥፲፭-፲፮ የተጻፈው ቃል ያሳስበናል። «የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።»
በነገራችን ላይ፥ ብዙዎች መተርጉማን እንደሚስማሙበት፥ ቅዱስ ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት በመቃወም ሳይሆን፥ ቅዱስ ጴጥሮስ የተናገራቸውን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት የሚያጣምሙትን ለማረምና ለማቃናት ነው።
፲. የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት ስለ እምነት እና ሥራ የሚያስተምረን ምንድነው? (ይቀጥላል)