መፃጉዕ 

“ልትድን ትወዳለህን” (ዮሐ.ምዕ 5ቁ6-7)

 መፃጉዕ

የጌታ መልአክ ቀርቦ
ፀጥ ያለውን ውኃ ሲያናውጠው
ሕሙማኑ ሲሽቀዳደሙ
የደከመው ከድካሙ
የታመመው ከሕመሙ
ተስፋ አድርጎ በእምነቱ
ቀርቦ ሲያየው ምልክቱ
የደህንነት ነፃነቱ
ፈውስ ሊሆን ሽልማቱ
የቆየበት የትዕግስቱ
አቤት!ያ መፃጉዕ ምን ይውጠው
መንገድ ላይ ተጥሎ እንደውዳቂ
ዕርቃኑን ሸፍኖ በልብስ እላቂ
ክረምትና በጋው ሲፈራረቅበት
የፀሐዩ ሀሩር ዋዕዩ ሲያቃጥለው
የሠራ አካላቱን እንደ እንጨት ሲያደርቀው
ፊቱንም አጥቁሮ ከሰል ሲያስመስለው
ዝናብና ዶፍ ሲወርድበት
ነጎድጓዱ ሲጮህበት
ብልጭልጭታው የመብረቁ
ድንጋጤው ልቡን ሰንጥቆ እየገባ
እሞት ይሆን እያለ እየባባ
የሐዘን ልቅሶ እያነባ
ለዘመናት ጀርባ ቆስሎ
ሥጋው ከድቶት ታሞ ዝሎ
እጅና እግሩ ተሽመድምዶ
ዐይኑ ሟሙቶ ፀጉሩ ረግፎ
በእህል አምሮት ምራቁ ለሀጭ ሆኖ
አረፋ እየደፈቀ
እህል ውኃ የሚሰጠውን እየናፈቀ
ሞት የጠላው ኃጢአተኛ
ድህነት የራቀው አበሰኛ
ለስንት ዓመት እዚህ ተኛ
እያሉ ሲሳለቁበት
ጣታቸውን እየቀሰሩ ሲያሾፉበት
ለዐይናቸው እንኳ ሲፀየፉት
ተሰብስበው ሲመክሩበት ምስኪኑ መፃጉዕ በአርምሞ
ከራሱ ጋር ሲነጋገር
በጣም ገርሞት የሰው ነገር
የሚያስጠጋው ዘመድ አጥቶ
በአልጋው ላይ ተቆራኝቶ
ሰው መሆኑ ተዘንግቶ
ከነስም አጠራሩ ተረስቶ
ወደ መጠመቂያይቱ ሥፍራ
የሚያደርሰው ጠፍቶ
እያለፈው ሁሉም ሲሄድ
በላዩ ላይ ሲረማመድ
ዐይኑ ብቻ ሲንከራተት
ፈውስን ሽቶ ፀንቶ በእምነት
ይኸው እሰይ! እሰይ! ዛሬስ አለፈለት
አንድ ቃል ብቻ ሲገኝለት
መዳኑን ሲያበስርለት
ቁርጭምጭሚቱ ፀንቶ
ኃይልና ጉልበትን አግኝቶ
ባለውለታውን አልጋውን አንስቶ
ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቶ
ፈጣሪውን ከልብ ፈርቶ
ተአምሩን ለመናገር ሽቶ
አልቀረም መፃጉዕ አልጋ ላይ ተኝቶ
መመስከር ጀመረ መንደር ውስጥ ገብቶ።

ከኃይለመስቀል ተስፋዬ

24/03/07(ለንደን)

 

Close Menu